Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Tuesday, September 4, 2012

ወ/ሮ አዜብ አቶ መለስን ለመተካት እየታገሉ ነው



ኢሳት ዜና:- ነሀሴ ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ወ/ሮ አዜብ መስፍን ባለቤታቸውን በሞት ካጡ በኃላ በእሳቸው እግር ተተክተው የህወሃትን የሊቀመንበርነት ቦታ ተቆናጥጦ ወደ ኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርነት ለመሳብ ድጋፍ የማሰባሰብ ዘመቻ ላይ መክረማቸውን ምንጮቻችን ጠቆሙ፡፡

በኢህአዴግ 36 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ብቸኛ ሴት ሆነው በመስከረም ወር 2003 ዓ.ም ከፍተኛውን የፓርቲ ሥልጣን በባለቤታቸው በአቶ መለስ ዜናዊ ልዩ ድጋፍ ማግኘት የቻሉት ወ/ሮ አዜብ የሰሞኑን ሐዘናቸውን ለድጋፍ ማሰባሰቢያ እንደተጠቀሙበት ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡


ወ/ሮ አዜብ ለድጋፍ ማሰባሰቢያ ይጠቅሙኛል የሚሉዋቸው የህወሃት ሰዎች ለቅሶ ለመድረስ ቤተመንግስት በሚመጡበት ወቅት አንገታቸውን እያነቁ በማልቀስና በማስለቀስ፣የማይፈልጉዋቸውን ደግሞ ፊት ሲነሱ መቆየታቸው በተለይ በአመራር ላይ ባሉት የብአዴን ሰዎች ዘንድ አልተወደደላቸውም፡፡

ወ/ሮ አዜብ ባለቤታቸው አቶ መለስ በ8ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በጡረታ ያሰናበታቸው አቶ ሥዩም መስፍን፣አቶ አባይ ጸሐዬ፣አቶ አርከበ ዕቁባይ፣አቶ ተፈራ ዋልዋ፣አቶ አዲሱ ለገሰን “የመለስን ራዕይ ለማሳካት” በሚል ስትራቴጂ ከጎንዋ ለማሰለፍ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መሰንበታቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮዋ በአቶ መለስ ቀብር ፕሮግራም ላይ በወ/ሮ ነጻነት አስፋው የተዘጋጀላቸውን ኦፊሻል ንግግር በመተው የራሳቸውን ኃሳብ ያንጸባረቁበት ንግግራቸው “መለስ የጀመራቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እስካልተበከሉና እስካልተበረዙ ድረስ …” የሚለው ንግግራቸው በመለስ ስም ለጀመሩት የድጋፍ ማሰባሰብ ጥረታቸው ይረዳቸው ዘንድ ሆን ብለው ያደረጉት መሆኑን ምንጫችን  አስቀምጦአል፡፡

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ጉባኤያቸውን በማካሄድ ለሁለት ዓመታት የሚቆዩ አመራሮቻቸውን የሚመርጡ ሲሆን በመጪው መስከረም ወር ኢህአዴግ በአቶ መለስ ዜናዊ ምትክ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ሊቀመንበር አድርጎ ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡በተለይም በአቶ ኃይለማርያም ተይዞ የነበረው የምክትል ሊቀመንበርነት ቦታ ህወሃት ላለማጣት ከብአዴን ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባቱን፣በዚህ ፍጥጫ ውስጥም ወ/ሮ አዜብ አሸናፊ ሆነው ለመውጣት እየጣሩ ነው፡፡ህወሃት ወ/ሮ አዜብ መስፍንን በሊቀመንበርነት ከተቀበለ የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርነት ቦታ የማግኘታቸው ጉዳይ አጠራጣሪ እንደማይሆን ከወዲሁ መገመቱን ምንጫችን ጠቁሟል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የህወሃት ሥራ አስፈጻሚ በመሆን በማገልገል ላይ ካሉት ውስጥ አቶ መለስ በሞት ሲለዩ ብዙዎቹ ከኢህአዴግ የመተካካት ስትራቴጂ ጋር ተያይዞ በአዲስ የሚተኩ ናቸው፡፡አቶ አባይ ወልዱ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት፣ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣አቶ ጸጋዬ በርሄ (የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንትና በአሁኑ ወቅት የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ) ፣ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፣ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣አቶ በየነ ምክሩ፣አቶ አባዲ ዘሙ የህወሀት የስራ አስፈጻሚ አባላት መሆናቸው ይታወቃል።

በተያያዘ ዜና ከ12 ቀናት በፊት የአቶ መለስ ሞት እንደተሰማ የሚኒስትሮች ም/ቤት ተሰብስቦ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በተጠባባቂ ጠ/ሚኒስትርነት እንዲሰሩ ውሳኔ ያሳለፈ ቢሆንም የም/ቤቱ ውሳኔ ከህግ አግባብ ውጪ ነው የሚል ቅሬታ በኢህአዴግ አመራር ውስጥ በመፈጠሩ ለጥቂት ቀናት “ተጠባባቂ፣ጊዜያዊ” በመባል በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሲነገርላቸው የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ብቻ እንዲባሉ በተላለፈው ትዕዛዝ መሰረት ሚዲያዎቹ በዚሁ መሰረት እየሰሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

የአቶ ኃይለማርያም ሹመት ቅሬታ ያስነሳው ጠ/ሚኒስትር(ተጠባባቂን ጨምሮ) እንዲሾምለት ዕጩ የማቅረብ ሥልጣን የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ እንጂ የሚኒስትሮች ም/ቤት ሥልጣን አይደለም፡፡ኢህአዴግ ዕጩ ካቀረበ በኃላ በቀጥታ ለፓርላማ ቀርቦ ሌሎችም ዕጩዎች ካሉ ተጠቁመው ተወዳድሮ ከተመረጠ በኃላ ቃለመሃላ ፈጽሞ ወደሥራ መግባት አለበት የሚል ህግ ነክ ክርክር ቀርቦ በማሸነፉ መሆኑን ምንጫችን አስታውሶአል፡፡በዚህ ውሳኔ መሰረትም አቶ ኃይለማርያም ጠ/ሚኒስትሩ በሌሉ ወቅት ተክተው ይሰራሉ በሚለው የህገመንግስቱ ድንጋጌ መሰረት በቀድሞ ማዕረጋቸው እየሰሩ መሆኑ  ነው፡፡

በፓርላማ ሊያደርጉት ታስቦ የነበረውም ቃለመሃላ እንዲሰረዝ የተደረገው ከዚሁ ምክንያት ጋር ተያይዞ መሆኑም ታውቋል፡፡ከሳምንት በፊት ይህው ጉዳይ በመግለጫ ላይ የተነሳባቸው አቶ በረከት ስምኦን የፓርላማ አባላቱ ሐዘን ላይ በመሆናቸው መራዘሙን መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡ትናንት በተካሄደው  አቶ መለስ የቀብር ሥነ-ስርዓት ላይ የውጪ አገር መሪዎችና ተወካዮች በንግራቸው መግቢያ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን “ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር”እያሉ ቢጠሯቸውም የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ግን በተደጋጋሚ ፦”ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር” ሲላቸው መዋሉ ይታወሳል።

የኢቲቪ ጋዜጠኞች ከ ሥነ-ስርዓቱ  መጀመሪያ አንስቶ እስከመጨረሻው ድረስ የነበረውን ሁኔታ በቀጥታ ስርጭት እያስተላለፉ በሚነጋገሩበት ወቅት በተለያዩ ጊዚያት በትንሹ ወደ 20 ጊዜ የአቶ ሀይለማርያምን ስም የጠቀሱ ሲሆን፤ ከነዚህ አጋጣሚዎች  በአንድኛቸው እንኳ ሳት ብሏቸው ፦”ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር”ብለው አልጠሯቸውም።

በተለይ በመስቀል አደባባይ የነበረው ዝግጅት ተጠናቆ አስከሬኑ ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሚያመራበት ጊዜ የኢቲቪ ጋዜጠኞች አድርጉ ተብለው የታዘዙ እስኪመስል ድረስ በተደጋጋሚ ፦”ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ” እያሉ  በተከታታይ  ሲናገሩ ተደምጠዋል።የአቶ መለስ ቀብር በመጠናቀቁ፤ የአቶ ሀይለማርያም ሹመት መጽደቅ እና አለመጽደቁ በቀጣዮቹ ቀናት ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።

No comments:

Post a Comment