በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በተለምዶው መገናኛ በሚባለው አካባቢ ማንነትዋ ያልታወቀ ሴት ህይወቷ አልፎ በአካባቢው በሚገኝ ገደል ውስጥ ተጥላ፣ እንዲሁም በአውሬ ተበልታ በትናንትው ቀን መገኘቷን የፍትህ ዘጋቢ በቦታው ተገኝቶ ለመመልከት ችሏል፡፡
30 ዓመት እንደሚሞላት የተገመተችው ይህች ወጣት ትናንት አስከሬኗ የተገኘ ሲሆን ግድያው መቼ እንደተፈፀመና አስክሬኗም መቼ በስፍራው እንደተጣለ የታወቀ ነገር የለም። በቦታው የተገኘው የፍትህ ዘጋቢም አስክሬኑ የቆየ መሆኑን ለማየት የቻለ በመሆኑ ከፊል የሰውነት አካሏ በአውሬ መበላቱን አረጋግጧል።
ዘጋቢውም ስለሟቿ የበለጠ መረጃ እንዲሰጡት በአካባቢ የነበሩትን የፖሊስ አባላት ቢጠይቅም ፖሊሶቹ ‹‹ገና ነው… ምንም ስላላወቅን መረጃ ልንሰጥ አንችልም።›› በማለታቸው ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። ለህትመት እስከገባንበት ሰአት ድረስ ማንነቷን የሚገልፅና ዘመድ ነኝ ብሎ የመጣ አካል አለመኖሩን ለማወቅ ተችሏል።
Source: www.fetehe.com
No comments:
Post a Comment