ኢሳት ዜና:- ዓለም-አቀፉ የስራ ድርጅት ወይም ILO ኢትዮጵያ የሠራተኞች መብትና ጥቅም ባግባቡ ከማይከበርባቸው
የዓለማችን አገሮች ከዋነኞቹ ረድፍ የምትመደብ መሆኗን አስታወቀ።
ድርጅቱ ይህንኑ አስመልክቶ ሰሞኑን ያወጣው ሪፖርት
እንደሚጠቁመው አርጀንቲና፣ ካምቦዲያ፣ ኢትዮጵያ፣ ፉጂ እና ፔሩ የሰራተኞችን መብት የሚጣስባቸው የዓለማችን አገሮች
ናቸው በማለት ይኮንናቸዋል።
ድርጅቱ ለዚህ እንደምሳሌ የጠቀሰው በገዥው ፓርቲ ጣልቃ ገብነት ዳግም የተቋቋመውን ተለጣፊውን የኢትዮጵያ የመምህራን ማህበር ሲሆን፣ ማሕበሩ ምንም እንኳን ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ የILO አባል ለመሆን ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ተለጣፊ ማሕበሩ በመንግስትም ሆነ በግል መምህራን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ለመሆኑ፣ እንዲሁም የመምህራኑን መብት በትክክል ለማስከበር የተቋቋመ ሆኖ ለመገኘቱ ሙሉ ማረጋገጫ ማግኘት ባልመቻሉ የአባልነት ጥያቄው በዓለም አቀፉ ድርጅት ዘንድ እስካሁን ድረስ ተቀባይነት ሊያገኝ አለመቻሉን ገልጿል።
እንደሚታወቀው ከተመሰረተ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረውና በመምሕራኑ ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ የመምህራን ማህበር በተለይም በወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን መንግስት ከፍተኛ ጫና ያደርግባቸው ከነበሩት የሲቪክ ተቋማት የመጀመሪያው ሲሆን፣ የማህበሩ ዋና ፀሃፊ የነበሩት አቶ አሰፋ ማሩ በገዥው ፓርቲ ታጣቂዎች ባደባባይ መገደላቸው፣ እንዲሁም አሁን በስደት የሚገኙት የማህበሩ የቀድሞ ሊቀመንበር ዶ/ር ታዬ ወልደ ሰማያት ደግሞ በፈጠራ ክስ ተወንጅለው የ18 ዓመታት ጽኑ እስራት ከተፈረደባቸው በኋላ፣ በዚህ ጉዳይ በመንግስት ላይ በደረሰበት ከፍተኛ ጫና ከ6 ዓመታት የእስር ቤት ስቃይ በኋላ በነፃ መለቀቃቸው የሚዘነጋ አይደለም።
በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተሰማርተው ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት እየጣሩ የሚገኙ መምህራን፣ የኢህአዴግ አባል ለመሆን ፈቃደኛ አልሆናችሁም፣ ከሌሎች የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና አባላት ጋር ትሰራላችሁ፣ የራሳችሁን የፖለቲካ አመለካከት ታራምዳላችሁ እየተባሉ ከፍተኛ ወከባና ማስፈራሪያ ብቻ ሳይሆን ከስራቸው ያለአግባብ እየተፈናቀሉ መሆናቸውን በተደጋጋሚ በኢሳት መዘገባችን ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment