Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Friday, April 27, 2012

የብርሃን እና ሠላም እና የጋዜጣ አሳታሚዎች ተፋጠዋል

ኢሳት ዜና:-
 የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ለአሳታሚዎች የላከው አወዛጋቢው የሕትመት ስምምነት ውል በመቃወም አሳታሚዎች አንድ አቋም በሚይዙበት ሁኔታ ላይ ዛሬ በአዲስአበባ መከሩ፡፡ 

 አብዛኛውን የጋዜጦች ሕትመት ገበያ አማራጭ ባለመኖሩ ምክንያት በብቸኝነት የያዘው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት በቅርቡ ጋዜጦችና መጽሔቶች በሕግ የሚያስጠይቅ ይዘት ያለው ሥራ ማሳተም እንደማይችሉ፣ድርጅቱ የሕግ ተጠያቂነትን ያስከትላል ብሎ ካመነ ለማተም እንደማይገደድ፣ ከነአካቴውም ውል እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ የሚያትት ረቂቅ ውል አዘጋጅቶ አሳታሚዎቹ እንዲፈርሙለት ጠይቋል፡፡ 

ማተሚያ ቤቱ አስገዳጅ በሆነ መልክ አሳታሚዎች ውሉን ካልፈረሙ ቀጣይ ጋዜጦቻቸውን እንደማያትም ጠበቅ ያለ አቋም መያዙ አሳታሚዎችን አስቆጥቷል፡፡  በዛሬው ዕለት በሚዲያና ኮምኒኬሸን ሴንተር ወይም በሪፖርተር ጋዜጣ አስተባባሪነት በርካታ የጋዜጣ እና የመጽሔት አሳታሚዎች ስብሰባ ተቀምጠው ነበር። 

አሳታሚዎቹ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በሁዋላ ከብርሃንና ሰላም የመጣው ውል ቅድመ ምርመራ መሆኑን በመስማማት ውሉን ላለመፈረም ወስነዋል፡፡የውሉ መፈረሚያ የመጨረሻ ቀን ዛሬ በመሆኑ ስለጉዳዩ ከድርጅቱ ኃላፊዎች ጋር የሚነጋገር በአቶ አማረ አረጋዊ የሚመራ ኮሚቴ በማቋቋም ዛሬ ከሰዓት በኃላ ከድርጅቱ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ በመያዝ ተበትኗል፡፡

 ማተሚያ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግለጫ እስካሁን ባይሰጥም ረቂቅ ውሉን ለማዘጋጀት የተገደደው በወንጀል ሕጉ ውስጥ በፕሬስ ጥፋት አታሚውም ጭምር የሚጠየቅበት ሁኔታ የተደነገገ በመሆኑ ከወዲሁ ሕግን በማክበር ሥጋትን ለመቀነስ ታሰቦ የተደረገ መሆኑን ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዘጋቢያችን ጠቁመዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት  በፖለቲካ፣ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ብቻ አተኩረው የሚታተሙ 35 ጋዜጦችና 23 መጽሔቶች በሕትመት ላይ ይገኛሉ፡፡

 በስፖርት፣ በፍቅር፣ በፋሸን፣ በሃይማኖት የሚታተሙት ሲደመሩ የጋዜጦቹ ቁጥር ወደ 83፣ የመጽሔቶቹ ደግሞ ወደ 128 ይደርሳል፡፡ ይሁን እንጅ ከጋዜጦቹ መካከል በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችት የሚያቀርቡት አንድ ወይም ሁለት ብቻ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት ማንኛውንም አይነት ትችት ለመስማት ትእግስቱ እየተሟጠጠ መምጣቱ ይነገራል።

No comments:

Post a Comment