ኢሳት ዜና:- ግንቦት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
የፌዴራል የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን
ሠራተኞቹን አንድ ለአምስት በሚል አደረጃጀት በማዋቀር በሥራ ሰዓት ጭምር ስብሰባዎችን በማካሄድ ሠራተኛው እርስ
በርስ እንዳይተማመን የማድረግ አሠራር ተግባራዊ በማድረጉ በሥራ ዋስትናቸው ላይ ከፍተኛ አደጋ መጋረጡን አንዳንድ
ሠራተኞች አስታውቀዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የልማት ሠራዊት ለመገንባት በሚል ሠራተኛው አንድ
ለአምስት እንዲደራጅና በየዕለቱ ከ30 ደቂቃ ላላነሰ ግዜ በቀኑ ውስጥ ባጋጠሙ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በሚል ሰበብ
ስብሰባ እንደሚቀመጥ ሰማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሠራተኞች ተናግረዋል፡፡
በስብሰባዎቹ ላይ ለየት ያለ ኀሳብ ማቅረብ
እንደማይቻል፣ከቀረበም “የአመለካከት ችግር አለብህ ወይም አለብሽ” የሚል ዛቻና ማሸማቀቅ የተለመደ ክስተት መሆኑን
ጠቁመዋል፡፡ሠራተኞቹ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አገራችንን በሙያችን ለማገልገል አስበን የተቀጠርን ቢሆንም ሳንወድ
በግድ እንድንደራጅ ተደርጎ በየቀኑ የሚደረገው ስብሰባ ውጤት ለአለቆች የሚላክበት ሁኔታ መፈጠሩ የሥራ ዋስትናችንን
አደጋ ላይ እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ
ሰራተኞች ከተጠረጠሩ የማባረረ ሥልጣን እንዳለው የጠቆሙት ሰራተኞቹ በአሁኑ ሰዓት ግን በፖለቲካ አመለካከት ብቻ
ሰራተኞች ከሥራ የሚባረሩበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡በዚህ ዓመት ብቻ ከ300 በላይ ሰራተኞች
መባረራቸውንም በምሳሌነት አንስተዋል፡፡
በአቶ ጁነዲን ሳዶ የሚመራው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ይህን
ዓይነቱ አሰራር“የልማት ሠራዊት ” በሚል ስያሜ የሚጠራው ሲሆን በሁሉም የመንግስት መ/ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ
አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በ2002 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ይህ የአንድ ለአምስት አደረጃጀት
ኢህአዴግን የ99 በመቶ ባለድል ካደረገው ወዲህ አደረጃጀቱ ለምርጫ ብቻ ሳይሆን ለልማትም መጠቀም አለብን በሚል
አደረጃጀቱ ወደ መንግስት መ/ቤቶች ለማውረድ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ኢህአዴግ የ2002ን ምርጫ
ለማስፈጸም ባወጣው የስትራቴጂ ወረቀት ላይ ፡“ …ከኢትዮጽያ ሕዝብ ውስጥ ከግማሸ በላይ የሚሆነው ዕድሜው ከ18
ዓመት በታች በመሆኑ የመራጩ ቁጥር ከ30 ሚሊየን በላይ ሊሆን እንደማይችል ይገመታል፡፡ከዚህ ውስጥ ቢያንስ አራት
ሚሊየን ያህሉ የድርጅታችን አባል ነው፡፡
እያንዳንዱ አባል በቀላሉ ሊቀርባቸውና ሊያሳምናቸው የሚችል ቢያንስ አራት
ወዳጆችና ዘመዶች አሉት ብንል እነዚህ ተደማምረው 20 ሚሊየን ይሆናሉ፡፡በእነዚህ ብቻ ቢያንስ 2/3 ኛውን ድምጽ
ማግኘት ይቻላል…”ሲል የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን ጠቀሜታ ገልጧል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በመንግስት መ/ቤቶች
ለማስረጽ እየተሞከረ ያለው የአንድ ለአምስት አደረጃጀት በሕዝብ ሐብትና ንብረት የኢህአዴግ ቀጣይ የምርጫ ድጋፍ
ማሰባሰቢያ፣ አዳዲስ አባላትና ደጋፊዎችን የመመልመያ ስትራቴጂ እንጂ የልማት ጥማት አለመሆኑን አንዳንድ ወገኖች
ከወዲሁ ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ኢህአዴግ በምርጫ 2002 በ99 ነጥብ 6 በመቶ ማሸነፉን መግለጹ በአለም አቀፍ
ደረጃ መሳለቂያ እንዳደረገው ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment