Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, April 22, 2012

የግልገል ጊቤ አንድ ግድብ ስጋት ፈጥሯል

By Reporter

የግልገል ጊቤ ቁጥር አንድ የኃይል ማመንጫ ግድብ በደለል የመሞላት ችግር አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው፣ በአገሪቱ ላይ የሚፈጥረው ተደራራቢ ተፅዕኖ ከባድ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስገነዘቡ፡፡ ደለሉን በአፈር በተሞላ ጆንያ ለመከላከል እየተሞከረ መሆኑም  ተገልጿል፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረት ደበበና ከሌሎች ኃላፊዎች ጋር ባለፈው ሐሙስ ውይይት ሲያካሂዱ እንደገለጹት፣ የግልገል ጊቤ ቁጥር አንድ በደለል የመሞላት ችግር አስቸኳይ መፍትሔ ካላገኘ በአገሪቱ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ላይ ከባድ ተፅዕኖ ማስከተሉ የማይቀር ነው፡፡

‹‹እውነት እንነጋገር፤ እንዲያውም እዚህ ስንወያይ ሚዲያ አንፈልግም [ነበር]፤ ጉዳዮችን በደንብ አይተን መሄድ አለብን፤›› በማለት አስተያየታቸውን መስጠት የጀመሩ አንድ የተወካዮች ምክር ቤት አባል፣ ከሁለት ዓመት በፊት የደለል ችግሩን ለመፍታት ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጣ ግብረ ኃይል ቢቋቋምም ችግሩ አሁንም አለመፈታቱን ተናግረዋል፡፡

‹‹እንዳየነው ግድቡ ችግር አለበት፤ በጆንያ አፈር ተሞልቶ ነው እኮ ለመገደብ ጥረት የሚደረገው፡፡ እዚያው ግድቡ ድረስ ሄደን ችግሩን አይተናል፤›› ያሉት እኝህ የፓርላማ አባል፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ረገድ በክልሉም ሆነ በጅማ ዞን የተሠራ ሥራ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በጉዳዩ ላይ ከአሁን በፊትም ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር ውይይት የተደረገ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ምንም የመጣ ለውጥ የለም፡፡

ሌላዋ የፓርላማ አባል በበኩላቸው በቅርቡ ‹‹ናይል ዲስኮርስ ፎረም›› በሚል በተዘጋጀ ወርክሾፕ ግልገል ጊቤ ቁጥር አንድ ግድብ በደለል እየተሞላ መምጣቱን የሚያሳይ ጥናት ያቀረበ አንድ አጥኚ፣ ደለሉ እስከወገቡ ሲውጠው የሚያሳይ ፊልም ለታዳሚው ማቅረቡን፣ ክስተቱን ተከትሎም በቦታው የነበሩ ታዳሚዎች ‹‹በቴሌቪዥን ይቅረብና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይመልከተው›› የሚል ጥያቄ ማቅረቡን የገለጹ ሲሆን፣ ጉዳዩ በፖለቲካ ረገድ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ምን ሊሆን እንደሚችል ሁሉም የሚረዳው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአካባቢው የሚኖረው ኅብረተሰብ ግድቡ አፍንጫ ሥር እንደሚያርስ፣ በቦታው የሚመረተው የበቆሎ አገዳስ የት ነው የሚጣለው? የሚል ጥያቄ እንደሚያስነሳ የገለጹት እኝሁ የፓርላማ አባል፣ ደለሉን በጆንያ በተሞላ አፈር ለመከላከል መሞከር ችግሩን ከማባባስ ውጪ የሚያመጣው ለውጥ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

‹‹የቅንጅት ሥራ ሊሠራ ይገባል፤ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ሰፊ በር ይከፍታል፤ ከህዳሴ ግድቦችና ከሌሎች ግድቦች ጋር ያያይዙታል፡፡ ‘ይኼ መንግሥት የሚያውቀው መገደብ ብቻ ነው ወይ? የገደበውን አይከታተልም?’ የሚል የፖለቲካ አንድምታ የሚያመጣ በመሆኑ ጊዜ ልንሰጠው አይገባም፤›› ሲሉ ጉዳዩ ከኢኮኖሚም አልፎ ከፖለቲካ ጋር የሚገናኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በፓርላማ አባላቱ ከተነሱት በርካታ ችግሮች መካከል የግንባታ ጊዜው ያለፈው የርብ የመስኖ ፕሮጀክት ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ የርብ የመስኖ ፕሮጀክትን ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት የጐበኙ መሆናቸውን የጠቆሙ አንድ የቋሚ ኮሚቴ አባል፣ በዲዛይኑ ውስጥ የካናል ሥራ አለመካተቱን፣ ግድቡም አሁን ባለበት ደረጃ ውኃ የመያዝ አቅም የሌለው መሆኑን ከገለጹ በኋላ፣ ‹‹ካናል በሌለበት ሁኔታ ግድቡ እንዴት አድርጐ ለመስኖ እንደሚውል ግልጽ አይደለም፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አካባቢውን ተዘዋውረው በተመለከቱበትና ኮንትራክተሮችን ባነጋገሩበት ወቅት የመቆፈርያ ማሽኖችና የገልባጭ መኪኖች ችግር እንዳለባቸው የገለጹላቸው መሆኑን የጠቆሙት የፓርላማው አባል፣ በጉዳዩ ላይ ማብራርያ እንዲሰጥ ከሚዲያ ጥያቄ የቀረበላት የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ ‹‹ችግሩ የተፈጠረው በሲሚንቶ እጥረት ነው›› በማለት የሰጡት ምላሽ እነሱ በቦታው ተገኝተው ካዩትና ከተገነዘቡት ጋር የማይመሳሰል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት የርብ ወንዝ የመስኖ ፕሮጀክት 14 ሺሕ ሔክታር የሚጠጋውን የፎገራና የሊቦ ከምከም ወረዳን እንደሚያለማ ቢታወቅም፣ ‹‹አሁን ባለበት ይኼ ይሳካል ወይ?›› የሚል ጥያቄ እንደሚያስነሳ አመልክተዋል፡፡

ከዓመታት በፊት የተጀመረው የደምቢዶሎ የውኃ መስመር ዝርጋታ የዘገየበት ምክንያት ምንድነው? የሚል ጥያቄም ከተለያዩ የፓርላማ አባላት ተነስቷል፡፡ የመብራት አገልግሎት ያገኛሉ ተብሎ መብራት ያልገባላቸው አካባቢዎች መኖራቸውን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ንብረቶች አላግባብ በየቦታው ተጥለው እንደሚገኙ የገለጹ የፓርላማ አባላትም ነበሩ፡፡

ከቋሚ ኮሚቴ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረበላቸው የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ችግሮች ስለመኖራቸው አልካዱም፡፡ የደምቢዶሎ የውኃ መስመር ዝርጋታ የተጓተተው በኮንትራክተሩ አልምጥነት መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በአውሮፓ ኅብረት አበዳሪነት የሚሠራውን ይህንን ፕሮጀክት ከኮንትራክተሩ ጋር ውል በማፍረስ ከማቋረጥ ይልቅ በኮንትራክተሩ ላይ ጫና በማሳረፍ ማሠራት የተሻለ አማራጭ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይኼ ገንዘብ የአውሮፓ ኅብረት ገንዘብ ነው፤ ኮንትራክተሩ የመጣው ከአውሮፓ ኅብረት አገሮች ነው፣ አንድ ቦታ ብትቆነጥጥ ሺሕ ነው የምታስጮኸው፤ ኮንትራክተሩን አንነክሰው ነገር ምን እናድርግ?›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ መንግሥት ኮንትራክተሩን ቢያባርር ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የሚወስደው ጊዜ ረጅም በመሆኑ፣ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ የሚቻለውን ያህል ትግል እያደረገ ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ከኮንትራክተሩ አልምጥነት በተጨማሪ ፕሮጀክት ሊያስተዳድሩ የሚችሉ የውኃ አገልግሎት ባለሙያዎች አለመኖራቸው ሌላው ችግር ነው፡፡ ‹‹ፕሮጀክቱን ለውኃ አገልግሎት አስተዳድር ብለን ብንሰጠው ማስተዳደር ይቅርና ትክክለኛ መረጃ እንኳን ማስተላለፍ የማይችል መዋቅር ነው ያለን፡፡ ይኼ የምንደብቀው ነገር አይደለም፡፡ በውኃ አገልግሎት ላይ ያለው አመራራችን አቅም ውስንነት አለው፡፡ ኮንትራት ማስተዳደር ይቅርና የተዘጋጀውን ውኃ እንኳን በትክክል ለኅብረተሰቡ እያከፋፈለ መልካም አስተዳደር የማይፈጥር ደካማ መዋቅር ነው ያለን፤›› በማለት ሚኒስቴሩ በባለሙያ ደረጃ ያለበትን ችግር ገልጸዋል፡፡

መብራት እንዳገኙ ተደርጐ በሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ የተጠቀሱ አካባቢዎች አገልግሎቱን እንደማያገኙ ታውቋል ተብሎ በቋሚ ኮሚቴ አባላት የተጠቀሰውን በተመለከተም፣ ‹‹እኛ ተሠርቷል በምንለውና ምክር ቤቱ አልተሠራም በሚለው ለመተማመን አዲስ ሪፖርት ማውጣት ይኖርብናል፡፡ ዝርዝሩን ይዘን እንመጣለን፤ ምናልባት ከታች ተሠርቷል ተብሎ እላይ ሊያንሳፍፈን ይችላል፤ መንሳፈፍ ግን አንፈልግም፤ ታች ድረስ መሄድ ይኖርብናል፤ ሰውም አሰማርተን ቢሆን በራሳችን ሰፊ ቁጥጥር ማካሄድ እንችላለን፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የግልገል ጊቤ ፕሮጀክት ችግር በጣም አስከፊ መሆኑን መሥርያ ቤታቸው የተገነዘበው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዓለማየሁ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደተከለለው አካባቢ መግባታቸው ተገቢ አለመሆኑን በማንሳት ከዞኑ አስተዳደር ጋር በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ቢገልጹም፣ ፎረም የተባለው ድርጅት ያቀረበው ጥናት ከበስተጀርባው ያለው ዓላማ ምን እንደሆነ መጠናት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

‹‹አንዳንድ ጉዳዮችን አንስቶ የገንዘብ መፈለጊያና መብያ የሚደረግበት ሁኔታ ስላለ [ጥናቱን] ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ነው የምናየው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የደለል ችግሩን ለመቅረፍ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ሥራ መሠራት አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ከዞኑ ጋር የተግባቡበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በቅርብ ጊዜ ከእነሱ [ከዞኑ አመራሮች ጋር] ስብሰባ አለን፤ ይህ ነገር አንገብጋቢ ነው፤ የእናንተን ነገር [አስተያየት] ወስደን በአካባቢው በሚደረገው የእንክብካቤ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ልንረባረብ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የርብ ግድብን በተመለከተም ቦታውን በአካል ሄደው በጐበኙበት ወቅት አንዳንድ ችግሮች መኖራቸውን የተመለከቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከካናል ዲዛይን ጋር በተገናኘ የነበረው ችግር በጉብኝታቸው ወቅት የተፈታ መሆኑን፣ የነበረውን የገልባጭ መኪኖች እጥረት ለመቅረፍም ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ካስገባቸው 53 ገልባጭ መኪኖች መካከል አሥሩ ወደ አካባቢው የተላኩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዓለማየሁ፣ ግድቡ በአሁኑ ጊዜ ውኃ መያዝ ካልቻለ እንደገና ሌላ ዓመት መጠበቅ የሚያስፈልግ በመሆኑ ‹‹ግድቡ ውኃ መያዝ አለበት›› የሚለው ግብ መሳካት እንዳለበት መግባባት ላይ የተደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ‹‹የርብ ግድብ ግንባታ መዘግየት ከሲሚንቶ እጥረት ጋር የሚያያዝ ነው›› በሚል የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሕዝብ ግንኙነት የሰጠውን ምላሽ በተመለከተም፣ ‹‹በሚዲያ ላይ የተናገረው የሕዝብ ግንኙነት ሰውዬ የሰጠው መግለጫ “Useless” (እርባና ቢስ) ነው፤ የማይጠቅምና መረጃ ሊሆን የሚችል አይደለም፤ ይህንን ገምግመናል፤ አንዳንድ ሰንካላ ምክንያት የሚሰጡ ባለሙያዎች እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል፤›› በማለት ትችት ሰንዝረዋል፡፡   

No comments:

Post a Comment