እንክብካቤ እየተደረገለት ያላደገ በጭቆናና በክፋት ያደገ በተዛባ አያያዝ ያደገ አእምሮ ለራሱ ለህብረተሰቡና ለአገርም ጐጂ እንደሚሆን ተገለፀ፡፡ ይህን የገለፁት ታዋቂው የህክምና ባለሞያ ዶ/ር መስፍን አርአያ ናቸው፡፡ ዶ/ር መስፍን ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያት ማህበር ከፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ጋር በመተባበር “ትውልዱን ከሱስ እናድን” በሚል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጽሐፍት ኤጀንሲ ባዘጋጀው ኪነጥበባዊ ምሽት ላይ ነው፡፡
በክብር ተናጋሪነት የተጋበዙት ዶ/ር መስፍ አርአያ በዕለቱ ለታደሙት ወጣትና አንጋፋ የሴት ደራሲያት እንዲሁም ለተጋበዙ እንግዶችና ጋዜጠኞች አስተምረዋል፡፡ ዶ/ር መስፍን “ሰውን ሰው ያደረገው ሥራና አውራጣቱ ነው ሲባል እሰማ ነበር በእኔ እምነት ግን ሰውን ሰው ያደረገው አእምሮ ነው፡፡” በማለት የመግቢያ ንግግራቸውን የጀመሩት ዶ/ር መስፍን አእምሮ እንክብካቤና ጥበቃ እየተደረገለት ማደግ እንደሚገባው አስምረውበታል፡፡ ዶ/ሩ እንዳሉት “በጭቆናና በክፋት ያደገ አእምሮ በተዛባ አያያዝ ያደገ አእምሮ ጤናማ ሆኖ ለራሱም ለህብረተሰቡም ሆነ ለአገር አይጠቅምም፡፡
ስለዚህ የአካላችን ንጉስ የሆነውን አእምሮ እንጠብቀው” ብለዋል፡፡ ዶ/ር መስፍን በማያያዝም “18 ዓመት ያልሞላቸው ህፃናት አልኮል እንዲጠጡ አይመከርም፡፡ አልኮል ብቻ ሳይሆን እንክብካቤና ጥበቃ ያልተደረገለት አእምሮ በመጨረሻ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ ነው፡፡” ብለውታል፡፡ በመጨረሻም ዶ/ር መስፍን “በርካታ ውድ ሰዎች አእምሮአቸውን መንከባከብ አቅቷቸው በእኔ መ/ ቤት በኩል አልፈዋል፡፡ ሐሳባቸውን ማውጣት እየፈለጉ ማውጣት ባለመቻላቸው በየሥርዓቱ በሚደርስባቸው ተጽኖ መቋቋም እያቃታቸው አእምሮአቸው ተበላሽቷል፡፡ ለሱሰኝነትና ለከፋ ድርጊት ተዳርገዋል፡፡ ስለዚህ አእምሮአችንን እንንከባከበው፡፡” በማለት እውቀታቸውንና የሞያ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡
በወቅቱ ባለመጀመሩና በአንድ ዕለት በርካታ ተመሳሳይና ተደራራቢ ፕሮግራም በመያዝ ታዳሚው መሰላቸት እየተሰማው ፕሮግራሙን እያቋረጡ ለመሄድ ቢገደድም በዚህ “ትውልዱን ከሱስ እንታደገው” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የኪነ ጥበብ ምሽት በርካታ ታዋቂና ወጣት የሴት ደራሲያን ዝግጅታቸውን ያቀረቡበት መነባንቦች የተደመጡበት ዝግጅት ነበር፡፡ በሱሰኝነት ለጐዳና ተዳርገው የነበሩ ሁለት ወጣቶች ሰዎች ባደረጉላቸው እርዳታ ከሱሰኝነት ወጥተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዴት ማስተዳደር እንደቻሉ ልምዳቸውን ለታዳሚው አካፍለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያት ማህበርና ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ፕሮግራም እንዳዘጋጁ ይታወቃል፡፡
Source: Finote Netsanet
No comments:
Post a Comment