Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Monday, May 28, 2012

የመድረክ አመራሮች የአበበ ገላውን ተቃውሞ ደገፉ

ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የቡድን ስምንት አገራት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ከአፍሪካ ከተጋበዙ አራት መሪዎች አንዱ የነበሩት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፤ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በሚለው አጀንዳ ዙሪያ የአገራቸውን ተመክሮ ለታዳሚው ከማጋራት ውጭ ሌላ ነገር ይገጥመኛል ብለው አላሰቡም ነበር፡፡

 አገር አማን ብለው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ የነበሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በ “ኢሳት” ተባባሪ መስራችና ጋዜጠኛ አበበ ገላው ተቃውሞ ነበር ከማብራሪያቸው የተናጠቡት፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች የስብሰባው ታዳሚዎች ያልጠበቁት ዱብዕዳ ቢሆንም ለጋዜጠኛው ግን ድንገተኛ አይመስልም – ተቃውሞው፡፡ ተቃውሞውን የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ በኢራቅ ንግግር ሲያደርጉ በአንድ ኢራቃዊ ጋዜጠኛ ከተወረወረባቸው ጫማ ጋር ይመሳሰላል፡፡ 

ድንገተኛው ተቃውሞ ከተሰማ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በሰጡት አስተያየት ተቃውሞው ትክክል አይደለም ብለዋል – “ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የጎደለው ተግባር ነው ፤ የአገሪቱን ብሎም የአፍሪካን ጥቅም ይነካል” በሚል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገር ውስጥ በትክክለኛ መንገድ መቃወም ስለማይቻል ጋዜጠኛው ያደረገው ትክክል ነው የሚሉም አልጠፉም፡፡ ይሄን ሃሳብ ከሚጋሩት መካከል የመድረክ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ አንዱ ሲሆኑ ጋዜጠኛው ያነሳቸው ሃሳቦች እኛም በየጊዜው መግለጫ የምንሰጥባቸው ናቸው ብለዋል፡፡ 

ፕ/ር በየነ ተቃውሞውን ለምን ተገቢ ነው እንዳሉ እንዲያስረዱን ጠይቀናቸው እንዲህ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡አንድ ህዝብ ሃሳቡን ለመግለጽ ክልከላ ተደርጐበት ሲታፈን የዚህ ዓይነት ነገሮች አምልጠው መውጣታቸው አይቀርም፡፡ ሰው ሲከፋና ህጋዊ የሆነውን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሲነፈግ”፤ ከዚህም አልፎ ሄዶ ተስፋ በቆረጠ እርምጃ ውስጥ ይገባል፡፡ የተተቹት ወገኖች ለምን እንደደነቃቸው አላውቅም፡፡የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ላይ ጫማ አልተወረወረም? ያም እኮ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ህዝባዊ መድረክ ላይ ያሉ የፓርቲ መሪዎች የዚህ አይነት ነገር እንደሚያጋጥማቸው አውቀው ነው መንቀሳቀስ ያለባቸው፡፡ እስከዛሬ ካየናቸው ክስተቶች የተለየ ነው ብዬ አላምንም፡፡

 ከተቃውሞው ጋር ተያይዞ የሚነሳውን “ኢትዮጵያዊ ጨዋነት” የሚል ነገር ያለቦ መደንጐርአያስፈልግም፡ መንጎድር፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ የዜና ሰው በተሰማራበት ዘርፍ መደመጥን ይፈልጋል፡፡ ያ ደግሞ ሰብዓዊ፣ አለማቀፋዊ መብት ነው፡፡ ይሄንን ተነፍጐ፤ ከዚህ በፊት የሚያደርጋቸው ነገሮች እየተንቋሸሹና እየተወነጀሉ ያለ ሰው፤ የዚህ ዓይነት አጋጣሚ አግኝቶ ድምጽን ማሰማት ቢፈልግ የማይጠበቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የሚለውን ነገር በተመለከተ፤ ሁሉም እኮ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን አክብሮ መገኘት አለበት፡፡ የአገሪቱም ገዢዎች እኮ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን አክብረው፤ የዜጐቻቸውን ሃሳብ ማዳመጥ አለባቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት እድልና መድረክ በተነፈገበት አገር ላይ ነው የምንኖረው፡፡ 

ጋዜጠኛው እንደልቡ ጥያቄ እንዲጠይቅ ጠ/ሚኒስትሩ ለምን እዛው እያሉ ለጋዜጠኞች ፕሬስ ኮንፈረንስ አይሰጡም ነበር? ይሄ እድል ቢኖር ጋዜጠኛው ጥያቄውን በአግባቡ ማቅረብ ይችል ነበር፡፡ ያ እድል ስላልተፈጠረለት፤ ያውም ተፈቅዶለት ሳይሆን ድምፁን ከፍ አድርጐ ሲናገር ነው ፖሊስ ይዞ ያስወጣው፡፡ጠ/ሚ መለስ አፍሪካንና አገርን ወክለው ሲሰጡት የነበረውን ሃሳብ በማቋረጥ ተቃውሞውን ማሰማቱ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን የአገርንና የአህጉሪቱዋን ገፅታ የሚያበላሽ ነው ሲሉ የሚቃወሙ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

አይ የጠ/ሚኒስትሩ ሃሳብማ አይቋረጥም፡፡ ቢቋረጥም ይቀጥላል፡፡ በተፈቀደላቸው ጊዜ ሀሳባቸውን አቅርበው እንደሚጠናቀቅ ነው የሚገባኝ፡፡ አሳፋሪው ነገር “ለካስ የማይታወቅባቸው ህዝቡ ብሶት የሚያሰማባቸው ሰው ናቸው!” የሚለው ነው፡፡ በተረፈ የሳቸው መልእክት በጋዜጠኛው ተቃውሞ ተቋርጦ አልቀረም፤ ተላልፉዋል፡፡ ነገር ግን ለመከበር ሌላውንም አክብሮ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ ለምንድነው ጠ/ሚኒስትሩና ባለስልጣኖቻቸው የኢትዮጵያውያኑን ብሶት የማያዳምጡት? ለምንድነው በደሉን ሲያሰማ የሚያንቋሽሹት? ከዚህ ጥያቄ ነው መነሳት ያለብን፡፡ ይሄ ጨዋነት የሚባለው እየየም እኮ ሲዳላ ነው፡፡

 ይሄ ሰው እኮ ሊደመጥ፤ ሊሰማ ያልቻለ ሰው ነው፡፡ ጨዋ ለመሆንም እኮ መድረክ አልተሰጠውም፤ የሞት ሞቱን እኮ ነው ተቃውሞውን የገለፀው ፤ ያውም ፖሊስ ይዞ እስኪያስወጣው ድረስ፡፡ ከተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች እንደተሰማው ጋዜጠኛው በተቃውሞው ያነሳቸው ጉዳዮች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣አምባገነናዊ መንግስት ስለመኖሩ፣ ያለነፃነት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አይቻልም የሚሉና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በእስር ላይ ያሉ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን የተመለከተ ነበር፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

ጋዜጠኛው ያነሳቸው ገዳዮች በአጠቃላይ እኛ የምንላቸው” በየጊዜው መግለጫ የምናወጣባቸው ሃሳቦች ናቸው፡፡ የታሰሩትንም ፍ/ቤት ድረስ ሄደን ለመከላከል እየታገልን ያለንበት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ እሱ ያነሳው ጉዳይ የስም ማጥፋት፣ የውሸት ነገር የለውም፡፡ ሁላችንም የምናነሳው ጉዳይ ነው፡፡ ያነሳበቱ አግባብ (መድረኩ) የሚነሳበት ነው ወይ ሲባል— እንግዲህ ተስፋ የቆረጠ ሰው ምን ያድርግ? የት ያሰማ፣ የት ይደመጥ? በዚያ ላይ ደግሞ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከልማት ጋር ግንኙነት የላቸውም እየተባለ ነው፡፡ 

በተለይ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት (መብቶችን መፍቀድ) ከልማትና ከአገር እድገት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም በማለት ፐብሊክ ወርልድ ፎረም ላይ ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ዲሞክራሲያዊ መብት ፈቅደው ሰው በነፃነት ሃሳቡን እንዲገልጽ ማድረግ ነበረባቸው፡፡የኢህአዴግ ስርዓት በራሱ እኮ አምባገነን ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የአምባገነኑ ስርዓት መሪ ናቸው፡፡ በአንድ ብቸኛ ፓርቲ አውራ አመራር “ 30 እና ከዛም በላይ ዓመት ገዝተን አገሪቱን ወደ ልማት እናሸጋግራለን ብለው በጽሑፍ ማስፈራቸው ይታወቃል፡፡ አምባገነንነቱን በራሳቸው ቃል እኮ ነው ያስቀመጡት፡፡

ስለ ኢትዮጵያ ጨዋነትም ሆነ ሌላ ነገር ሲወራ ከሁሉም አቅጣጫ ነው መታየት ያለበት፡፡ አመራሩ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ተላብሶ የህዝቡን መብት አክብሮ ነው እያስተዳደረ ያለው? ህዝቡንና ወገኑን አሸባሪዎች (ቴሬሪስት) እያለ የሚያንቋሽሽ ስርዓት እንዴት ብሎ አክብሮት ያገኛል? በዚህ ህብረተሰብ ውስጥ መከባበርን መጀመር ፤ የህዝብን ሀሳብም አስተሳሰብም ማድመጥ መጀመር ይኖርበታል፡፡ ከዚያም በመነሳት መተማመን መጀመር አለበት፡፡ ጠ/ሚ የሚመሩት መንግስታቸው ደግሞ ይሄንን ጉዳይ ተቀብሎ የሚንቀሳቀስ አይደለም፡፡ ራሳቸውም በሚናገሩበት ጊዜ የምናየው ነው ፤ ዜጐችን የሚያከብር አይደለም፡፡ 

ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ኢትዮጵያውያን ተስፋ የቆረጠ ትግል ውስጥ እንዲገቡ ስርዓታቸው እየገፋቸው መሆኑን ቢያውቁትና ሊያርሙት ቢገባ መልካም ነው፡፡ አቶ አስራት ጣሴ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ ዋና ፀሃፊ ናቸው፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት ”አንድ ጋዜጠኛ ይቅርና ማንም ዜጋ ባገኘው መድረክና ባገኘበት ፎረም ላይ ጥቃት ሳያደርስ በጥሩ ቋንቋ ቅዋሜውን ማንሳት በአገርም በኢትዮጵያዊነት ጨዋነት ላይም አቶ አበበ ያደረገው መጥፎ ነው የሚል አስተያየት የለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ፍትህና መልካም አስተዳደር ሊሰፍንባት ያልቻለች አገር ናት፡፡ አብዛኛው ህዝብ በድህነት እየማቀቀ ጥቂቶች የሚበለፅጉበት አገር ሆናለች፡፡ 

የሰበዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ እየተጣሰ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ትቀጥላለች ወይ? እንደ አገር አለች ወይ? የሚለው ነው የሚያሰጋኝ፡፡ የጋራ ችግር፣ የጋራ ረሃብ የፍትህ እጦት አለብን፡፡ ጋዜጦች በራሳቸው ያለባቸውን አደጋ እናውቃለን፡፡ የአሜሪካ ሬድዮና የጀርመን ሬድዮ ጃም በሚደረግባት አገር እየኖርን በተገኘው አለማቀፍ ፎረም ኢትዮጵያ ያለችበትን ችግር መግለፅና መናገር እንደዚ ዓይነት ድፍረትና ትግል የሚጠበቅ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች አለመብዛታቸው ነው የሚያሳዝነኝ፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ስርዓት ባለበት አገር በተገኘው ፎረም መቃወም ተገቢ ነው፤ ግዴታም ነው ብየ ነው የማስበው፡፡“ ብለዋል፡፡

(ምንጭ አዲስ አድማስ)

No comments:

Post a Comment