Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Thursday, July 5, 2012

የማስተርስና የመጀመርያ ዲግሪ ያላቸው ዜጐች አዲስ አበባ ውስጥ የጐዳና ተዳዳሪ ሆነዋል

ኢሳት ዜና:- ሰኔ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ይህ የተገለፀው፤የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ትናንትና በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ካህሳይ ገብረመድህን እንዳሉት፤ በከተማው ያሉትን የጐዳና ላይ ተዳዳሪዎች ወደ መልካም ሕይወት ለመመለስ፣ አስተዳደሩ በማድረግ ላይ ባለው እንቅስቃሴ፤ መምህር፣ ነርሶችና በተለያዩ ሙያዎች የተመረቁ ዜጐች የጐዳና ላይ ተዳዳሪ ሆነው መገኘታቸውን አረጋግጧል፡፡


እነዚህን የተማሩ ዜጐች ለጐዳና ሕይወት የዳረጋቸውን ምክንያት በማጣራትና አስፈላጊውን የማስተካከያ ውሳኔ በማስተላለፍ ፤ቀድሞ ወደ ነበሩበት ሥራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም፣ አቶ ካህሳይ ገልጸዋል፡፡

አስተዳደሩ በጐዳና ላይ የሚኖሩትን ዜጐች ለማቋቋምና ሥራ በመፍጠር ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ፣ በአራት ዙር ከሰባት ሺሕ በላይ የጐዳና ተዳዳሪዎችን  በኮብል ስቶን ሥራ፣ በጥቃቅንና አነስተኛና በመሳሰሉት ዘርፎች ለማሰማራት ባደረገው ጥረት፤ አስደሳችና አሳዛኝ ገጠመኝ እንዳለው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

እንደ ሪፖርተር ዘገባ፤የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለጊዜው ቁጥራቸውን በውል አላውቀውም ቢልም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ጎዳና ላይ ይኖራሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ ገበታቸው የተፈናቀሉ፣ በተለያዩ ሱሶች የተለከፉና በሕመም ምክንያት ሥራቸውን ማከናወን ያልቻሉ የመጀመርያና የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች ፤መኖሪያቸውን ጎዳና ላይ አድርገዋል፡፡

ቢሮው በሥሩ በተዋቀረው የማኅበራዊ ችግሮች፣ መንስኤዎች መከላከልና ተሃድሶ ዋና የሥራ ሒደት  አማካይነት፤በከተማው ውስጥ ያሉ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በተመለከተ ያደረገው ጥናት ቢጠናቀቅም፣ ምን ያህል ምሩቃን ጎዳና ላይ እንዳሉ ውጤቱን ይፋ አለማድረጉ ታውቋል፡፡

ጋዜጣው፦ በባለፈው ሳምንት እትሙ “የትምህርት ፖሊሲው ምን እያፈራ ነው? ድንጋይ ጠራቢ? ወይስ ባለሙያ?”በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሁፍ -<ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች  በመጀመሪያ ዲግሪ እየተመረቁ የሚወጡ ወጣቶች በድንጋይ ማንጠፍ ሥራ መሰማራታቸውን  ኢቲቪ እንደ ስኬት አድርጎ በተከታታይ መዘገቡ እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ እንደሆነ>  አጠንክሮ ተችቷል። የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እና ምሁራን ፤በኢትዮጵያ እጅግ እያሽቆለቆለ ለመጣው የትምህርት ጥራት፤  ገዥውን ፓርቲ ሲከሱ ይደመጣሉ።

እነዚህ ወገኖች፤ለፖለቲካ ትርፍ በሚል ስሌት፤ ብዛትና ሽፋን ላይ ብቻ በማትኮር የትምህርት ጥራትን መግደል፤ትውልድን እና አገርን እንደመግደል ነው በማለት ለዓመታት ሲያሣስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment