Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Saturday, July 7, 2012

ከፖለቲካ ወገንተኝነት ያልፀዳው የስፖርት ውድድር

ከዛሬ 29 ዓመት በፊት የተቋቋመው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በየዓመቱ በሚያካሂደው ፌስቲቫል በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚያገናኝ መድረክ ነበር:: ድርጅቱ በየዓመቱ በሚያካሂደው ፌስቲቫል የኢትዮጵያን ባህልና ቅርስ ከማስተዋወቅ አልፎ ለኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ማኅበረሰብ አመቺ ከባቢዎችን በመፍጠር ረገድ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል::

የድርጅቱ ተልዕኮ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ማጠናከር፣ የቢዝነስ ማኅበረሰቡን መደገፍ፣ ለወጣቶች የስኮላርሺፕ ዕድል መስጠት ሲሆን፣ ይህንን ተልዕኮ ለማስፈጸምም የእግር ኳስ ውድድሮችን፣ ሌሎች የስፖርት ክንውኖችንና የባህል ዝግጅቶችን ያካሂዳል:: የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፌዴሬሽን ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖትና ከብሔር ወገንተኝነት የፀዳ፣ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚያስተናግድና የሚያሳትፍ ድርጅት ነበር:: 

ላለፉት 29 ዓመታት ኢትዮጵያውያንን ሲያገናኝና ሲያቀራርብ የኖረው ይህ የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአመራሮቹ መካከል በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት የአንድነት ሳይሆን የልዩነት ተምሳሌት እየሆነ መጥቷል:: በአመራሮቹ መካከል የተፈጠረው ልዩነት እየተካረረ ሄዶ ድርጅቱ ለሁለት የተከፈለ ሲሆን፣ የተለያየ ስያሜ የያዙት እነኚህ ማኅበራት ላለፉት 29 ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዋሽንግተንና በዳላስ የየራሳቸውን ፌስቲቫል አዘጋጅተዋል:: 

በዘር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይፈጥር ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በአንድ መድረክ ያገናኝ የነበረው የስፖርት ፌዴሬሽን፣ አመራሮቹ በፈጠሩት የፖለቲካ ሽኩቻ ምክንያት ለውድቀት ተጋልጧል:: ከአገርና ከወገን ርቀው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚገናኙበት ይህ መድረክ በጥቂት ግለሰቦች ፍላጐት ምክንያት ለሁለት መከፈሉ በርካቶችን አሳዝኗል:: አንዳንዶቹም ኢትዮጵያውያን መቼ ነው የምንስማማው? ሲሉ ይጠይቃሉ:: 

በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽን አመራሮች መካከል አለመግባባት የተፈጠረው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የኢሕአዴግ ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሼክ መሐመድ አል አሙዲ ፌዴሬሽኑን በገንዘብ መደገፍ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ቢሆንም፣ በአመራሮች መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ ወጥቶ የታየው ግን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ፌስቲቫል የክብር እንግዳ ሆነው በተጋበዙበት ጊዜ ነው:: 

የተወሰኑት አመራሮች ‹‹ድርጅቱ ከፖለቲካ የፀዳ በመሆኑ የፖለቲካ ሰዎችን መጋበዝ የለብንም›› የሚል አቋም ሲይዙ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከዚህ ቀደም የፖለቲካ ሰዎች ተጋብዘው የነበረ በመሆኑ ወ/ት ብርቱካን የክብር እንግዳ ቢሆኑ የሚያመጣው ለውጥ የለም የሚል አቋም ያዙ:: ወ/ት ብርቱካን እንግዳ ሆነው እንዲቀርቡ የፈለጉት የፌዴሬሽኑ የቦርድ አመራሮች ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ፌዴሬሽኑን የፖለቲካ መሣርያ እንዳደረገው ይገልጻሉ:: 

የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን አመራሮች በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት በውይይት መፍታት ባለመቻላቸው የተወሰኑ አመራሮች ራሳቸውን በማግለል ‹‹የሁሉም ኢትዮጵያውያን ስፖርት ማኅበር አንድ›› የሚባል ድርጅት አቋቋሙ:: የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት ይህ ድርጅት፣ በዋሽንግተን ዲሲ ከጁላይ 1 እስከ ጁላይ 7 የሚቆይ የስፖርት ፌስቲቫል ሲያዘጋጅ፣ የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የስፖርት ማኅበር በበኩሉ ዳላስ ላይ ከጁላይ 1 እስከ 7 የሚቆይ የስፖርት ፌስቲቫል አዘጋጅቷል:: 

ለማስታወቂያ ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንዳወጣ የሚነገርለት የሁሉም ኢትዮጵያውያን የስፖርት ማኅበር አንድ በተሳታፊዎች ድርቅ የተመታ መሆኑን ከስፍራው የሚወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ:: ታዛቢዎች እንደሚገልጹት፣ ተቀናቃኙ የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ማኅበር ያካሄደበት ዘመቻ ለተሳታፊዎች ቁጥር ማነስ ዋነኛ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም:: 

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባቀረበው ጥሪ ‹‹በዋሽንግተን ዲሲ የወያኔ መልዕክተኞች ትናንት ተቋቋምን ብለው ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር አውጥተው አዘጋጀን የሚሉትን ፌስቲቫል አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዳትተባበሩ ጥሪ እናደርጋለን:: 

በሚሊዮን ዶላር የተከራዩት ስታዲየም የሰዓት እላፊ የታወጀበት መንደር ሆኖ ጭር እንዲል እንድናደርገው እንጠይቃለን:: በአንፃሩ ወደ ዳላስ ቴክሳስ በማምራት ከጁላይ 1 እስከ 7 ቀን 2012 ድረስ በሚካሄደው የሁላችንም መገናኛ፣ መዝናኛና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ በሆነው 29ኛው ESFNA ፌስቲቫል ላይ በመሳተፍ በዓሉን የደመቀ እንድናደርገው እናሳስባለን፤›› ብሎ ነበር:: የሁሉም ኢትዮጵያውያን ስፖርት ማኅበር በበኩሉ ከፖለቲካና ከሃይማኖት ተፅዕኖ ነፃ የሆነና ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚያቅፍ ድርጅት መሆኑን፣ ተልዕኮውም በስፖርትና በባህል ላይ ብቻ የተኮረ መሆኑን ይገልጻል:: 

‹‹የሁሉም ኢትዮጵያውያን ስፖርት ማኅበር አንድ የእግር ኳስ ውድድርና የመዝናኛ ፕሮግራም በሰሜን አሜሪካ የሚካሄድ መሆኑን በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሲያበስር ደስታ ይሰማዋል:: ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን የሕዝብ ጥያቄ ለማርካት የውድድርና የባህል መሰባሰቢያ ድርጅቱ ምሥረታ እውን ሆኗል፤›› ይላል ጁላይ 1 ቀን 2012 የወጣው የማኅበሩ መግለጫ:: የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በአሜሪካ ያደረገው ጥሪ የሰመረለት ይመስላል:: ፌስቲቫሉ በተከፈተበት ዕለት ዋሽንግተን ወደሚገኘው ‹‹RFK›› ስታዲየም ያመሩ ኢትዮጵያውያን በጣም ጥቂቶች መሆናቸውን ከዩናይትድ ስቴትስ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ:: 

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ኢትዮጵያውያን በፌስቲቫሉ ላይ እንዳይሳተፉ ጥሪ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ፌስቲቫሉን ለማክሸፍም ሰላማዊ ሠልፍ ጠርቷል:: ዘ ሐበሻ የተሰኘው ድረ ገጽ እንዳስነበበው፣ በሼክ አል አሙዲ ከሚደገፈው ፌስቲቫል ይልቅ በዋሽንግተን ዲሲ ሠልፍ ላይ የነበሩት ሰዎች አካባቢውን አድምቀውታል:: ኢትዮጵያውያንን እንወክላለን የሚሉት ሁለቱ ማኅበራት በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በውይይት መፍታት ባለመቻላቸው ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት ይዘው እስከመሄድ ደርሰዋል:: 

ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረትም ከኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ተገንጥሎ ወጥቶ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ሰሜን አሜሪካ አንድ በሚል ስያሜ ሲንቀሳቀስ የነበረው ድርጅት ‹‹ESFNAONE›› የሚለውን ስያሜ እንዳይጠቀም፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን መፈክር የሆነውን ‹‹Bringing All Ethiopians Together›› የሚለውን መፈክር እንዳይጠቀም፣ እንዲሁም ከ‹‹ESFNA›› ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለውና ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት የስፖርት ውድድር አካሂዶ እንደማያውቅ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ፍርድ ቤቱ ወስኖበታል:: 

የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ለሁለት እስከተከፈለበት ጊዜ ድረስ ሼክ መሐመድ አል አሙዲ 700 ሺሕ ዶላር ለድርጅቱ ድጋፍ ማድረጋቸው ይነገራል::  የተወሰኑት የአመራር አባላት ከማኅበሩ ተገንጥለው ወጥተው አዲስ ድርጅት ካቋቋሙ በኋላም የሼኩ ድጋፍ እንዳልተለያቸው ይገለጻል:: ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ በጉጉት የሚጠብቁት የስፖርት ፌስቲቫል ከሃያ ዘጠኝ ዓመታት ጉዞ በኋላ ወደ ፖለቲካ ፌስቲቫልነት የተቀየረ መስሏል:: 

ፌስቲቫሉ የአንድነት ሳይሆን የልዩነት ተምሳሌት እየሆነ መጥቷል:: የአንድ አገር ዜጐች ልዩነታቸውን ወደ ጐን አድርገው በሚስማሙበት ጉዳይ ላይ ኅብር ይፈጥሩበት የነበረው ፌስቲቫል ዓላማውንና ተልዕኮውን እየቀየረ በመምጣቱ በዝግጅቱ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መጥቷል:: 

‹‹ኢትዮጵያውያን የምንስማማው መቼ ነው?›› የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል:: ኑሮአቸውን በዩናይትድ ስቴትስ የመሠረቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚዎች ችግሩ የተፈጠረው በመንግሥት በኩል መሆኑን ይገልጻሉ:: ሼክ መሐመድ አል አሙዲ እ.ኤ.አ ከ2005 ጀምሮ ለኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን የገንዘብ ድጋፍ መስጠት የጀመሩት ጠንካራውን የዳያስፖራ ኮሙዩኒቲ ለመቆጣጠር ታሳቢ በማድረግ መሆኑን እነኝሁ ወገኖች ያስረዳሉ:: 

በሼክ አል አሙዲ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ቡድን በየአውቶብሱና በምድር ውስጥ ባቡሩ በተከራየው ትላልቅ ማስታወቂያ ሰሌዳ በዋሽንግተን የሚያካደውን ፌስቲቫል ቢያስተወውቅም፣ በመክፈቻው ዕለት የተገኘው ሰው ቁጥር በጣም ጥቂት ነበረ:: አዘጋጆቹ በከፍተኛ ወጪ የተከራዩት ለከተማው ቅርብ የሆነው ‹‹RFK›› ስታዲየምም ኦና ሆኖ ነው ያሳለፈው:: ሪፖርተር ያነጋገረው አንድ በዋሽግንተን ዲሲ የሚኖር ኢትዮጵያዊ እንደገለጸው፣ በከተማው በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን የመኖራቸውን ያህል በዝግጅቱ የተሳተፉት ሰዎች ጥቂት ናቸው:: 

ፌስቲቫሉ በዋሽግንተን በተከፈተበት ዕለት በአሜሪካ የፖለቲካ ንቅናቄ የሚያካሂዱ የተቃዋሚ ኃይሎች ሰላማዊ ሠልፍ ያካሄዱ ሲሆን፣ ‹‹ሕዝብን ከሚያፍን መንግሥት ጋር የሚሠሩ ሰዎችና የንግድ ድርጅቶች ናቸው›› የሚል ተቃውሞ አሰምተዋል:: የዝግጅቱ አስተባባሪዎችም በሼክ አል አሙዲ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑን አልካዱም:: በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ‹‹ይህንን ዘግጅት ስፖንሰር ያደረጉልን ክቡር ሼክ መሐመድ አል አሙዲንን እናመሰግናለን፤›› ብለዋል::

 ጉዳዮን ጠለቅ ብለው የሚያውቁ ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የስፖርት ማኅበር አመራሮች መካከል የለው ልዩነት ጐልቶ የወጣው በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ምክንያት ቢሆንም፣ ከዚያ በፊት ሥልጣን በሌላቸው መሥራቾችና በአመራሮች መካከል ከባድ የሆነ የውስጥ ትግል ነበር:: ዋናው ችግራቸውም ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነበር:: በማኅበሩ አመራር አባላት መካከል የተፈጠረውን ሽኩቻ ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት በፌስቲቫሉ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያኖች ቁጥር በመጠኑ ቀንሶ ነበር:: 

ዘንድሮ በዳላስ ላይ እየተካሄደ ባለው ፌስቲቫል በርካታ ኢትዮጵያውያንና የንግድ ድርጅቶች ተገኝተዋል:: በአንፃሩ ከፍተኛ ገንዘብ በወጣበት የዋሽንግተኑ ፌስቲቫል ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው:: ዛሬ ማታ በሚካሄደው የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት የግራሚ አዋርድ ያሸነፉ አሜሪካውያን አርቲስቶች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎችም በዝግጅቱ እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል:: 

አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፣ በዋሽንግተን የተካሄደው ዝግጅት የድርጅቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመወሰን ደረጃ የራሱን ተፅዕኖ ይፈጥራል:: በየዓመቱ የሚካሄድን ፌስቲቫል በአንድና በሁለት ስፖንሰር ድጋፍ ብቻ ማካሄድ እንደሚከብድም እነዚሁ ታዛቢዎች ይገልጻሉ:: በተቃራኒው በዳላስ በተካሄደው ዝግጅት የመንግሥት ተቃዋሚ መሆናቸውን የሚነገርላቸው በርካታ ሰዎች ተሳታፊዎች ሆነዋል:: 

በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የንግድ ድርጅቶችም አንድ ድንኳን ለአንድ ሳምንት በሦስት ሺሕ ዶላር ተከራይተው ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅና በመሸጥ ላይ መሆናቸው ተሰምቷል:: በዚህ ምክንያት የዳላሱ ፌስቲቫል ውጤታማ ነው ማለት ቢቻልም፣ ይህንን ዝግጅት በመሩት የፌዴሬሽኑ አመራሮች መካከል ግን ነገ ልዩነት ስላለመፈጠሩ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም::

Source: Reporter News

No comments:

Post a Comment