By ተመስገን ደሳለኝ
የካቲት 11/1967 ደደቢት በረሃ
‹‹የትግራይ ህዝብ በብሔራዊ ጭቆና ውስጥ ነው። እናም የግድ ከዚህ ብሔራዊ ጭቆና እና ብዝበዛ ነፃ የሚያወጣው ብሔራዊ ድርጅት ያስፈልገዋል›› (ይህንን መልዕክት የምናገኘው ህወሓት በ1967ዓ.ም የካቲት 11 ቀን ወደ በረሃ ለትግል ሲወጣ ያወጣው ማኒፌስቶን በግርድፉ ከትግርኛ ወደ አማርኛ ስንመልሰው ነው) ግንቦት 20/1983 አዲስ አበባ ‹‹ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬዲዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲል ተቆጣጥሮታል።
ግንቦት ሃያ ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሶስት፡፡
›› (በዘመቻ ወጋገን አዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር መውደቋን የኢህአዴግ ታጋይ ያበሰረበት ዜና)
ግንቦት 10/2004 ዋሽንግተን-አሜሪካ
“Meles zenawi is a dictator! Free
Eskinder Nega and all political prisoners!
We need freedom more than food! Meles
has committed crimes against humanity!
We need freedom! Freedom! Freedom!
Freedom!››
(መለስ ዜናዊ አምባገነን ናቸው፤ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፤ ምግብ ያለነፃነት ዋጋ የለውም፤ መለስ በሰው ልጆች ላይ ወንጀል ፈፅመዋል፤ ነፃነታችንን እንፈልጋለን፤ ነፃነት! ነፃነት! ነፃነት!) (ይህ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ
በዋሽንግተን ዲሲ አዘጋጅተውት በነበረው አለም አቀፍ ስብሰባ ላይ በአዳራሹ ውስጥ በመገኘት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ንግግርን በማቋረጥ ያሰማው የተቃውሞ ድምፅ ነው) …ለአስራ ሰባት አመት በትግል፤ ያሳለፈው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ከነገ በስቲያ (ግንቦት 20/2004ዓ.ም) ድፍን ሃያ አንድ አመት ይሞላዋል።
“Meles zenawi is a dictator! Free
Eskinder Nega and all political prisoners!
We need freedom more than food! Meles
has committed crimes against humanity!
We need freedom! Freedom! Freedom!
Freedom!››
(መለስ ዜናዊ አምባገነን ናቸው፤ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፤ ምግብ ያለነፃነት ዋጋ የለውም፤ መለስ በሰው ልጆች ላይ ወንጀል ፈፅመዋል፤ ነፃነታችንን እንፈልጋለን፤ ነፃነት! ነፃነት! ነፃነት!) (ይህ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ
በዋሽንግተን ዲሲ አዘጋጅተውት በነበረው አለም አቀፍ ስብሰባ ላይ በአዳራሹ ውስጥ በመገኘት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ንግግርን በማቋረጥ ያሰማው የተቃውሞ ድምፅ ነው) …ለአስራ ሰባት አመት በትግል፤ ያሳለፈው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ከነገ በስቲያ (ግንቦት 20/2004ዓ.ም) ድፍን ሃያ አንድ አመት ይሞላዋል።
ግንባሩ ከተመሰረተበት ከ1981ዓ.ም ጀምሮ የሚመራው ዛሬም በስልጣን ላይ ባሉት ሊቀመንበር መለስ ዜናዊ ሲሆኑ፣ የመንግስት ስልጣን ከያዘም በኋላ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ራሳቸው መለስ ናቸው። ይህ ሁኔታም ድርጅቱን ለሁለት መሰረታዊ ትችቶች ዳርጎታል። የመጀመሪያው የፓርቲ (የውስጥ) ዴሞክራሲ ያለመኖሩ ማረጋገጫ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ድርጅቱ ምንም እንኳ ሰባት ሚሊዮን አባላት ያሉት ቢሆንም አቶ መለስን ለመተካት አንድም ብቁ ሰው እንደሌለው ወይም ማፍራት ያለመቻሉን የሚያሳይ በመሆኑ ነው።
የመከኑ ተስፋዎች…
እንደ 17 አመቱ የትግል ታሪክ ትርክት ከሆነ ኢህአዴግ ለስልጣን የበቃው መራራ ትግል በማድረግ እና ከ60-70 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያንን ህይወት በመገበር ነው። ህም ሆኖ ወደ ስልጣን በመጣበት ሰሞን በርካታ መልካም ነገሮች ከመኖራቸው አንፃር፣ የተከፈለውን መስዋዕትነት ያህል ባይሆንም ብዙ ተስፋ የተጣለባችው ወሳኝ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ እናም የዘንድሮውን ግንቦት ሃያ በማሰመልከት ከእነዚህ ውስጥ ሶስቱን መዘን በሃያ አንድ ዓመት ውስጥ የት እንደደረሱ እንፈትሻለን፡፡ ነፃ ፕሬስ፣ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እና የሰብአዊ መብት አያያዝ፡፡
ነፃ ፕሬስ
በሀገሪቱ ታሪክ የነፃ-ፕሬስ በአዋጅ የተፈቀደው በኢህአዴግ ዘመን ለመሆኑ መስካሪ አያስፈልግም። በእርግጥ በአፄ ምኒልክ ዘመን በአንድ ግሪካዊ ባለቤትነት በየሳምንቱ 200 ኮፒ ያህል የሚታተም ‹‹አእምሮ›› የተባለ ጋዜጣ የሀገሪቱ የመጀመሪያው የፕሬስ ውጤት መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዓመታዊ መጽሔት በህዳር 2002 ዓ.ም እትሙ በ1915 ዓ.ም. በምፅዋ ከተማ እየተዘጋጀ የሚታተም ‹‹መለከተ ሰላም››ን ጨምሮ በግሪካውያን ‹‹ኢትዮ አለም›› እና በብላታ ጌታ ኀሩይ ወልደስላሴ ‹‹ኮከበ ጽባህ›› የሚባሉ ጋዜጦች ይዘጋጁ እንደነበር ገልጿአል።
ከ16 ዓመት በኋላ ደግሞ በ1917 ዓ.ም. ‹‹ብርሃንና ሰላም›› የተባለ ጋዜጣ በንጉሰ ነገስቱ ትዕዛዝ መንግስት ልሳን ሆኖ መታተም ጀመረ። ከዚህ በኋላም እነሆ ዛሬም ድረስ የመንግስት ‹‹አንደበት›› ሆኖ እያገለገለ ያለው ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ በ1933ዓ.ም ተቋቋመ። በ1935ዓ.ም ‹‹ኢትዮጵያን ሄራልድ›› የህትመት ስራን ተቀላቀለ፡፡ እንደ ብሮድካስት ዘገባ በአፄው ዘመን ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ሰንደቅ አላማችን፣ ኅብረት፣ አክሎቲዲያኖ፣ አልአለም እና በሬሳ›› የተሰኙ ጋዜጦችም በተጨማሪነት ለመታተም ችለዋል። ከመጽሔት ደግሞ በንግስቲቱ ስም የተሰየመችው ‹‹መነን›› መጽሔት የመጀመሪያዋ ነች።
ንጉሱ ወድቀው ወታደራዊው የመንግስቱ ኃ/ማርያም መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ (ውስጥ ውስጡን የኢህአፓ እንደሆነች የሚነገርላት) በጨረታ ማስታወቂያ ስር የምትታተመው ‹‹ጎህ›› መጽሔት ለሁለት አመት ያህል ብቻ ብቅ ብላ፣ ከእነ‹‹እናት ድርጅቷ›› ኢህአፓ ጋር በወታደራዊ ኃይል ምድረ ገጽ እንድትጠፋ ከመደረጓ ውጭ፤ በአዋጅ የፕሬስ ነፃነት ከመገደቡም አልፎ ቅድመ ምርምራ በይፋ ስራ ላይ ውሎ ስለነበር ደርግ ከነፃ ፕሬስ ጋር ምንም አይነት ‹‹ፅዋ›› አልነበረውም። …ኢህአዴግ የእርስ በእርስ ጦርነቱን በአሸናፊነት ተወጥቶ በ1983 ወርሃ ግንቦት ወደ ስልጣን ሲመጣ የነፃ ፕሬስ ህልውናን በአዋጅ በማረጋገጡ የመጀመሪያ ሆና የተመዘገበችውን የእስክንድር ነጋን ‹‹ኢትዮጲስ›› ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነፃ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ከአዲስ አበባ አንስቶ በሁሉም የክልል አውራ ጎዳናዎች ተጥለቀለቁ።
የብሮድካስት ምንጭ ‹‹በ1985ዓ.ም በሀገሪቱ 118 ጋዜጦች እና መጽሔቶች ተመዝግበው ስራ የጀመሩ ሲሆን፤ ይኸው አሀዝ በ1990ዓ.ም.554 ደርሶአል›› ይላል። በ2000ዓ.ም. በሀገሪቱ የነበረው መጽሔት እና ጋዜጣ ቁጥር ከአንድ ሺ በላይ ደርሶ እንደነበረም አረጋግጧል። ‹‹የኢትዮጵያ ብሮድካስት ለስልጣን ዓመታዊ መጽሔት›› በሚል የታተመው የኤጀንሲው ልሳን በዚህ ዕትሙ አንድ አስቂኝ ጥያቄም ይዟል። እንዲህ የሚል ‹‹የህትመት ውጤቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። በ2000 ዓ.ም.ተመዝግበው የነበሩት ከአንድ ሺህ በላይ ደርሰው እንደነበር ቢያውቁ እውነት ላይ-መስል ይችላል፡፡ ግን ነው! ከዚህ ላይ ሊቀርብ የሚገባው ጥያቄ ግን ይህን ያህል ቁጥር የነበራቸው ጋዜጦችና መጽሔቶች አሁን ከወዴት ገቡ? የሚል ይሆናል›› ቀልዱ የሚገባን ደግሞ በኢትዮጵያ ለህትመትም ሆነ ለኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ፍቃድ የሚሰጠውም ሆነ የሚከለክለው ይኸው መስሪያ ቤት መሆኑን ስናውቅ ነው።
ልክ ከፕሬስ ህልውና ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ‹‹የገጠርና ግብርና ሚንስቴር›› ወይም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር›› መስሪያ ቤትን ይመስል ‹‹ሚዲያዎቹ የት ገቡ?›› ሲል መጠየቁ ነው ቀልዱን መራር ቀልድ የሚያደርገው። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። ምሳሌ በመጀመሪያስ ጋዜጦቹ እንዲህ በብዛት እንዲታተሙ ለምን ፍቃድ መስጠት አስፈለገ? በእርግጥ የዚህ ጥያቄ መልስ አዙሮ አዙሮ ‹‹ምዕራባውያንን ለማስደሰት›› የሚል ምላሽ ላይ ቢያደርሰንም፤ በዚህ መሀል ግን የኢህአዴግ የተደበቀ ‹‹ቀጭን የማሳደድ እና የማጥፋት ፍላጐት›› እንደነበረ መካድ አይቻልም። ሆኖም ምንም እንኳ አመራሮቹም ሆኑ ታጋዮቹ በሶሻሊዝም እና ማርክሲዝም አስተሳሰብ የተቀኙ ቢሆኑም ከቀደምቶቹ የኢትዮጵያ ገዢዎች የተለዩ እንደሆኑ የማሳየቱ ፍላጐት አልነበራቸውም ልንል አንችልም።
እናም የግንባሩን መሪዎች የእነዚህ ውጤት ነው በወቅቱ ያአለአንዳች ማንገራገር የነፃ ፕሬስ ህልውናን በአዋጅ እንዲፈቅዱ ያስገደዳው። ነገር ግን ፕሬሱ በስራ ላይ በዋለ ማግስት ከመንግስት ጋር መላተም ጀመረ። ለዚህም እንደመነሻ የሆነው የተሸነፈው የሀገሪቱ ሰራዊት ‹‹የደርግ ወታደር›› ተብሎ መበተኑ፣ በርካታ ሰራተኞች ያሉአቸው መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች እንዲፈርሱ እና ሰራተኞቹም ያለአንዳች ካሳ መበተናቸው፣ የብሔር ፖለቲካ መጦዝ፣ እንዲሁም የኤርትራ መገንጠል እና ሀገሪቱ ያለወደብ መቅረት… በነፃው ፕሬስ በስፋት የሚተችበት መሆኑ ነው ገዥውን ፓርቲ ‹‹ሆደባሻ›› ያደረገው። በአናቱም በእነዚህ ጋዜጦች እና መፅሄቶች የሚስተናገዱት ጽሑፎች የንባብ ባህል ከመፍጠርም አልፈው በህብረተሰቡ ውስጥ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ እየሆኑ መሄዳቸውም ለአዲሱ መንግስት ምቾት እንደነሳው ፍንጮች መታየት የጀመሩት ገና በጠዋቱ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎንም ያለፉት ስርዓቶች ትተው ያለፉት የ‹‹ፖለቲካን በሩቁ›› አመለካከት ቀስ በቀስ ደብዘዝ ጀመረ። የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና አመራሮችም የመንግስት ዋነኛ የአደባባይ ነቃፊ ለመሆን ቻሉ። በተጨማሪም የመንግስት ሚዲያ ሙሉ በሙሉ ‹‹የፕሮፓጋንዳ ማሽን›› በመሆኑ እነዚህ ጋዜጦች እና መጽሔቶች አማራጭ የመረጃ ምንጭ ተደርገው የተሻለ ተአማኒነት ግኘታቸው ከቀን ወደ ቀን ኢህአዴግን እያስቆጣው ሄደ። የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው በምርጫ 97 ሀገራዊ መነቃቃት ፈጥሮ በህዝብ ተሳትፎ በአፍሪካ አቻ ያልተገኘለት ምርጫ ሊካሄድ የበቃው። እንደሚታወቀውም የምርጫው ውጤት ወደተቃዋሚዎች ማጋደሉን ተከትሎ ግንባሩ ወደ እውነተኛ ማንነቱ ተመልሶ በቀጥታ ብትር እና በተለያዩ አፋኝ አዋጆች ጭምር ‹‹ነፃ ሚዲያ›› ወደመቃብር ተገፋ።
እንግዲህ ከግንቦት ሃያ ፍሬዎች አንዱ የሆነው ነፃ ፕሬስ ዛሬ ሙሉ በሙሉ የለም ሊባል የሚችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በቀናት የሚቆጠሩ እድሜዎች ብቻ መቅረቱን አስተውለን፣ በቅርቡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በ‹‹ስታንዳርድ ውል›› ስም በስራ ላይ ለማዋል ደፋ ቀና እያለበት ያለውን ‹‹የቅድመ ምርመራ ህግ›› ስንደምርበት ነው ከሃያ አንድ አመት በኋላ፣ ያውም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያኖች ደምና አጥንታቸውን ከስክሰው ወደ ገረሰሱት ስርዓት መመለሳችንን የምንረዳው-ግንቦት ሃያ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሶስት፡፡
የመድበለ ፓርቲ ስርዓት
ይህ ደግሞ ሌላኛው የግንቦት ሃያ ፍሬ ነው። ምክንያቱም ለ17 አመት የነበረውን የአንድ ብቸኛ ፓርቲ ስርዓት ገርስሶ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በተግባር የታየው ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣበት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት አመታት ነውና።
ግንቦት 20/1983ዓ.ም ኢሠፓ የተሰኘው የመንግስቱ ኃ/ማርያም ፓርቲ ከስልጣን ከወረደ በኋላ ኢህአዴግ ራሱን በኢሠፓ ቦታ ተክቶ ብቻውን ስልጣን አልያዘም። ይልቁንም ሁሉንም በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ከኢህአፓ እና መኢሶን በስተቀር) በአዋጅ ሰብስቦ ስልጣን አካፈለ እንጂ፤ ያውም በምርጫ ሳይሆን በዕደላ። በዚህም መሰረት በ1983ዓ.ም መጨረሻ ‹‹ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ምክር ቤት ተወካዮች›› የሚባል በአጠቃላይ 87 የውክልና ቦታ /መቀመጫ/ ያለው መንግስት ተቋቋመ። ከዚህ ውስጥም ኢህአዴግ 32 (37%) ወንበር ብቻ ወስዶ የተቀረውን ኦነግን ጨምሮ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች አከፋፈለ። (አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንድ፣ የሰራተኞች ማህበር ሶስት ወንበር እንዲያገኙ ተደርገዋል)።
ይህንንም ተከትሎ የትግሉ ዋነኛ የስንቅና ትጥቅ ምንጭ የነበሩት ምዕራባውያን ‹‹በኢትዮጵያ መድበለ ፓርቲ ስርዓት እውን የሚሆንበት መደላድል ተፈጠረ›› ሲሉ ከማድነቅም አልፈው የሽግግር መንግስቱን በሙሉ አቅማቸው መርዳት ጀመሩ። ይህ ደግሞ ድርጅቱ ታግሎ ያመጣው መልካም ነገር በመሆኑ የሚመሰገንበት ነው። / ምንም እንኳን ምስጋናው ዘላቂ ባይሆንም/ የሆነ ሆኖ በቀጣዮቹ አመት በሚታዩ እና በማይታዩ መሰናክሎች በሽግግር መንግስቱ ውስጥ በርካታ ወንበር የነበራቸውን ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማፈናቀል ተጀመረ። ከዚህ በኋላም የአራቱ አመት የሽግግር ዘመን አልፎ፣ ህገ መንግስቱ ፀድቆ እና ሀገሪቱ የምትመራው በፓርላሜንታዊ ስርዓት መሆኑ በህገ መንግስቱ ከተገለፀ በኋላ ፓርላማው 547 ወንበር እንዳለው ተደንግጐ የ1987ዓ.ም ምርጫ ተካሄደ።
የዚህ ምርጫ ውጤት ምን ሆነ? የሚለውን ካየን፣ ውጤቱ ይህ ነው፡- ኢህአዴግ 493፣ አጋር ፓርቲዎች እና ተቃዋሚዎች 40 ወንበሮች ሲያገኙ ቀሪዎቹ አስራ አራት ወንበሮች በግል ተወዳዳሪዎች ተያዙና በጥቂቱም ቢሆን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ለመኖሩ ምልክት ሆኑ። በምርጫ 92 ደግሞ ኢህአዴግ 481 ወንበር ሲያገኝ፤ አጋር ፓርቲዎች 40 ወንበር ተቃዋሚዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች በድምሩ 13 ወንበር አገኙ። በእርግጥ ለተቃዋሚዎች ደካማ ውጤት፤ ደካማ አደረጃጀታቸው እንደ ምክንያት በስፋት ይቀርብ እንደነበር አስታውሳለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም ‹‹ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ከአገኘን ግማሽ መንገድ ድረስ ሄደን እንቀበለዋለን›› ሲሉ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ድክመት አዘኔታቸውን የገለፁበት ጊዜ ነበር-ያ ጊዜ።
በአናቱም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት እና እርስ በእርስ ያላቸው ንቁርያ የድክመታቸው አንዱ ምክንያት ተደርጎ በተንታኞች የሚቀርብበት ዘመንም ነበር-ያ ዘመን። በዚህ ሁኔታም ምርጫ 97 ደረሰ። በዋዜማው በ1996 ክረምት በተደረገው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀመንበሩ አቶ መለስ ዜናዊ ‹‹ቀጣዩ ምርጫ እንከን የለሽ ይሆናል›› ሲሉ ቃል ገቡ። ይህንም ተከትሎ አንድም የህዝቡን ‹‹ወይ ተባበሩ፤ አሊያም ተሰባበሩ››ን ግፊት፣ ሁለትም የታላላቅ ሰዎች ሽምግልና ታክሎበት በወቅቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የነበሩት መኢአድ እና ኢዴፓ ዘግይተው የተቀላቀሉትን ቀስተደመና እና ኢዴሊን ጨምረው ‹‹ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ››ን ሲመሰርቱ፤ ራሳቸውን በዘውግ ከልለው የቆዩት የሐድያ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እና የኦሮሞ ኮንግረስ ፓርቲም መቀመጫቸውን በሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ ካደረጉ ሌሎች 12 ድርጅቶች ጋር የጋራ ህብረት በመፍጠር ‹‹የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት (ኢዴኃሕ)››ን መስርተው በተቃውሞ ጎራ ያለው ቡድን ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዲሆን አደረጉት።
በዚህ እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች አብዛኛው የፖለቲካ ተንታኞች ምርጫ 97 የኢትዮጵያውያኖች የፖለቲካ ንቃተ ህሊና የተሻለ ደረጃ የደረሰበት እንደነበር ይስማማሉ። በዚህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ በተሳተፈበት ምርጫም ኢህአዴግ ያልጠበቀው ሽንፈት ደረሰበት። ይህንን ሁኔታም አቶ በረከት ስምኦን ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፋቸው ላይ ውጤቱን ‹‹የብራ መብረቅ›› ሲሉ ምን ያህል ከባድ ሽንፈት እንደደረሰባቸው ገልፀውታል። ይሁንና ይህንን ምርጫ ተከትሎ ድርጅታቸው በመድብለ ፓርቲ ስርዓትም ሆነ በምርጫ ፖለቲካ ላይ መአት እጆቹን ለቅጣት አነሳ። እናም የምርጫውን ግርግር ታክኮ የተነሳውን ሁከት እንደምክንያት በማድረግ ሁሉንም የቅንጅት አመራር ጨምሮ ከ40 እስከ 50 ሺህ የሚገመቱ ዜጎችን ‹‹የተቃዋሚ ተባባሪ እና የጎዳና ላይ ነውጠኛ›› በሚል የእመቃ እርምጃ ወሰደባቸው።
ከዚሁም ጋር መራጮች በምርጫው ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው፣ ሀገራዊ ንቃተ ህሊና እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉት ጋዜጦች ህትመታቸው እንዲቆም ሲደረግ፤ አሳታሚዎቹ እና ጋዜጠኞቹ ‹‹የአመፁ ጠንሳሽ›› ተብለው ለ20 ወር እስር ተዳረጉና ፋይሉ ተዘጋ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ‹‹ሀገራዊ ድብት›› የሰፈነው። በዚህ ድብት ውስጥም ነው ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ አውራ ፓርቲ እንደሆነ ያወጀበት ምርጫ 2002 የተካሄደው። በዚህም የፓርላማው መቀመጫ የአንድ ፓርቲ ብቻ ሆነ። እንግዲህ ይህ ነው ሌላኛው ወደ ግንቦት ሃያ ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሶስት ለመመለሱ ማረጋገጫ የሚሆነው። እናም እዚህም ጋር እንዲህ ልንል እንችላለን ‹‹ሌላ ፋይል ተዘጋ››፤ መድበለ ፓርቲ ስርዓት ጠፍቶ አውራ ፓርቲ ነገሰ፡፡
ሰብዓዊ መብት
ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ዕለት ጀምሮ አንዳችም ‹‹ተስፋ የሚሰጥ›› ነገር ያልታየበት ነው-የሰብዓዊ መብት አያያዙ። በመጀመሪያዎቹ ጥቂት አመታት በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ላይ በጎ ጅማሬዎች እንደነበሩ ከላይ ተነጋግረናል። ነገር ግን የሰብዓዊ መብት አያያዙ በ1969ዓ.ም ሆነ በ1983ዓ.ም ወይም በ2004ዓ.ም አንዳች ልዩነት የለውም። ደርግ ለሰብዓዊ መብት ቅንጣት ታኽል ደንታ የለውም። ኢህአዴግም የለውም። በዚህ መካከል ልዩነት የለም። ምንአልባትም በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የተደረገው ጦርነት ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተገናኘ ብቻ ቢሆን ኖሮ ሁለቱም በጋራ ይሰለፋሉ እንጂ ወደ ጦርነቱ አይገቡም ነበር ማለት በሚያስደፍር ሁናቴ ነው ተመሳሳይነታቸው። ሁለቱም ስርዓቶች ሰብዓዊ መብትን ሲጥሱ ለየትኛውም የሀገሪቱ ህግ አይጨነቁም። ከዚህ በተጨማሪም ይህን አይነቱን ወንጀል ሲፈጽሙ ከጊዜ ልዩነት ውጭ የሚጠቀሙበት መንገድ ፍፁም ተመሳሳይ ነው። ለንፅፅር ይርዳ ዘንድ በሁለቱም ስርዓት ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የተደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደምሳሌ እንይ።
ሚያዚያ 23/1969-ደርግ
‹‹…የ1969 ዓ.ምቱ የላባደር ቀን (ሜይ ዴይ) እንደማንኛውም ተራ ቀን እንዲያልፍ ተወስኖ ነበር። የኢላአማ በይነ ቀጠና ኮሚቴ በዚህ ውሳኔ ላይ ያለውን ቅሬታ አሰምቶ ትናንሽ ቡድኖችን በቀበሌ ደረጃ አዘጋጅቶ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ሃሳብ አቀረበ። ይህ የኢላአማ ሃሳብ በአዲስ አበባ በይነ ቀጠና ኮሚቴ ተቀባይነት አገኘና ለሰልፍ የሚደረጉ ዝግጅቶች መካሄድ ጀመሩ። …ሰልፉ ከመደረጉ ከሶስት ወይም ከአራት ሰአት በፊት የኢህአፓ የአዲስ አበባ በይነ ቀጠና ኮሚቴ አገዛዙ ስለተቃውሞ ሰልፎቹ ዝርዝር መረጃዎች እንዳገኘ የሚገልፅ መረጃ ደረሰው…. በዚህ ዕለት አገዛዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሚገባ የታጠቁ የደህንነት ሰራተኞችን አሰማራ። የደህንነት ሰራተኞቹ የደንብ ልብስ የለበሱም ያለበሱም ነበሩበት።
በአንዳንድ ስፍራዎች የተቃውሞ ሰልፎቹ ተጀምረው ጥቂት ደቂቃዎች እንዳለፉ ከአካባቢያቸው ጋር የተመሳሰሉ ወታደሮች ከአብዮት ጥበቃ አባላት ጋር በመሆን ተኩስ ከፈቱ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደቁ። አንዳንድ ቤተሰቦች በአንዲት ቅጽበት ብቻ ሁለት ወይም ሶስት ልጆቻቸውን አጥተዋል። በዚያው ፍጅቱ በተፈፀመበት ዕለት ማታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሬሳዎች ወደ ዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታል ሬሳ ማቆያ ክፍል ተላኩ። … ታዳጊ የሆኑ ወጣቶች፣ ገና ሃያ ዓመት ያልደፈኑ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ አረጋውያን፣ ፀጉራቸውን በአጭሩ የተቆረጡ፣ በወቅቱ አፍሮ የተባለ የፀጉር አቆራረጥና ሌሎችም ጉንጉን እየተባለ በሚጠራው ዓይነት ሐገራዊ የፀጉር አሰራር የተሰሩ ሴት ልጆች ሬሳ በየስፍራው ተዘርግቷል። አንዳንዶቹ ሱሪ ታጥቀዋል። ሌሎቹም ቀሚስ አጥልቀዋል።
አብዛኞቹ አስክሬኖቹ በጥይት ተበጣጥቀውና የአንዳንዶቹም ፊት ጨርሶ ስለተበላሸ ማንነታቸውን እንኳን ለመለየት ያስቸግር ነበር›› (የተሰመረበትን ልብ ይበሉ) (ያ ትውልድ ቅጽ ሶስት መፅሀፍ፤ ክፍሉ ታደሰ)
ታህሳስ 26/1985-ኢህአዴግ
‹‹በ24/04/85 ማታ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ መሆናቸው በዜና ማሰራጫዎች እንደተሰማ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ ወደ ኤርትራ ታዛቢዎችን ለመላክ የወሰኑትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ውይይት ጀመሩ። …የመጨረሻው የሰልፈኞች ረድፍ ከግቢው እንደወጣ ታጣቂ ኃይሎች ወዲያውኑ የዩኒቨርስቲውን በር ዘጉት። ወዲያውኑ ሰልፈኞቹን ከብበው የነበሩ የተለያዩ ታጣቂ ኃይሎች ተኩስ ከፈቱ። …ይበልጥ የሚዘገንነው ተራ ልብስ ለብሰው ተማሪ መስለው በዩኒቨርስቲው ውስጥ የተሰማሩት ታጣቂ ቡድኖች ነበሩ።
በዚህም የተነሳ በጠመንጃ በሽጉጥ፣ በጩቤና በዱላ ሰላማዊ ተማሪዎች፣ ሴቶችና ዓይነ ስውራን ሳይቀሩ፣ በሚዘገንንና ታይቶ በማይታወቅ ጭካኔ ተጨፈጨፉ። በሥራቸው ምክንያት በግቢው ውስጥ የተገኙ ወንዶችና ሴቶች መምሕራን፣ ሌሎች ሰራተኞችም የጭካኔው ጭፍጨፋ ደርሶባቸዋል። ከዚህ በኋላ የተፈጸመው ደግሞ የጭካኔውን እቅድና ኢሰብዓዊ መሠረት ያመለክታል።
1. በከባድ ሁኔታ በጥይት፣ በጩቤና በዱላ ተደብድበው የተጎዱና በጣም የሚደሙ ወጣቶች የሕክምና እርዳታ ወደሚያገኙበት እንዳይወሰዱ ተከለከሉ።
2. አምቡላንሶች ገብተው ቁስለኞቹን ወደ ሐኪም ቤት እንዳይወስዱ ታገዱ። 3. ከገቡም በኋላ ቁስለኞቹን ይዘው እንዳይወጡ ታገዱ።
4. ተኩስ በተከፈተበትና አምቡላንሶች እንዲወጡ በተፈቀደበት መሀከል ቢያንስ የሁለት ሰዓቶች ያህል ልዩነት ነበረ።
…መንፈሱ ይህ ከሆነ መንግስት የተማሪዎቹን የሰላማዊ ሰልፍ እቅድ ገና ከውጥኑ ያውቀው ነበር። ግልጽ ማስረጃውም መንግስት ከባድ ኃይል አዘጋጅቶ መጠበቁ ነው። ዋናው ጥያቄም የሚነሳው እዚህ ላይ ነው። አንደኛ፤ ያ ተዘጋጅቶ ይጠብቅ የነበረው ኃይል ተማሪዎቹ ከዩኒቨርስቲው ግቢ እንዳይወጡ ለምን አላገዳቸውም ነበር?...›› (የተሰመረበትን ልብ ይበሉ) (በወቅቱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ /ኢሰመጉ/ የተማሪዎቹን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ካወጣው መግለጫ የተወሰደ) 1997 እና 1998-ኢህአዴግ ኢሰመጉ እ.ኤ.አ. በታህሳስ 6 2005 ዓ.ም. ‹‹No Human Rights=No Democracy›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ‹‹በሰኔ ወር አጋማሽ መንግስት በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በወሰደው የአፈና እርምጃ ብዙዎች ሲገደሉ ከአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጐች ለእስር ተዳርገዋል›› ሲል በዛው ዓመት በጥር ወር ‹‹Human rights are not respected=There is no democracy›› በሚል ርዕስ ያወጣው መግለጫ ደግሞ ‹‹የመንግስት ሃይሎች ሰላማዊ ሰልፈኞቹን ለማስቆም ባደረጉት ሙከራ ሰላሳ አራት ሰዎች ተገድለው ስልሳ ሁለት የሚሆኑ ሲቆስሉ ሌሎች ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ዜጐች በተለያዩ ቦታዎች ለእስር ተዳርገዋል›› በማለት የወቅቱን ሁኔታ ያትታል።
…መንፈሱ ይህ ከሆነ መንግስት የተማሪዎቹን የሰላማዊ ሰልፍ እቅድ ገና ከውጥኑ ያውቀው ነበር። ግልጽ ማስረጃውም መንግስት ከባድ ኃይል አዘጋጅቶ መጠበቁ ነው። ዋናው ጥያቄም የሚነሳው እዚህ ላይ ነው። አንደኛ፤ ያ ተዘጋጅቶ ይጠብቅ የነበረው ኃይል ተማሪዎቹ ከዩኒቨርስቲው ግቢ እንዳይወጡ ለምን አላገዳቸውም ነበር?...›› (የተሰመረበትን ልብ ይበሉ) (በወቅቱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ /ኢሰመጉ/ የተማሪዎቹን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ካወጣው መግለጫ የተወሰደ) 1997 እና 1998-ኢህአዴግ ኢሰመጉ እ.ኤ.አ. በታህሳስ 6 2005 ዓ.ም. ‹‹No Human Rights=No Democracy›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ‹‹በሰኔ ወር አጋማሽ መንግስት በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በወሰደው የአፈና እርምጃ ብዙዎች ሲገደሉ ከአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጐች ለእስር ተዳርገዋል›› ሲል በዛው ዓመት በጥር ወር ‹‹Human rights are not respected=There is no democracy›› በሚል ርዕስ ያወጣው መግለጫ ደግሞ ‹‹የመንግስት ሃይሎች ሰላማዊ ሰልፈኞቹን ለማስቆም ባደረጉት ሙከራ ሰላሳ አራት ሰዎች ተገድለው ስልሳ ሁለት የሚሆኑ ሲቆስሉ ሌሎች ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ዜጐች በተለያዩ ቦታዎች ለእስር ተዳርገዋል›› በማለት የወቅቱን ሁኔታ ያትታል።
ከዚህ በተጨማሪም በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ዘርዝሮ ኢህአዴግ እና ሰብዓዊ መብት እንደማይተዋወቁ መሞገት ይቻላል። ሆኖም የቦታ ውስንነት ስላለ የኦጋዴን፣ የሲዳማ፣ የጋምቤላ፣ የኦሮሚያ፣ የጎራፈርዳ እንዲሁም በልማት ስም ያለአንዳች ካሳ እና ምትክ ቤት የሚፈናቀሉ ዜጎችን እንደማሳያ ልንወስድ እንችላለን። የሆነ ሆኖ ከነገ በስቲያ የሚከበረው የ‹‹ግንቦት ሃያ›› 21ኛ አመት በነፃ ፕሬስ፣ በመድብለ ፓርቲ ስርዓት እና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ሃያ አንድ አመት ወደኋላ ተጉዘን ከመሆኑም ባሻገር ህወሓት ‹‹በትግራይ ያለውን ጭቆና አስወግዳለሁ›› ሲል እንደተመሰረተው ሁሉ አብዛኛው የህወሓት መስራቾች ‹‹ህወሓት ጨቋኝ ነው›› ሲሉ ሌላ የትግራይ ህዝብን ከጭቆና ነፃ የሚያወጣ ድርጅት መስርተው፣ በትግል ላይ መሆናቸውን ስናይ ነው ህወሓትን እዚህ ለማድረስ የተሰዉት ሰማዕታት በሀገርም ሆነ በቤተሰቦቻቸው ዘንድ በዚህ በዓል በድል ሳይሆን በሀዘን እና በፀፀት ሊታወሱ ግድ ያለው።
‹‹ለህዝብ ጥቅም ሲባል…›› ኢህአዴግ እንደተቆጣጠረው የሰማነው የመንግስት ሚዲያም እንዲህ የአንድ ፓርቲ አገልጋይ መሆኑ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ሌላ ችንካር ነው። እናም መለስ በ1983 ዓ.ም. የሰኔ ኮንፈረንስ አንገታቸውን በኩራት ቀና አድርገው በተስፋ የተሞላ ዲስኩር እንዳሰሙት ሁሉ በዚህ ዘመን ስለዛሬይቱም ሆነ የወደፊቷ ኢትዮጵያ አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚናገሩበት ጀምበር እየጠለቀች ነው። ባለፈው ሳምንት በኃያላን ሀገራት መሪዎች ፊት ለፊት ሆነው ንግግራቸውን እያሰሙ ሳለ የመብረቅን ያህል አስደንጋጭ በሆነ ድምፅ እንዳቋረጣቸው ‹‹የነፃነት ድምፅ›› አይነት ብዙ ድምፆች ከየቦታቸው እየተሰሙ ነውና። ...ለዚህም መሰለኝ ‹‹እውነተኛው ግንቦት ሃያ ከወዴት ነህ?›› ሲል የሚጠይቅ የበዛው፡፡
No comments:
Post a Comment