Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, July 11, 2012

የፍትህ ዋና አዘጋጅ ደህንነት አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል

ኢሳት ዜና:- ሐምሌ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
በሳምንታዊው ፍትህ የአማርኛ ጋዜጣና በዋና አዘጋጁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የግል እንቅስቃሴ ላይ የደህንነት ኃይሎች የሁለት ቀናት የሃያ አራት ሰዓታት ግልጽ ክትትል ማድረጋቸውን ለጋዜጠኛው ቅርበት ያላቸው ምንጮች አስታወቁ፡፡ በጋዜጣው የኢሜል አድራሻም ከአልሸባብ ለዋና አዘጋጁ የተላከ የሚያስመስል ቁጥር 2 የፈጠራ ደብዳቤ ከሰሞኑ ተልኳል፡፡

ቅዳሜ ሰኔ 30 ቀን እና እሁድ ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም ጋዜጠኛ ተመስጌን ራሳቸውን በግልጽ ባቀረቡ የደህንነት ሰዎች ሙሉ ክትትል ሥር የዋለ ሲሆን ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት ዙሪያ፣ በመመገቢያ ሥፍራው፣ በቢሮው አቅራቢያ፣ በቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት ዙሪያ እና በሚንቀሳቀስበት ሁሉ እየተፈራረቁ  በመከታተል አእምሮው እረፍት እንዲያጣና እንዲጨናነቅ ጫና ለመፍጠር ሞከራውል በማለት ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡

መንግሥታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣም በፍትህ ጋዜጣ እና በጋዜጣው ዓምደኞች ላይ የመወንጀያ፣ የማስፈራሪያ እና የማሸማቀቂያ ጽሑፎችን ማስነበቡን ቀጥሏል፡፡ቅዳሜ ከጠዋቱ 3፡30 ሰዓት ላይ ጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝ ከመኖሪያ ቤቱ ሲወጣ የክትትል ቀለበት  ውስጥ የከተቱት ወጣት የደህንነት ኃይሎች ሙሉ ቀኑን እንደሚከታተሉት እንዲያውቅ በማድረግ ሲከታተሉት የዋሉ ሲሆን አመሻሽ ላይ ወደ ቤቱ የሚሄድ በመምሰል በአቅራቢያው በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ቤርጎ ይዞ ለማደር ተገዷል።

ጠዋት ሲወጣ ግን ከአደረበት ሆቴል በር ፊት ለፊት ጠብቀው ልክ ከወራት በፊት የፍትህ ባልደረቦችን ሲያስጨንቁበት ወደ ነበረው ግልጽ የክትትል መረብ ሥር ከተውታል ብለውናል፡፡ወደ ጋዜጣው የኢሜል አድራሻ የተላከው የፈጠራ መወንጀያ ከአልሸባብ ለዋና አዘጋጁ የተላከ የሚያስመስል ቁጥር 2 የፈጠራ ደብዳቤ ሲሆን የመልዕክቱ አዝማሚያ በኢህአዴግ መንግሥት አሸባሪው ተብለው የተፈረጁት አልሽባብ፣ ግንቦት 7 ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የኤርትራውን መንግሥት የሚመራው ሻቢያ በጋራ እንደሚሰሩ እና የፕሮፓጋንዳ ሥራቸውንም በፍትህ ጋዜጣ በክፍያ እንደሚስተናገዱ በማስመሰል የቀረበ ነው ያሉን ምንጫችን የላኪው ሥም ኮሎኔል ተወልደ ሃብቴ ነጋሽ  የሚል ነው ብለዋል፡፡

ይህ ደብዳቤ ከቀድሞው የሚለየው ላኪው የሰሜን ኢትዮጵያና የኤርትራ ሰው ሥም የያዘ እና ከግንቦት 7 እና ከሻቢያ ጋር አያይዞ ፍትህ ጋዜጣን እና ዋና አዘጋጁን ለመወንጀል የተዘጋጀ ወጥመድ ነው ያሉን የፍትህ ምንጮች፣  ቋንቋውም ከቀድሞው የተሻለ እና የቀድሞዎቹን የአመክንዮ መጣረሶች ለማስተካከል የሞከረ ነው ብለዋል።

ኢህአዴግ የኢሳት ጋዜጠኞችን አሸባሪ ብሎ ስለከሰሰ ዋና አዘጋጁ ቀደም ሲል ከኢሳት ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ሁሉ እንደመወንጀያ ሊጠቀሙበት ያሰቡ ይመስላሉ ብለዋል፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “የመለስ አምልኮ” መጽሐፍ ሦስተኛ ህትመት በመጠናቀቁ አራተኛው ህትመት በመታተም ላይ መሆኑን አሳታሚው ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

ይህን መጽሐፍ ሲያትም የነበረው የግል ማተሚያ ቤት በመንግሥት የደህንነት ኃይሎችና በፌዴራል ፖሊስ ማስጨነቅና ውክቢያ የደረሰበት ሲሆን ለማተሚያ ቤቱ ባለቤትም መንግሥት አካባቢውን ለልማት ስለሚፈልገው ማተሚያ ቤቱ በቅርቡ ሊፈርስ እንደሚችል በመግለጽ አስፈራርተዋቸዋል።  ይህን መጽሐፍና መሰል ሥረታዎችን እንዳያትሙም እንደነገሯቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡በዚህ የተነሳም የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የመለስ አምልኮ መጽሐፍ አራተኛ ህትመት በሌላ የግል ማተሚያ ቤት በመታተም ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Source: Ethsat news

No comments:

Post a Comment