ኢሳት ዜና:-የነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሸበት በ30 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ አደረገ ኤጀንሲው
ትላንት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚጠቁመው ከ12 ወራቱ አጠቃላይ አገራዊ የዋጋ ግሸበት ውስጥ የምግብ ዋጋ ግሸበት
36 ነጥብ 5 በመቶ፣ምግብ ነክ ያልሆኑ 20 ነጥብ 9 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ ከምግብ ውስጥ ሥጋ በ57 በመቶ ጭማሪ
በማሳየት ከፍተኛውን ሪከርድ ይዟል፡፡
የ12 ወራቱ ተንከባላይ አማካይ የዋጋ ግሸበት ረዘም ያለ ጊዜ የዋጋ
ግሸበትን ሁኔታን ያሳያል ያለው ኤጀንሲው ወርሃዊ የዋጋ ግሸበት ምጣኔው የወቅቱን ሁኔታ የሚያሳይ መሆኑን
ጠቁሟል፡፡በዚሁ መሰረት የነሐሴ ወር 2004 አጠቃላይ የዋጋ ግሸበት ካለፈው ሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር
በ1 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አረጋግጧል፡፡
የነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም የአገር አቀፍ ጠቅላላ
የችርቻሮ ዋጋ ኢንዴክስ ከነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር በ20 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ አሳይቶአል፡፡ለዚህ
ጭማሪ ምክንያት የሆኑት ምግብ 20ነጥብ 4 በመቶ፣መጠጥ በ21 ነጥብ 4 በመቶ፣ልብስና መጫሚያ በ31 ነጥብ 8
በመቶ፣የቤት ኪራይ፣የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ውሃና ኢነርጂ በ14 ነጥብ 9 በመቶ፣የቤት ዕቃዎች ፣የቤት
ማስጌጫዎች፣የቤት ቁሳቁስና የቤት ሠራተኛ ደመወዝ በ26 ነጥብ 4 በመቶ፣ህክምና በ11 ነጥብ 1 በመቶ፣መዝናኛና
ትምህርት በ16 ነጥብ 8 በመቶ፣የግል ንጽህናና የግል ቋሚ ዕቃዎች በ22 ነጥብ 3 በመቶ እና ሌሎች ዕቃዎች በ21
ነጥብ 6 በመቶ በየኢንዴክሶቻቸው ጭማሪ አሳይተዋል፡፡
ኤጀንሲው አያይዞም ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጋር
ሲነጻጸር አብዛኛዎቹ የምግብ ክፍሎች ጭማሪ ማሳየታቸውን ጠቁሟል፡፡በዚሁ መሰረት እህል በ25 ነጥብ 4 በመቶ፣ጥራጥሬ
በ6 ነጥብ 7 በመቶ፣ዳቦና ሌሎች የተዘጋጁ ምግቦች በ21 ነጥብ 5 በመቶ፣ሥጋ በ56 ነጥብ 5 በመቶ ፣ወተት
አይብና ዕንቁላል በ30 ነጥብ 4 በመቶ፣አትክልትና ፍራፍሬ በ49 ነጥብ 2 በመቶ፣ድንችና ሌሎች ሥራስሮች በ44
ነጥብ 2 በመቶ፣ሌሎች ምግቦች በ16 ነጥብ 5 በመቶ፣የማስፈጫ አገልግሎት በ21 ነጥብ 6 በመቶ፣ከቤት ውጪ የተወሰዱ
ምግቦች በ29 ነጥብ 2 በመቶ እድገት አሳይተዋል፡፡ በሌላ በኩል ዘይትና ቅባቶች በ8 ነጥብ 4 በመቶ፣ቅመማቅመም በ18 ነጥብ 4 በመቶ፣ ያልተቆላ ቡናና ሻይ ቅጠል በ1 በመቶ ቅናሸ አሳይተዋል፡፡
የኤጀንሲው
መረጃ እንደሚጠቁመው የነሐሴ ወር 2004 የአገር አቀፍ ጠቅላላ የችርቻሮ ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ከነሐሴ 2003
ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር በ20 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ አሳይቶአል፡፡ለዚህ ጭማሪ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት ክልሎች
መካከል ትግራይ በ25 ነጥብ 4 በመቶ በመያዝ እየመራ ይገኛል፡፡በመቀጠል አማራ በ20 ነጥብ 1 በመቶ፣ኦሮሚያ በ20
በመቶ፣ አዲስ አበባ በ19 ነጥብ 7 በመቶ የሚከተሉ ሲሆን የተቀሩት ክልሎች ከ 19 እስከ 11 በመቶ ድርሻ
ይዘዋል፡፡
መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት የዋጋ ግሸበቱን ለመቆጣጠር በሚል ስንዴና ዘይት አምጥቶ በድጎማ
ከማከፋፈል ጀምሮ እንደጤፍ ያሉ ምርቶች ወደ ውጭ እንዳይላኩ፣በተወሰኑ ሸቀጦችም ላይ የዋጋ ተመን በማውጣት
የወሰዳቸውእርምጃዎች ቢኖሩም በዘላቂነት ግን ችግሩን መቅረፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ
ሚኒሰትር አቶ መለስ ዜናዊ የዋጋ ግሸበቱ እስከነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም ከሁለት አሃዝ ወደ አንድ አሃዝ እንደሚቀንስ
ወይም እንደሚረጋጋ በሚያዝያ ወር 2004 ዓ.ም ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር ቃል ቢገቡም በተግባር ግን ግሸበቱ
በመጨመሩ ህልማቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በየጊዜው እየናረ ከሚሄደው የዋጋ ግሸበት ጋር በተያያዘ አብዛኛው ደሃና መካከለኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል በወርሃዊ ገቢው መኖር ወደማይችልበት ደረጃ መድረሱ የሚታወቅ ነው፡፡
አቶ
መለስ ዜናዊ በህመም አልጋ በያዙበት ቀን እንዲሁም ዜና እረፍታቸው ከተሰማ በሁዋላ በታወጀው ረጅም የሀዘን ቀን
ወቅት ኢኮኖሚው እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ መመሪያ የሚሰጥ ባለስልጣን በመጥፋቱ ኢኮኖሚው አሁን ካለበት በበሳ
መላሸቁን የቅርብ ምንጮች ይናገራሉ። መሪ አልባው የኢህአዴግ አገዛዝ ፣ የውስጥ የስልጣን ሽኩቻውን አቁሞ
በአስቸኳይ ተስማምቶ መሪውን መምረጥ ካልቻለ፣ አሁን የሚታየው የዋጋ ግሽበት በአንድ ወቅት ዝምባብዌ ያጋጠማትን
አይነት ችግር ሊያጋጥማት እንደሚችል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
በመላ አገሪቱ የእህል ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ
መጨመሩ፣ አጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እያናጋው ነው። አቶ መለስ መታመማቸው እንደተሰማ የውጭ እና የአገር ውስጥ
ባለሀብቶች ሀብታቸውን ማሸሽ መጀመራቸው፣ ችግሩን እንዳባባሰው ባለሙያዎች ይናገራሉ። በያዝነው ወር ውስጥ ወደ አንድ አሀዝ ዝቅ ይላል ተብሎ የተነገረለት የዋጋ ግሽበት በተቃራኒው ወደ ሰማይ መውጣቱ ህዝቡን እጅግ ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል። መንግስት አቶ መለስ የጀመሩትን ልማት ለማስቀጠል በሚል አዲስ የገቢ ማሰባሰቢያ መጀመሩ የመንግስት ሰራተኛውን በእጅጉ እያበሳጨ ነው።
በኢትዮጵያ
ውስጥ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የውጭ አገር ለጋሽ መንግስታት በአቶ መለስ ዘመን ሲያደርጉት
እንደነበረው ገንዘባቸውን በቀላሉ ለመስጠት እንዳማይፈልጉ እየተነገረ ነው። አንዳንድ መንግስታት የስልጣን ሽግግሩ
በሰላም እስከሚጠናቀቅ ድረስ ገንዘባቸውን በመያዣነት ለመጠቀም መፈለጋቸውን ከዲፐሎማቲክ ማህበረሰቡ የተገኘው መረጃ
ያመለክታል። አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ግሽበቱን ለመረጋጊያ የሚሆን መጠነኛ ገንዘብ ከቻይና መንግስት በብድር ለማግኘት ችለዋል።
No comments:
Post a Comment