ልምሰል የሞላለት
አዎ "ልምሰል የሞላለት ! "
በልቸ ጠጥቸ ስለኖርኩ በድሎት i
መብቴ ተገፎ አጥቼ ነጻነት ፤
በስደት ሃበሳ ስኖር ስንከራተት፤
የደላኝ ይመስላል ! አኗኗሬን ሲቃኙት፤
የደላኝ ይመስላል ! ተክለ ቁመናየን መላብሴን ሲያዩት፤
የደላኝ ይመስላል! ስናገር ሲያደምጡኝ የምኖር በስኬት !
ታዲያሳ. . . !
በአደባባይ ልሳቅ ከቶ ምን አለበት ፤
በደስታ ልምነሽነሽ ልምሰል የሞላለት ፤
ኑሮ ግብግቡን አስተውለው ሲያዩት፤
ድብብቆሽ ኑሮ፤ አለፋውን ስቅየት ፤
የመንገዱን ርቀት ፤ የሰው ልጅን ክፋት፤
ሲታዘቡት ውለው ሲያሰላስሉ ቢያድሩት፤
ምስለኔያችን ከፍቶ ሲደሰኩት ኩሸት፤
ሰብዕና ጠፍቶ ሰው ሁሉ ሲራኮት፤
ወገኔ ዝም ብሏል ቤቱ እስኪደርስበት፤
ደፋር ይናገራል እሱ ምናለበት ፤
"እድል እጣቸው ነው የተፈጠሩበት"
"ለምን መጡ" ይላል መድገፉ ጠፍቶት፤
ይለናል ጎረምሳው መደገፉ ጠፍቶት ፤
ድምጽ ማሰማቱ ፤ውሃ ማቅረብ ገዶት ፤
እናም. . .
ስላየሁ በአይኖቸ ይህን መሳይ ትንግርት፤
ስላየሁ ህይዎቱን የዳፋ ቀማሹ የመሪሩን ስደት፤
ያስታግሰው እንደሁ የንዳድ ቃጠሎ የብሽቀቴን ብርታት፤
ድብቅ ሽሽግ ብየ . . .ሲለኝ አለቅሳለሁ ለመረረው ህይዎት፤
አዎ … እውነት ብለሃል ወንድም አደም
ይህ ነው የእውነቱ ገጽታ የዚህች አለም . . .
"በጨለውማ ተስፋ ፤ጥርሴ ጧፍ ከሆነ ፤
የህይዎቴን ግርዶሽ ገላልጦት ካደረ፤
ምናለ ልሳቀው ባንች ሆየ ቅኝት ፤
ልንከትከት በዜማ ልምሰል የሞላለት !"
© © ©
ወዳጀ አደም ሁሴን ዘራፍ አስባልከኝ እኮ ፡) ! ግጥም ደስ ይላል . . . የላክልኝ ግጥም ውስጤን ነካችውና ከተጋደምኩበት ይህችኑ ቋጠርኩልህ ! ስንኝ መገጣጠሙን በትክክል አሳክቸዋለሁ ባልልም ስሜቴን ካስረዳልኝ ይበቃል! ገጣሚ አይደለሁ እንዳንተ ! ለሁሉም ይህችም ላንተ ትሆን ዘንድ ፈቅጃለሁ !
ነቢዩ ሲራክ
No comments:
Post a Comment