Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Monday, July 9, 2012

የአቶ መለስ ዜናዊ የጤና ሁኔታ አሁንም ሚስጢር እንደሆነ ነው

ኢሳት ዜና:- ሐምሌ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
የፓርላማ አባላት ግራ ተጋብተዋል፣ የተለያዩ ዝግጅቶች ተሰርዘዋል ፣ አንዳንድ መረጃዎች አቶ መለስ የወራት እድሜ እንዳላቸው ይጠቁማሉ ዝርዝሩ ኢሳት የፓርላማው መዝጊያ በአንድ ሳምንት እንደሚራዘም፣ ምክንያቱ ደግሞ የአቶ መለስ ዜናዊ የጤና ችግር እንደሆነ ከዘገበ በሁዋላ ፣ የአቶ መለስ የጤና ሁኔታ የመላው ኢትዮጵያውያን የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል። 

በኢህአዴግ ዙሪያ የተሰባሰቡ አባላት ሳይቀሩ ግራ ተጋብተዋል። አቶ መለስ ዜናዊ በተገኙበት በፈጠራና ምርምር የላቀ ውጤት ላስገኙ ስድስት ኢትዮጵያዊያን በጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ሰሞኑን ሊሰጥ የታሰበው ሸልማት ለሁለተኛ ጊዜ  ተላልፏል፡፡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰኔ 21 ቀን 2004  ዓ.ም ሊሰጥ ታሰቦ የነበረው ሸልማት በሥራ መደራረብ ምክንያት ለሰኔ 28 ቀን 2004 ዓ.ም መተላለፉን በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጭምር ይፋ ከተደረገ በኃላ እንደገና  ምክንያት ባልተገለጠበት ሁኔታ ዝግጅቱ እንዲቀር ተደርጓል፡፡


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ባለፈው ሳምንት የሚከተለውን ዘግቦ ነበር “ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰኔ 28 ቀን 2004ዓ.ም ስድስት የፈጠራና የምርምር ስራዎችን ላበረከቱ ኢትዮጵያውያን ሽልማት እንደሚሰጡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሰኔ 21 ቀን 2004ዓ.ም ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የሽልማት ስነ-ስርዓት በፕሮግራም መጣበብ ምክንያት ወደ ሰኔ 28 መሸጋሸጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ሌሎቹ በማምረቻና አገልግሎት ዘርፍ ተሸላሚ የሚሆኑት ሶስት የፈጠራ ግኝቶች ሲሆኑ የጃትሮፋን ተክል በመጠቀም ባዮዲዝልና ናፍታ ማምረት የሚችል መሳሪያ፣በአንድ ጊዜ 100 ቀሰሞችን ማጠንጠን የሚችል የክር ማሽን እና የእሸት ቡና ማጠቢያ ማሽን የፈጠራ ባለቤቶች ናቸው። 

በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሙስጠፋ አብዱልሰመድ እንደገለጹት ስድስቱ የምርምርና የፈጠራ ባለቤቶች ሰኔ 28 ቀን 2004 ዓ.ም በጠቅላይ ሚነስቴር ጽህፈት ቤት የሰብሰባ አዳራሽ በሚከናወነው የሽልማት ስነ -ስርዓት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።”

ሰኔ 28 ምንም አይነት የሽልማት መስጠት ስነስርአት ያልተካሄደ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩም ስነስርአቱ ለምን እንዳልተካሄደ ይፋዊ መግለጫ ከመስጠት ተቆጥቧል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰኔ 30 ቀን እንደሚዘጋ በሕገመንግስት ጭምር የተደነገገው የኢትዮጽያ ፓርላማ አሁንም በመዝጊያው ሥነሥርዓት ላይ መገኘት የሚገባቸው አቶ መለስ እንደማይገኙ በመታወቁ የሚዘጋበት ጊዜ ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል፡፡ አንዳንድ ምንጮች የፓርላማው መዝጊያ እንደገና ለተጨማሪ አንድ ሳምንት ይተላለፋል ቢሉም ሌሎች ወገኖች ግን መዝጊያው ያለ አቶ መለስ ሊካሄድ ይችላል ይላሉ።

በሕገመንግስቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት “ የም/ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ 30 ነው፡፡በመካከሉ ም/ቤቱ በሚወስነው ጊዜ የአንድ ወር ዕረፍት ይኖረዋል” ይላል፡፡ ስለ ህግ መንግስት ተናግሮ የማይጠግበው የመለስ መንግስት ፣ አንዳች ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር ፣ ህገመንግስቱን ጥሶ የፓርላማ መዝጊያውን ጊዜ ላልተወሰነ ጊዜ የሚያራዝምበት ምክንያት አይኖርም ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች።

ጉዳዩን ለማወቅ የአዲስ አበባው ወኪላችን የተለያዩ የፓርላማ አባላትን ለማነጋር ጥረት ቢያደርግም ” አናውቅም” የሚል መልስ ከማግኘት በስተቀር ተጨባጭ የሆነ መረጃ ለማግኘት ሳይችል ቀርቷል። ዘጋቢያችን እንደሚለው በፓርላማ አባላቱ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ግራ መጋባት ይታያል። የፓርላማ አባላቱ ችግሩ ከአቶ መለስ ጤና ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን እንደገለጡለት ዘጋቢያችን ጠቁሟል።

ደቡብ ሱዳን ዛሬ ነጻ የወጣችበትን አንደኛ አመቱዋን ስታከብር የኢትዮጵያ፣ የኬንያና እና የዩጋንዳ መሪዎች እንደተገኙ ቢቢሲና አልጀዚራ ቢናገሩም፣ በኢትዮጵያ በኩል የተገኘውን ሰው በስም አልጠቀሱም። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት ድረገጽም፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ወደ ደቡብ ሱዳን ማምራቱን ከመግለጥ ውጭ ዘወትር እንደሚያደርገው የልኡካኑን መሪ አልገለጠም።

በዝግጅቱ ላይ የዩጋንዳው መሪ ንግግር ሲያደርጉ ኢትዮጵያን በመወከል ንግግር እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት አቶ መለስ ስቱዲዮ እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ንግግር አላደረጉም። አቶ መለስ ዜናዊ መታመማቸው እርግጥ ቢሆንም የህመማቸው አይነት ግን እስካሁን በግልጥ አልታወቀም። አንዳንድ ወገኖች ህመማቸው የደም ካንሰር ነው ሲሉ ሌሎች ወገኖች ደግሞ የእአምሮ ካንሰር ነው ይላሉ። የህወሀት ደጋፊዎች በበኩላቸው አቶ መለስ የታመሙት በምግብ መመረዝ ነው በማለት እያስወሩ ነው።

 ያልተረጋገጡ ምንጮች እንደሚናገሩት አቶ መለስ በህይወት የሚቆዩበት ጊዜ በግልጽ ተነግሮአቸዋል። ይሁን እንጅ ኢሳት በራሱ መንገድ ለማጣራት አደረገው ሙከራ አልተሳካም። ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው እለት ስካይፕን ጨምሮ ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ታፍነው እንደነበር ዘጋቢያችን ገልጧል። የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን ተከትሎ ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም፣ በዛሬው እለት ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ጥበቃ ሲካሄድ ውሎአል።

No comments:

Post a Comment