አቤ ቶኪቻው
በወዳጃችን
ዳንኤል ተፈራ የተሰናዳው “ዳንዲ የነጋሶ መንገድ” የተሰኘው መፅሀፍ ላይ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በአንድ ስብሰባ ላይ
አቶ መለስ ዜናዊ እነ ስዬን አጓጉል ሲዘልፏቸው ይሰማሉ። (ምን እያሉ…? ይበሉ እንጂ…) ምን የማይሉት አለ ብዬ
እቀጥላለሁ፤ “አፈንጋጮቹን ጃኬታቸውን አስወልቀን ሸኝተናቸዋል።” በማለት ይናገሩ ነበር። ይሄኔ ዶክተር ነጋሶ ሆዬ
መንጌ በአንድ ወቅት ጀነራሎቹን “ማዕረጋቸውን አስወልቀን ቂጣቸውን በሳንጃ ወግተናቸዋል” ያለው ትዝ አላቸው… ትዝ
ብሏቸውም ዝም አላሉም አቶ መለስን ትኩር ብለው እያዩ “አሁንስ መንግስቱን መንግስቱን መሰልከኝ!” ብለው እርፍ።
እዝች ጋ ከሁሉ ያሳቀኝ ምን እንደሆነ ያውቃሉ የወ/ሮ ገነት ዘውዴ ነገር፤ “እንዴት መለስን ከመንግስቱ ጋር
ታመሳስለዋለህ” ብለው እዛው ስብሰባ መሃል ስቅስቅ ብለው አላለቀሱም መሰልዎ…? ያኔ ወ/ሮ አዜብ በስብሰባው ላይ
መኖራቸውን እንጃ፤ ቢኖሩ ግን ወ/ሮ ገነትን ዝም የሚሏቸው አይመስለኝም።
ሳስበው ወደ ዶክተር ነጋሶ ዞር ብለው “እርስዎ ቆይ እንነጋገራለን… አንቺ ግን ምን ቤት ነሽ እንዲህ
የምትነፋረቂብኝ…” ካሉ በኋላ፤ ወደ አቶ መለስ ደግሞ ዞረው፤ “ስማ እንጂ አንተ የጀመራችሁት ነገር አለ እንዴ…?
እዛች ቤት እንገናኛታለን!” ብለው ሲያመናጭቋቸው አሁንም ያው ወ/ሮ ገነት መቼም አያስችላቸውም እንባ ሳይተናነቃቸው
አይቀርም። ይሄኔ… “አላበዛሽውም እንዴ…!?” እየተባባሉ በስሊፐር ሲጠፋጠፉ ይታየኝ ነበር።
እኔ የምለው ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ግን የት ጠፉ? በነገራችን ላይ ከባለቤታቸው ጋር እንዴት እንደተፋቱ ሰምተዋል…? ቆይ ልንገርዎትማ… ባለቤታቸው ከኢህአዴግ አመራር አባላት መካከል ነበሩ። ታድያ ሲያስቡት ሲያስቡት የኢህአዴግ ነገረ ስራው ምንም
አልጥም አላቸው። እናም “በቃኝ ከእንግዲህ አባልነቱ ይቅርብኝ እና በባልነቱ እንቀጥላለን” ብለው አማከሯቸው። ታድያ
ወ/ሮ ገነት ሆዬ ምን አሉ መሰልዎ… “ከኢህዴግ ጋር ተፋቶ ከእኔ ጋር መኖር አይቻልም ልጅነቴን የሰጠሁት ባሌ
ድርጅቴ ነው። ከድርጅቱ ከወጣህ ከቤቴም ትወጣልኛለህ… መንገዱንጨርቅ ያድርግልህ” ብለው አሰናበቷቸው። (እውነትም
ወ/ሮ አዜብ መጠራጠር አለባቸው… ብለው ግፍ እንዳይናገሩ ወዳጄ…!)
እናልዎ አንዳንድ ተናግሮ አናገሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ዛሬ ዶክተር ነጋሶ አቶ መለስን “አሁንስ መንግስቱን
መንግስቱን መሰልከኝ” ብለው ቢናገሩ እንደዛን ግዜ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ብቻ ሳይሆኑ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስቅስቅ
ብሎ ያለቅስ ነበር ይሎታል።
እንዴት ያላችሁ እንደሆነ “መንጌ ምን በደለን እና ከመለስ ጋር ያመሳስሉታል?” ብለው
ይመልሳሉ።
ለነገሩ ይሄም ተጋኗል። እኔ ይቅርታ አድርጉልኝና መለስ ከመንግስቱ የበለጡ እርኩስ ናቸው ብዬ አላምንም። ይልቅስ መቼለታ አየር ሃይል ሰልጣኞቹን ሲያስመርቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አድርገው ነበር። ታድያ ወደመድረክ
የጋበዛቸው ሰውዬ ምን ብሎ እንደጠራቸው ያውቃሉ…? “የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አቶመለስ ዜናዊ…” በእውነት ክው
ነው ያልኩት ቁርጥ መንግስቱን መሰሉኝ። ለነገሩ ባለፈው ግዜ ተመስገን ደሳለኝ እንደዘረዘረልን ጠቅላይ ሚኒስትሩ
የያዙት ስልጣን መንጌ ይዘውት ከነበረው ይበልጥ እንደሁ እንጂ አይተናነስም።
ከሁሉ ከሁሉ ግን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን አሁን በተለይ ኮሎኔር መንግስቱን ስናብጠለጥልባቸው የነበሩ
ነገሮችን በሙሉ እያሟሉ ይገኛሉ። እንደ እግዜር ፈቃድ በቅርቡ ሚኒማውን በሙሉ አሟልተው ቁርጥ መንግስቱን የሚሆኑ
ይመስለኛል። በየእስር ቤቱ ያለውን ገረፋ እና ስቃይ አናነሳም… ገብስ ገብሱን ለማንሳት ያህል፤ ለምሳሌ ነፃ ፕሬሱ
ላይ የተጋረጠው ነገር፣ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ላይ እደረሰ ያለው፣ የሙያ ማኅበራት እየሆኑ ያሉትን በሙሉ ስናይ
“አሁንስ መንግስቱን መንግስቱን መሰልከኝ” የሚባሉበት ትክክለኛው ግዜ ላይ እየደረሱ ይመስላሉ። ቀለል ያለ ቋንቋ
መጣችልኝ… እንደውም ከአይን ያውጣቸው እንጂ አቶ መለስ ዜናዊ ለአቅመ መንግስቱ ኃይለ ማርያም ደርሰዋል! ብንል
የተሻለ ሳይሆን አይቀርም።
የምር ግን ወዳጄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ አሁን አሁን ጥያቄ ሲጠየቁ ቆጣ ቆጣ ማለታቸውን ስታዩ “ይሄንን ቁጣ
የት ነበር የማውቀው?” ብላችሁ ድንገት መንጌ ትውስ አይሏችሁም። የምሬን እኮ ነው… እውነቱን ለመናገር አቶ መለስ
ከመንጌ የሚለዩት “ኢትዮጵያ የኛ መመኪያ” ሲባል ልባቸው ድንድጥ አለማለቱ፣ ባንዲራ ገልብጠው በየ ሰዉ አገር
መታየታቸው እና የአክሱም ሀውልት ለደቡብ ምኑ ነው በሚለው ፍልስፍናቸው ካልሆነ በስተቀር ከመንጌ ምንም
አይተናነሱም። እሰይ የኔ አንበሳ! አይሏቸውም እንዴ!?
ምስጋና
ለፌስ ቡክ ወዳጄ ቤዚ ቢል ይህንን ፎቶ “ታግ” አድርገህ ለዚህች ጨዋታ አነሰሳስተኸኛልና! ምስጋና ይገባሃል።
No comments:
Post a Comment