Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, May 27, 2012

ትምህርት ቤቶች ከመደበኛው የመዘጊያ ዕለታቸው አንድ ወር ከ 15 ቀደም ብለው እንዲዘጉ ትዕዛዝ ተላለፈ

ኢሳት ዜና:-
መምህራን ለ ኢሳት እንደገለጹት፤በአዲስ አበባ እና በዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች የሁለተኛ መንፈቅ ትምህርት ክፍለ ጊዜን ከያዙት መርሃ- ግብር ቀደም ብለው እንዲያጠናቅቁና ትምህርት ቤቶቹ እንዲዘጉ ኢህአዴግ መመሪያ አውርዷል።

የኢህአዴግን ድንገተኛ ውሳኔ በመቃወም ከወረዳ እና ከዞን ትምህርት ቢሮዎች ጋር ለመነጋገር የሞከሩ ትምህርት ቤቶች ተቀባይነት አላገኙም ያሉን አንድ ርዕሰ መምህር ፣ ተማሪዎች በሁለተኛው መንፈቅ የትምህርት ጊዜ ሊሸፍኑት ይገባ የነበረውን የትምህርት መርሃ ግብር እንዲዘሉትና ሁኔታውን ታሳቢ ያደረገ ቦነስ ውጤት በአስቸኳይ ለተማሪዎች እየሰጡነ እንዲሸኟቸው መታዘዛቸውን ገልጸዋል፡፡

ከደመወዝ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ከኢህአዴግ መንግሥት ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑት መምህራን ከወራት በፊት በመቱት የሥራ ማቆም አድማ የበቀል እርምጃ እየተወሰደባቸው እንዳለ ለዘጋቢያችን የተናገሩ አንድ የአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት መምህር ፤ የሥራ ማቆም አድማውን አስተባብራችኋል የተባሉ መምህራን እየተቀጡና ከሥራ እየተፈናቀሉ ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ መምህሩ ገለፃ ከመምህራኑ የሥራ ማቆም አድማ በኋላ በሁሉም ትምህርት ቤቶች አካባቢ በርካታ ፖሊሶች፣ ሲቪል ፖሊሶች እና የደህንነት ሠራተኞች ዘወትር በሥራ ሰዓት በብዛት መሰማራት ጀምረዋል።

“ ተራ የተማሪዎች ጸብ ሳይቀር በደህንነት ሠራተኞችና በሲቭል ፖሊሶች ክትትል ስለሚደረግበት ለተማሪዎቻችንና ለእራሳችንም ህይወት ጭምር ሰግተናል” ሲሉም  በየትምህርት ቤቶች አቅራቢያ የሚታየው ውጥረት እየተባባሰ መሆኑን አመላክተዋል።

መንግስት የትምህርቱን መርሃ-ግብር ሳናጠናቅቅ ተማሪዎቻችንን እንድንበትን የፈለገበውም ፤ የተቃውሞው ሁኔታ ተማሪዎችን አካቶ ያገረሻል ከሚል ሥጋት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት በመምህራኑ ዘንድ  እንዳለ አክለው ገልጸዋል፡፡

በሌላ ዜና  የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር የአመራር ለውጥ አድርጓል።  ሰሞኑን በተደረገው ምርጫ ላይ የተሳተፉ የመምህራን ማህበር የትምህርተ ቤት ተወካዮች ለነባሩ አመራር የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበው እንደነበርም ታውቋል።

መምህራኑ መንግስት ባደረገው የእርከን ማሻሻያ፣ በመምህራን ላይ እየደረሰ ባለው ወከባ እና የተባረሩ መመህራንን ወደ ስራ በመመለስ በኩል እየተደረገ ባለው ትግል ማህበሩ ጥረት አላደረገም በማለት የተቃውሞው ንግግሮችን አድርገዋል።

No comments:

Post a Comment