Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Thursday, September 6, 2012

በአማራ ክልል የመንግስት ስራተኛዉ የወር ደሞዙን እንዲለግስ ተጠየቀ

አ ማ ራ  ክ ል ል 
ኢሳት ዜና:-ሰራተኛው ለአባይ ግድብ ማሰሪያ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀዱትን ልማት ለማስቀጠል በሚል ሰበብ የወር ደሞዙን በግድ እንዲለግስ እየተገደደ መሆኑን የደረሰን ዘገባ ያመለክታል። የመንግስት ሰራተኛዉ በኑሮ ዉድነት እየተንገላታ ባለበት ባሁኑ ወቅት እንዲህ አይነቱን ውሳኔ ማስተላለፍ እጅግ የሚዘገንን ነው በማለት አንድ የመንግስት ሰራተኛ ምሬታቸውን ለኢሳት ገልጠዋል። ከዚህ ቀደም ለአባይ ግድብ ማሰሪያ የከፈሉት ገንዘብ አራቁቷቸው መሄዱን የገለጡት ሰራተኛው አሁን ደግሞ በድጋሚ ለግድቡ ማሰሪያ አውጡ መባሉን ሰራተኛው በሙሉ እየተቃወመው መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጤፍ እና  የአትክልት እጥረት በመላ አገሪቱ መከሰቱ ታውቋል። ምክንያቱ ባልታወቀና ነጋዴዎችም ሲጠየቁ ምላሽ መስጠት ፈቃደኛ ባልሆኑበት ሁኔታ፣ የጤፍ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መናሩ ስጋት እንደፈጠረባቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው። ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፣ ከወር በፊት  1 ሺህ 450 ብር የነበረው አንድ ኩንታል ማኛ ጤፍ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ  አሻቅቦ 2‚100 ብር  እየተሸጠ ነው።

ይህ ማለት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በአንድ ኩንታል ጤፍ ላይ የ 650 ብር ጭማሪ ተደርጓል ማለት ነው። ወቅቱ የበልግ ምርት የሚደርስበት በመሆኑ የተወሰነ የዋጋ ቅናሽ መደረግ ሲገባው ያለምንም ምክንያት መጨመሩ እንዳሳሰባቸው  ለሪፖርተር የገለጹት ወይዘሮ ቀለሟ የተባሉ የ አዲስ አበባ ነዋሪ፤”  “እረኛና ነጋዴ የሚታየው ነገር ይኖራል” በሚል ፍራቻ 420 ብር ይሸጥ የነበረውን ግማሽ ኩንታል ሰርገኛ ጤፍ፣  ለወትሮው ማኛ ጤፍ በሚገዙበት ዋጋ ሸምተው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ነዋሪዎች ጤፍ ከሚመረትበት ቦታ ወይም በቀጣይ የሚፈጠር ችግር እንዳለ በሚል ነጋዴዎቹን ሲጠይቋቸው፦ “ከፈለጋችሁ መውሰድ ትችላላችሁ፤ አለበለዚያ ተውት” እንደሚሏቸው ገልጸዋል፡፡ ከጤፍ በተጨማሪም  እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዱቄት፣ ምስር፣ ባቄላ፣አተር፣ሽምብራ እና ጓያ በመሳሰሉ ለሽሮ በሚያገለግሉ ጥራጥሬዎች  ላይም   እንደ ጤፍ ከፍተኛ ባይሆንም የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ  መስተዋሉን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የኢሳት ዘጋቢ ከ አዲስ አበባ ያጠናቀረው መረጃ እንደሚያመለክተው  በአዲስ አበባ የጤፍ፣የጥራጥሬ እና ከፍተኛ የቅጠላቅጠል እና የአትክልት እጥረት ተከስቷል።

ለወትሮው  የዓመት በዓል ገበያ ላይ ጭማሪ ይታይ የነበረው በቁም ከብቶች፣በበግ፣በዶሮ እና በቅቤ ላይ እንደነበር ያስታወሱ የመዲናይቱ ነዋሪዎች፤ በዘንድሮው የዘመን መለወጫ ዋዜማ ላይ በጤፍ፣በጥራጥሬ እና በአትክልት ላይ እንደዚህ አይነት አስደንጋጭ ጭማሪ መታዬቱ እጅግ አሣስቦናል ብለዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የጤፍ እና የአትክልት ጅምላ አከፋፋዮች አቅርቦታቸውን እስከማቆም  የደረሱ ሲሆን፤በዚህም ምክንያት በዋነኞቹ የጤፍ መገበያያ ገበያዎች በእህል በረንዳ እና በመሳለሚያ  ከትናንት ጀምሮ የጤፍ ግብይት ጨርሶ መቆሙን ዘጋቢዎቻችን ተዘዋውረው አረጋግጠዋል።

አንድ የ አትክልት ጅምላ አከፋፋይ እጥረቱ እንዴት እንደተከሰተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፦”ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ አመራር በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ላይ የጣለብን አዲስ ከፍተኛ ታክስ አቅርቦታችንን እንድናቆም አስገድዶናል” ብለዋል። በታየው የጤፍ ዋጋ ንረትና በሌሎች ሸቀጦች ላይ በተስተዋለው የዋጋ ጭማሪ  ዙሪያ ምክንያቱን  ያብራሩ ዘንድ የሚመለከታቸውን የመስተዳድሩን አካላት  ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

No comments:

Post a Comment