Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, May 23, 2012

ሚኒስትሩን የዘለፈችው ሙስሊም ወጣት፤ በደህንነቶች በደረሰባት አሰቃቂ ድብደባ ህይወቷ ማለፉ ተነገረ

ኢሳት ዜና:- ግንቦት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩን ስብሰባ ላይ የዘለፈችው ሙስሊም ወጣት፤ በደህንነቶች በደረሰባት አሰቃቂ ድብደባ ህይወቷ ማለፉ ተነገረ።ይህ አሳዛኝ ዜና ይፋ የሆነው፤የብዙሀኑ ሙስሊም አስተባባሪ  አካል የሆነው “ድምፃችን ይሰማ” ኮሚቴ ፦አሳዛኝ የግፍ ዜና”በሚል ርዕስ ያሰራጨው መረጃ  ነው።

በቅርቡ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሙስሊሞችን ጥያቄ በተመለከተ ከየክፍለ-ከተማው ሰዎችን በመምረጥ ስብሰባ አካሂዶ እንደነበር ያወሳው ኮሚቴው፤በዚሁ ስብሰባ ላይ ከኮልፌ ክፍለ-ከተማ ሁለት ወንዶች እና ፍርዶስ የተባለች ወጣት  ሴት መሳተፋቸውን አመልክቷል።

ስብሰባውን ሲመሩ የነበሩት ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም  ብዙሀኑን ሙስሊም ያስተባብሩ ዘንድ በተመረጡት የኮሚቴ አባላት ላይ አስፀያፊ እና ድንበር ዘለል ንግግሮችን ሲደጋግሙ መደመጣቸውን የጠቀሰው ኮሚቴው፤የሰውዬውን ዘለፋና ስድብ መሸከም ያቃታት እህት ፍርዶስ የእልህ ሲቃ እየተናነቃት ሚኒስትሩን ዘልፋ የስብሰባ አዳራሹን ለቅቃ መውጣቷን አብራርቷል።

ከአዳራሹ ወጥታ በ አቅራቢያው ወዳቆመቻት ቶዮታ ቪትዝ የግል መኪናዋ በመግባት ወደመጣችበት ለመመለስ መንቀሳቀስ እንደጀመረች በሁለት ላንድክሩዘር መኪኖች የሞሉ ደህንነቶች ተከትለው በማስቆም እሷንም፤መኪናዋንም ይዘው መሰወራቸውን ኮሚቴው አጋልጧል። “ከዚያም እህታችን ፍርዶስን  በሚያሰቅቅ እና በሚዘገንን መልኩ በኤሌክትሪክ “ሾክ”እያደረጉ አቃጠሏት” ያለው ኮሚቴው፤በዚህም ምክንያት ወጣት ፍርዶስ ወዲያውኑ መናገርም፤መንቀሳቀስም ማቆሟን ገልጿል።

እንደ ድምፃችን ይሰማ መግለጫ፦ደህንነቶቹ በፍርዶስ ላይ የተጠቀሰውን የጭካኔ ድርጊት ከፈፀሙባት በሁዋላ  ከነ መኪናዋ መኖሪያ ቤቷ በሯ ላይ ጥለዋት ሄደዋል። በሁኔታው ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ የወደቁት የፍርዶስ ቤተሰቦች ልጃቸውን ለመታደግ  ሩጫ መጀመራቸውን የጠቀሰው ኮሚቴው፤ሆኖም የደረሰባት ጉዳት እጅግ ከባድ በመሆኑ ጥራታቸው ሁሉ ከንቱ መቅረቱን ነው ያመለከተው።

በሆነው ነገር ልባቸው በሀዘን የደማው የፍርዶስ አባት  የልጃቸውን ህይወት ለማትረፍ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለህክምና  ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ይዘዋት ቢሄዱም፤ ደህንነቶቹ ባደረሱባት የኤሌክትሪክ ቃጠሎ በርካታ አካሎቿ ከጥቅም ውጪ በመሆናቸው ወጣት ፍርዶስ እስከወዲያኛው ተሰናብታለች። የከፋው አሳዛኝ ነገር  የወጣት ፍርዶስ ህይወት ማለፉን ተከትሎ ወላጅ እናቷ  በደህንነቶች ታፍነው መወሰዳቸው ነው ይላል ኮሚቴው።

ወላጅ እናቷን አፍነው የወሰዷቸውም የፈፀሙት አሰቃቂ ግፍ እንዳይሰማባቸው ለማድረግ በማሰብ ነው ብሎ እንደሚያምን የድምጻችን ይሰማ ኮሚቴ ገልጿል። መምህር የኔሰው ገብሬ ፦”ፍትህ በሌለበት አገር መኖር አልፈልግም”በማለት ራሱን ማቃጠሉን ተከትሎ የደህንነት አባሎች ፦”መረጃ እንዳትሰጥ”በሚል እህቱን በመኖሪያ ቤቷ አፍነው ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

ወጣት ፍርዶስ እሷን እና ጓደኞቿን  እላፊ እየተናገሯቸው የነበሩትን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩን በንዴት  በመዝለፏ ሳቢያ  በኤሌትሪክ ሾክ እየተደረገች እንድትሞት መደረጉን የሰሙ እትዮጵያውያን፤ሰሞኑን ጋዜጠኛ አበበ ገላው ፦ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የተቃወማቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ባለ ስብሰባ ላይ ቢሆን ኖሮ ምን ሊያደርጉት ይችሉ እንደነበር መገመቱ ቀላል ነው ብለዋል። 

ኢሳት የሟቹዋን ቤተሰቦች ለማነጋገር አደረገው ጥረት አልተሳካለትም። የኢትዮጵያ መንግስትም በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው አስተያየት የለም።

No comments:

Post a Comment