Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Thursday, May 31, 2012

10ሩ የድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራዎች

ነብዩ ኃይሉ
አቶ መለስና ጓደኞቻቸው አምባገነን ስርአትን ለመቀየር ነፍጥ አንስተው፣ በጭቆና ላለመኖር ሲሉ በህይወታቸው ተወራርደዋል፤ አላማቸውን ለማሳካት ገድለዋል ሞተዋል፡፡ ድል ቀንቷቸው የዛሬ 21 አመት አምባገነኑን የደርግ ስርአት አስወግደው ምኒሊክ ቤተመንግስት ሲገቡ ኢትዮጵያን በለውጥ ጎዳና ሊመሩ፣ ዴሞክራሲን በማስፈን በሀገሪቱ አዲስ ታሪክ እንዲያኖሩ የሚያስችል ዕድል ነበራቸው ፡፡ አምባገነኑን የኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ደርግ ካስወገዱ በኋላ ግን አምባገነኑን የአቶ መለስ ዜናዊን ስርአት ከማስቀመጥ ባለፈ በግንቦት 20 ድል ታሪክ ሊሰሩ አልቻሉም፡፡ 

ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለበት፣ በተለያዩ ጎራዎች የተሰለፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ዶጋ አመድ አድርጎ ግንቦት 20, 1983 ዓ.ም የተቋጨው ጦርነት አንድን ወታደራዊ አምባገነን መሪ በኃይል በማስወገድ የይምሰል ዴሞክራሲያዊ ስርአትን(pseudo democracy) የገነባ ሲቪል አምባገነን መተካት የተወሰነ ቡድንን ወይም ግለሰቦችን ፖለቲካዊ የበላይነት(hegemony) ለማረጋገጥ ያለመ እንዳልነበር በትጥቅ ትግሉ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦች ያረጋግጣሉ፡፡ የህወሓት ነባር ታጋይና የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገብሩ አስራት ሰኔ 19,2002 ለወጣችው አዲስ ፕሬስ ጋዜጣ አሞራው ስለተባለ የህወሓት ጀግና ታጋይ ሲያስረዱ ‹‹አሞራው ቀና ብሎ እየተደረገና እየሆነ ያለውን ነገር ቢያይ ይገርመው ነበር›› ካሉ በኋላ የአቶ መለስ መንግስት በአሞራውና በሌሎች ታጋይ ሰማእታት መስዋዕትነት ስልጣን እየነገደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡  

ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን የያዘበት ተመሳሳይ ወቅት አምባገነናዊ ኮሚኒስት ስርአቶችን በማስወገድ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ የጀመሩት የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ለውጥ ማምጣታቸውን Carleton UniversityInstitute of European and Russian Studies  አጥኚ የሆኑት ድራጎስ ፖፓ (DRAGOS POPA) ሮሜኒያንና ቡልጋሪያን ነቅሰው ያመላክታሉ፡፡ የባልካን ሀገራትም ሁለት አስርት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ እምርታ ማምጣታቸውን  The democratic transformation of the Balkans በሚል ርዕስ የቀረበው የሮዛ ባልፈር እና ኮሪና ስትራቱላት (Rosa Balfour and Corina Stratulat) ጥናት ያመላክታል፡፡

ጥናቱ የባልካን ሀገራት በአጭር ጊዜያት ውስጥ ሶስት መሰረታዊ ለውጦችን ማስመዝገባቸውን ያስረዳል‹‹ከጦርነት ወደ ሰላም፣ ከኮሚኒዝም የእዝ ኢኮኖሚ ወደ ነፃ ገበያ እንዲሁም ከአንድ ፓርቲ አገዛዝ ወደ መድብለ ዴሞክራሲ ተለውጠዋል›› ይላል፡፡ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ባለፉት 21 አመታት የታየውና አሁንም ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለግንቦት 20 ድል የወጣውን  የህይወት ግብር እና በድሉ ማግስት የተገኘውን የግንቦት 20 ፍሬ ስናወራርድ ውጤቱ ኪሳራን የሚያመላክት ነው፡፡ይህ ጽሁፍ በህወሓት በስተመጨረሻም በህወሓት/ኢህአዴግ መሪነት ለ17 አመታት በተደረገው ፅኑ ትግል የተገኘው የግንቦት 20 ድል ሊያመጣ ያልቻላቸውን አስር አንኳር ነጥቦች ይፈትሻል፡፡   

ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባት ያለመቻሉ
ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ በሂደት ውጤት የሚያስገኝ ጥረት ነው፡፡ ጤናማ ሂደት እስከኖረ ድረስም የግንባታው እድገት አይቀሬ ውጤት ነው፡፡ ዛሬ በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታቸው ምሳሌ የሚሆኑት ሀገራት በቅፅበታዊ ለውጥ/ክስተት ካሉበት ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ከ1983 ግንቦት 20 ወዲህ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደት ውስጥ መግባቷን የአቶ መለስ መንግስት ሲናገር ይደመጣል፡፡

ሆኖም ሂደቱ አንዴ ወደ ፊት ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደኋላ ሲንሸራተት ቆይቶ በአሁኑ ጊዜ ተኮላሽቷል፡፡ ምርጫ ቦርድም ሆነ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ወይም የእንባ ጠባቂ ተቋም በኢህአዴግ ‹‹ሞተር›› የሚንቀሳቀሱ፣ በመንግስት ሳምባ የሚተነፍሱ በህዝብ አመኔታ የሌላቸው የስም ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ናቸው፡፡ የአቶ መለስ መንግስት በ21 አመት የስልጣን ዘመኑ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባት አለመድፈሩ/አለመፈለጉ የድህረ ግንቦት 20 ኪሳራ ማሳያነው፡፡  
ከተፅዕኖ ነፃ የሆኑ የፍትህ አካላትን መገንባት አለመቻሉ
በኢትዮጵያ ለህግ የሚሰጠው ቦታ ከፍ ያለ ነው፡፡ ህግን የማክበር እና ለፍትህ አካላት አመቴታና ክብር የሚሰጥ ባህላዊ መሠረትም አለ፡፡ ይህ ባህላዊና ሞራላዊ መሠረት በተለይ ከደርግ መንግስት ስልጣን መያዝ በኋላ የመሸርሸር ምልክት ማሳየት ጀመረ፡፡ “የደርግ ሹማምንት በፍትህ አካላት ላይ የተለያዩ ጫናዎችን በማሳደር ፍርድን ለማጣመም ጥረት ያደርጉ ነበር” የሚሉት አቶ አለማየሁ አዱኛ በህግ አማካሪና ጠበቃነት ይሰራሉ፡፡ አቶ አለማየሁ እንደሚሉት ከመንግስት አካላት ጫና ቢኖርም የፍትህ አካላቱ ከነበራቸው ጠንካራ መሠረት አንፃር ነፃነታቸውን ያስደፈሩ አልነበሩም፡፡

ይህ ሁኔታ የደርግ ባለስልጣናት ለሚወስዷቸው እርምጃዎች ህጋዊ ከለላ ከመስጠት ይልቅ ግልጽ ፖለቲካዊ እርምጃ ይወስዱ ነበር፡፡ የደርግ አምባገነንነትና ጨፍጫፊነት አጠያያቂ ባይሆንም እነዚህ ህገወጥ እርምጃዎች የሚወስዱት በማናለብኝነት በተወጠሩ ባለስልጣናት “የጐበዝ አለቆች” እንጂ በፍትህ አካላት አልነበረም፡፡ ህወሓት /ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ግን ሁሉንም ተቋማት በአንድ የፖለቲካ አስተሳሰብ የማጥመድ አባዜ የፍትህ አካላትንም አልተወም፡፡ ፖሊስ፣ አቃቤ ህግ እና ፍርድ ቤቶች ከመጋረጃ ጀርባ በኢህአዴግ ባለስልጣናት የሚሰጡ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን “በህግ” ስም ያስተላልፋሉ፡፡ ኢህአዴግ እራሱ ያፀደቀውን ህገ መንግስት በመጣሱ የፍትህ አካላትን ነፃነት ከመጋፋት ባለፈም፣ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ የሚያደርሱ አፋኝና ኢፍትሀዊ ‹‹ህጐችንም›› በማፅደቅ ፍትህንና ህጋዊ ስርዓትን የሚያዋርዱ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ግንቦት 20 ነፃ የፍትህ አካላት እንዲለመልሙ አለማድረጉ ሌላው የድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራ ነው፡፡
ብሔራዊ ስሜትን መናዱ (ኢትዮጵያዊነትን ማኮሰሱ)
ብሔራዊ ስሜት መናድ ለአንድ ሀገርና በውስጧ ለሚኖሩ ዜጎች ደህንነት አደጋን ይደቅናል፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ኢትዮጵያዊነት የሚንዱና ጎጣዊ ማንነት ላይ የሚያተኩሩ ፖለቲካዊ እሳቤዎችን በህዝቡ ውስጥ እንዲዘሩና እንዲስፋፉ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያን ጥንተ ታሪክ በመካድ ህዝቦች በግድ የተጠፈሩባት ‹‹የአጤ ምኒሊክ ፍጡር›› አድርገው ያስቀምጧታል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ህወሓት ስልጣን ላይ ሳይወጣ ያራምደው እንደ ነበር ግልፅ ነው፤(የኤርትራ ህዝብ ትግል ከየት ወዴት 1979ን ልብ ይሏል) የአስተሳሰቡ መነሻ የኢትዮጵያን ጥንተ ታሪክ በመካድ ቢነሳም መጨረሻው የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚል ክፉ ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ ነው፡፡

 ይህ የፀረ ኢትዮጵያዊነት ውጤት በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን መጀመሪያ ኤርትራን በማስገንጠል ተጀምሮ በ1987ቱ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39ን በማካተት መሰረቱን አጠናከረ፡፡ ከኤርትራ መገንጠል በኋላ በተነሳው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጦስ ከሁለቱም ሀገራት ‹‹ወደ ሀገራቸው› የተሸኙ ዜጎችን ሰቆቃ ለተመለከተ፣ የተሳሰረን ህዝብ ‹‹የራስን እድል በራስ በመወሰን›› ሰበብ መነጠል የሚያመጣውን ስነልቦናዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጦስ ለማገናዘብ አይቸግረውም፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ አደገኛ አስተሳሰቡን ለማረቅ የሚፈልግ አይመስልም፡፡ 

የአቶ መለስ መንግስት አራምዳለሁ ለሚለው ‹‹የልማታዊ መንግስት›› ፍልስፍና ብሔራዊ ስሜት የጎላ ሚና እንዳለው ምሁራን የተለያዩ ሀገራትን ልምድ በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ተፋልሶ ውስጥ የሚዋትተው የአቶ መለስ ኢህአዴግ ከኢትዮጵያዊነት ጋር መላተሙ ሌላው የድህረ-ግንቦት 20 ክስረት አመላካች ነው፡፡
የብሔር ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱ
በ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ይስተጋቡ ከነበሩ የፖለቲካ ጥያቄዎች ውስጥ የብሔር ጥያቄ አንደኛው ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን ጥያቄ እንደ ሰንደቅ አንስቶ የብሔረሰቦችን እኩልነት እንዳረጋገጠ ይናገራል፡፡ የብሔር እኩልነት የግንቦት 20 ፍሬ እንደሆነም ደግሞ ደጋግሞ ለማሳመን ጥሯል፡፡ ሆኖም ከግንቦት 20 በኋላም ተገፋን ተጨቆንን የሚሉ የብሔር ቡድኖች በየምክንያቱ ብቅ ብቅ ማለት ቀጥለዋል፡፡ ኢህአዴግ በቋንቋ ከመማርና ከመዳኘት ባለፈ ብሄረሰቦች ራሳቸውን የምር እንዲያስተዳድሩ የሚፈልግ አይመስልም፡፡ 

አቶ ገብሩ አስራትም በኢትዮጵያ የብሔረሰቦች መብት እንዳልተከበረ ያምናሉ፡፡ አቶ ገብሩ ‹‹ህወሓት ከጋርዮሽ አመራር ወደ አንድ ሰው ብቸኛ መሪነት›› በሚለው ፅሁፋቸው ብሔሮች በአካባቢያቸው ጉዳይ ፖለቲካዊ ስልጣን ኖሯቸው እንደማይወስኑና በአካባቢያቸው ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ያስረዳሉ፡፡  ለዚህም ይመስላል ከህወሓትና ከፌደራል መንግስት የሚወከሉ አካላት በክልል አስተዳደሮች ውስጥ ጣልቃ ገብ ተሳትፎ ያላቸው፡፡ 

 በፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ በቁጥር 39 የተሰራጨው መረጃ እንዳመለከተው ‹‹ኦሮሚያ የምትተዳደረው በክልሉ ም/ቤት በተመረጡት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ሳይሆን ከህወሓት በተመደቡት አቶ ገ/ተንሳይ ወ/ትንሳይ ነው፡፡›› ይኸው መረጃ አያይዞም ቀደም ሲልም ሰለሞን ጢሞ የተባሉ የህወሓት ሰው ኦሮሚያን ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ያስተዳድሯት እንደ ነበር አስታውሷል፡፡ የሌሎች ክልሎች ብሄረሰቦችም ራስን በራስ የማስተዳደር ዕድል እንደሌላቸው ይነገራል፡፡ 

በብሄር ብሄረሰቦች ቀን ብቻ በጭፈራ የሚታየውና በስርአቱ ተቺዎች ዘንድ ‹‹የብሔር ብሄረሰቦች መብት እስከ መጨፈር›› የሚል ስላቅ የሚገለፀው ‹‹እኩልነት›› በፖለቲካው መድረክ አይታይም፡፡ ይህ ሁኔታ ተጨማሪ የድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራ ሆኗል፡፡  
ፍትሀዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መስፈን (corny capitalism)
የአቶ መለስ መንግስት በ21 አመት የስልጣን ቆይታው ሊያሳካ ካልቻላቸው መሰረታዊ የህዝብ ጥቅሞች መካከል ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አለማረጋገጡ ዋንኛው ነው፡፡ መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ የሚያደርገው የበዛ ጣልቃ ገብነት፣ ኢትዮጵያውያን በኢኮኖሚው ውስጥ ፍትሀዊ ጥቅም እንዲያገኙ የሚያግዝ እንደሆነ ሹማምንቱ በተለያዩ መድረኮች ከመግለፅ አይታክቱም፡፡ መንግስትም የሚያንቀሳቅሳቸውን ግዙፍ ድርጅቶችም ከእጁ ለማውጣት አይፈልግም፡፡ የበታፈነ ደረጃ የተፈቀደው ‹‹የነፃ ገበያ ስርአት›› ሁሉንም የንግድ ህብረተሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚ አላደረገም፡፡ 

ኢህአዴግ ራሱ ያወጣውን ህግ ተላልፎ የፈለፈላቸው፣ በቢሊየን የሚቆጠር ካፒታል የሚያንቀሳቅሱትን የገዢው ፓርቲ ንብረት የሆኑ ኩባንያዎችን በማጠናከር እንዲሁም ከመንግስቱ ጋር ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች የተለየ ጥቅም የሚያገኙበት ሁኔታ ፈጥሯል፡፡  የዘርፉ ባለሙያዎች ይህንን ስርአት ኮርኒ ካፒታሊዝም (crony capitalism) በሚል ይጠሩታል፡፡ ኮርኒ ካፒታሊዝም የሀገሪቱ ሀብት ከስርአቱ ጋር ስምም ወደ ሆኑ ጥቂት ባለፀጋ ግለሰቦች እንዲፈስ የሚያደርግ ስርአት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ኢኮኖሚም ሆነ ቁሳዊ ልማት ጥቂቶችን ብቻ ተጠቃሚ ማድረጉ የድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራዎች መሀከል የሚጠቀስ ከመሆኑም በላይ አስተዳደሩ ለተዘፈቀበት ሙስና ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው፡፡ 
የሙስና መስፋፋት
ፕሮፌሰር ሰይድ ሐሰን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ትንታኔዎችን በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡ እኚህ ምሁር ሙስና ኢትዮጵያ ውስጥ ስር የሰደደ ስርአት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡በቅርቡ ‹‹ሙስና ኡ!  ኡ! እሪ! እሪ!›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ ዓለም ባንክ ባደረገው ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና አደገኛ ስርአነት ወደ መሆን መሸጋገሩን ያብራራሉ፡፡ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ ጉምሩክና የገቢዎች ባለስልጣን፣ የወረዳ አስተዳደርና ማዘጋጃ ቤቶች ሙስና በእጅጉ የተንሰራፋባቸው ናቸው፡፡ 

የህወሓት አንጋፋ መሪ የነበሩት አቶ ስብሀት ነጋም ሙስና በሀገሪቱ አደገኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ እንዳሳሰባቸው በይፋ መግለፃቸውና አቶ መለስም የመንግስት አካላትም በአደገኛ ሙስና ዘፈቃቸውን ማመናቸው ሙስና ከድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራዎች መሀከል የሚጠቀስ ሆኗል፡፡                                                                                      
ስርአቱን የሚተቹ አካላትን ማፈን
የህወሓት/ኢህአዴግ ታጋዮች ደርግን ከተዋጉበት ምክንያት አንዱ የደርግ ተቃውሞን የማፈን እርማጃ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ታጋዮቹ ደርግን አስወግደው ሌላ ‹‹ደርግ›› መተካታቸውን የሚያስረዱ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ስርአቱን የሚተቹ አካላትን የአቶ መለስ መንግስት ማሰር የጀመረው በቅርቡ ባይሆንም፣ በአረብ ሀገራት የተከሰተውን መነሳሳት ተከትሎ የተቃውሞ ፖለቲካ አመራሮችንና ጋዜጠኞችን ‹‹በሽብር›› ሰበብ ቃሊቲ አውርዷል፡፡ በይፋም ሆነ በኢመደበኛ ወጎች መንግስትን መተቸት የሚያስጠይቅበት ደረጃ በመድረስ ላይ ይገኛል፡፡ 

መንግስት ስርአቱን የሚተቹ አካላትን ለማሸማቀቅ የሚጠቀምባቸው መንገዶች ሰላማዊ ትግልን የሚያደናቅፉ ከመሆናቸውም በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ብሶትና ተቃውሞ ወደ ግብታዊ አብዮት የመምራት ውጤትም ሊያስከትል ይችላል፡፡ በሰላማዊ ትግል ተስፋ ቆርጠው መሳሪያ ያነሱ ቡድኖችን ያበራከተው ይህ አካሄድ፣ ከኢህአዴግ ጋር ልዩነት ያላቸው የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ ትግል እንዲሳተፉ አለማበረታታቱ የአቶ መለስ ስርአት የድህረ-ግንቦት 20 ክስረት አንድ አካል ነው፡፡      
ነፃ የሲቪክ ማህበራት አለመጠናከራቸው
ነፃ ማህበራት በአንድ ሀገር ላይ ዴሞክራሲ እንዲያብብ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ሚካኤል ባራቶን (Michael Bratton) ‹‹CIVIL SOCIETY AND POLITICAL TRANSITION IN AFRICA›› በሚል ፅሁፋቸው ከቀዝቃዛው ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ ነፃ ማህበራት በዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸው ሚና እየተጠናከረ እንደመጣ ያስረዳሉ፡፡ አያይዘውም ነፃ ማህበራት ይህን አበርክቷቸውን እንዲወጡ የመንግስትን ኃይል የሚዘውሩ አካላት ፈቃደኝነት አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ይገልፃሉ፡፡ የነፃ ማህበራት አበርክቶ በኢትዮጵያ ከመዳከም አልፎ የተዳፈነ ይመስላል፡፡

ኢህአዴግ ከ1997 በፊት በአንፃራዊ መለኪያ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸውን ማህበራት፣ ከድህረ 97 በኋላ ነፃነታቸውን የሚጋፋና ህልውናቸውን የሚፈታተን ህግ በማፅደቅ አልፈስፍሷቸዋል፡፡ የማህበራቱን ነፃነት በመጋፋት የፓርቲውን ፖለቲካ የሚያራምዱ ግለሰቦችን በአመራር ደረጃ በማስረግ ጭምር ተሳትፏቸውን አዳፍኗል፡፡ 

መንግስት ነፃ ማህበራት የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ ባህልና ግንዛቤ በማዳበር የሚያበረከረቱትን አስተዋፅኦ ከማበረታታት ይልቅ፣ ከዚምባቡዌ፣ ሲንጋፖርና ሩሲያ የተወሰዱ አደገኛ ልምዶችን የቃረመ አደገኛ የበጎ አድራጎትና የሲቪክ ድርጅቶች አዋጅ አፅድቋል፡፡ በዚህ ህግ ምክንያት የመስራት አቅማቸው የተሸመደመደ እና ወደ ሌላ ዘርፍ ስራቸውን የቀየሩ ማህበራት ቁጥር በርካታ ነው፡፡

ይህ ማህበራትን የማዳከምና ነፃነታቸውን የማሳጣት ስትራቴጂ በቀጥታ የህዝቡን የነፃነት የመደራጀት መብት የሚጋፋ ከመሆኑም በላይ ዴሞክራሲ የማይዋጥላቸው አምባገነን መንግስታት ተግባር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር 21 አመታትን በምኒሊክ ቤተመንግስት ያሳለፈው የአቶ መለስ መንግስት ነፃ ማህበራትን በስልት ማዳከሙ የድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡ 
         
የነፃ ፕሬስስ ሀሳብን የመግለፅ መብት አለመከበሩ
 ኢህአዴግ ወደ ስልጣን እንደወጣ ከወሰዳቸው አበረታች እርምጃዎች ውስጥ የፕሬስና ሀሳብን የመግለፅ መብትን “መፍቀዱ” ነው፡፡ መንግስት ይህ መብት ህገመንግስታዊ እንዲሆን ቢያደርግም በተግባር ግን አፋኝ እርምጃዎችን ከጅምሩ መውሰዱ ነፃ ፕሬስ እንዳይዳብር እንቅፋት ሆኗል፡፡የአንድ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መገለጫ የሆነው የፕሬስና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በኢትዮጵያ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ መንግስት ላይ ትችት የሚያቀርቡ ጋዜጠኞች እና ሀሳባቸውን በይፋ የሚገልፁ ፖለቲከኞች መታሰር፤ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የአደባባይ ምሁራንን አርቋል፡፡ 

ሀሳባቸው የሚገልፁ ጋዜጠኞችና ተቺዎች ከእስር ጋር ተፋጠው ለመስራት ተገደዋል፡፡ ኢህአዴግ ያወጣቸው የፕሬስና የፀረ ሽብር አዋጆች ኢትዮጵያውያን ሀሳባቸውን በፕሬስ ውጤቶች እንዳይገልፁ የሚጠፍር ከመሆኑም በላይ በአንዳንድ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን እንዳያገኙ አግዷል፡፡ በተለይም ኢህአዴግ በቅርቡ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በኩል ቅድመ ምርመራን ለመጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩ ከላይ ያየናቸው የድህረ ግንቦት 20 ኪሳራዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሀገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ እንዲከስም አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ በሚረዱት የፕሬስ ውጤቶች አለማደግ ብሎም መመናመን የድህረ ግንቦት 20 ኪሳራ ሌላው ማሳያ ነው፡፡
ሀገሪቱ በአንድ ጠቅላይ አምባገነን መሪ ስር መውደቋ
ጠቅላይ አምባገነንነት በአጭር ጊዜ የሚገነባ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ከመገንባት የበለጠ ጊዜና ወጪ ይጠይቃል፡፡ ይህን አምባገነናዊ ስርአት ለመገንባት መንግስት በህዝቡ ሁሉን አቀፍ የህይወት ፈርጅ ውስጥ ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በትምህርት ፣ በኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊ፣ በባህልና ኪነጥበብ ውስጥ ፖለቲካዊ ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም ፖለቲካዊ እንነታቸውን በማጥመቅ አቶ መለስ ጠቅላይ አምባገነን መሆንን መርጠዋል፡፡ 

በ2002 ምርጫ 99.6 በመቶ በሆነ ውጤት ፓርላማውን የተቆጣጠረው የአቶ መለስ መንግስት አውራ ፓርቲ መሆኑን በመግለጽ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ተንኮታኩቶ ጠቅላይ አምባገነን ስርዓት መደላደሉን አብስሯል፡፡ ግንቦት 20 አቶ መለስን በኢትዮጵያ አንግሷል፡፡ በሀገሪቱ ላይ ብቸኛው አድራጊና ፈጣሪ አቶ መለስ ናቸው፡፡ ሙገሳቸውም ሆነ ወቀሳቸው ድጋፋቸውም ሆነ ተቃውሟቸው እንደ እግዜር ቃል ይታያል፡፡ ለግንቦት ሃያ የተከፈለው መስዋዕትነት አቶ መለስን የሀገሪቱን ቁንጮ ከማድረግ ያለፈ ውጤት ያመጣ አይመስልም፡፡ የድህረ ግንቦት 20 ኪሳራዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ከህወሓት/ኢህአዴግ ነፃ የሚወጣውን የድል ቀን እንዲጠብቅ ሳያስገድዱት የሚቀር አይመስልም፡፡

Source: http://www.ethiomedia.com/2012_report/fenote_forty_four.pdf,  ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ, page 2

No comments:

Post a Comment