Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Tuesday, May 22, 2012

በሰሜን ጐንደር ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ከሁለት ሺህ በላይ ገበሬዎች ከእርሻ መሬቶቻቸው ተፈናቅሉ ተባለ

 By www.fetehe.com
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ጐንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የሚኖሩ ከሁለት ሺህ በላይ ገበሬዎች ለአመታት እያረሱ ከሚያለሙት የእርሻ መሬታቸው በተለይ ከባለፈው ወር ጀምሮ በኢንቨስትመንት ሰበብ መፈናቀላቸውን የፍትህ ምንጮች ገለፁ።

ከስድስት እስከ አስራ አምስት ዓመት ያህል እንደያዙት የእርሻ መሬት ስፋት መጠን ለመንግስት  ተገቢውን ግብር በመክፈል መሬታቸውን በማልማት ይተዳደሩ እንደነበረ የሚናገሩት እነኚህ ገበሬዎች፣ የማፈናቀል ሂደቱ ከጀመረበት ከሶስት ወራት ወዲህ በአጠቃላይ መፈናቀላቸውን ምንጮች ያስረዳሉ። ለገበሬዎቹ መፈናቀል ዋናው ምክንያትም ከሌላ አካባቢ ለመጡ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት ኢንቨስተሮች መሬታቸው መሰጠቱ ነው።

‹‹ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ለመሬቱ ውል አልያዛችሁም ተብለናል። እኛ ደግሞ ውል ያልሰጣችሁን እናንተ ናችሁ የሚል መልስ ስንሰጣቸው ከአሁን በኋላ ለአዲስ ሰው እንጂ ለሌላ ለነባር አንሰጥም ተባልን›› የሚሉት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ‹‹እየተሰራ ያለው ስራ ይዘገንናል›› በማለት ለፍትሕ ተናግረዋል።

‹‹እህል አብቃይና እህል የማያበቅል መሬት›› እየተባለ እንዲጠቀሙ ለተፈለጉ አካላት ጥሩ ቦታ፣ እንዲጠቀሙ ላልተፈለጉት ደግሞ ለእርሻ ስራ የማያመች መሬት ተለይቶ መስጠቱን ምንጮች በሃዘኔታ አስረድተዋል። ለአመታት ተገቢውን ህጋዊ ግብር የሚከፍሉበትን የእርሻ መሬት እየተነጠቁ ለባለሃብቶችና ለኢንቨስተሮች ሲሰጥ በተባለው መሰረት ምትክ ቦታ እንዳልተሰጣቸው ገበሬዎቹ ገልፀዋል።

ለችግራቸው መፍትሄ ለማግኘት የሰሜን ጐንደር መስተዳድር ጋር በተደጋጋሚ በመመላለስ የመስተዳሩ ኃላፊ የሆኑትን አቶ ግዛው አማረን ቢያነጋግሩም ‹‹አሁን ምንም እንዳትናገሩ፣ ሄዳችሁ ወረዳቸውን ጠየቁ›› የሚል መልስ ማግኘታቸውንና ወረዳውም ‹‹ዞኑን ጠይቁ›› እንዳላቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ ያልፈለጉት የአካባቢው ነዋሪ ለፍትህ ተናግረዋል።

‹‹የዘንድሮ እርሻ ሊጀምር የቀረው ሶስት ወር ነው፡፡ ግብር ከምንከፍልበት መሬት ተፈናቅለናል፡፡ የአርማጭሆ ህዝብ እየተፈናቀለ ይገኛል፡፡ ህብረተሰቡ ከቀየው ከተነቀለ የት ሊሄድ እንደሚችል ማሰብ ነው›› በማለት ተፈናቃዮች ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ፍትሃዊ የሆነ የመሬት ክፍፍል ሊያገኙ እንደሚገባና አድሏዊ ስራ መስራቱ ሊቆም እንደሚገባ ያስገነዘቡት ምንጮች ‹‹የሚመለከተው አካል ለችግራቸው አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠንና መሬታችንን ሊመለስልን ይገባል›› በማለት በምሬትና በሀዘን ለፍትህ ተናግረዋል። 

የፍትህ ዘጋቢም ጉዳዩ ወደሚመለከተው ወደ ሰሜን ጐንደር አስተዳደር ቢሮ ስልክ ብንደውልም የቢሮው ስልክ ስለማይመልስ ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም።

No comments:

Post a Comment