Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, July 15, 2012

ሕዝብ ተገፋ! ተጠያቂነት ጠፋ!

በየስብሰባው፣ በመገናኛ ብዙኅን፣ በዓመታዊ ሪፖርት፣ ወዘተ በተደጋጋሚ የምንሰማው ይህ ተከናወነ፣ ይህ ተሠራ፣ ይህ ተሳካ፣ አንዳንድ መጠነኛ እንቅፋት ቢያጋጥምም አበረታች ነበር፣ ወዘተ የሚል ነው፡፡

የተሳካና የተፈጸመ ነገር የለም አንልም፡፡ አለ፡፡ ነገር ግን ተደናቅፎ ስለቀረው፣ ሳይሳካ ቀርቶ ገንዘብ ስላከሰረው፣ ሲጠበቅ ስለነበረውና ሥራ ላይ ሳይውል ስለቀረው ልማትም ሆነ ሌላ ጉዳይ አንሰማም፡፡ በተለይ በተለይ ለተሰጣቸው ሥራ ኃላፊነት ወስደው ሳይፈጽሙ በመቅረታቸው፣ አገርና ሕዝብ እንዲጐዳ ያደረጉ መሥርያ ቤቶችና ግለሰቦች ተጠያቂ ሲሆኑ አይነገረንም፡፡


በአጭሩ፡- ተጠያቂነት እየጠፋ ነው፡፡
ይህን ያህል ቢሊዮን የሚፈጅ ኢንቨስትመንት በዚህ ዓመት ተመዘገበ፣ ፈቃድ ተሰጠው የሚል እንሰማለን፡፡ ነገር ግን ያ የተመዘገበው ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ አይውልም፡፡ አንዳንዱ ተመዝግቦ ብቻ የውኃ ሽታ ይሆናል፡፡ አንዳንዱ ግንባታ ጀምሮ ሊያጠናቅቅ ሲል ኤሌክትሪክ የለም ሲባል መክኖ ይቀራል፡፡ አንዳንዱ በሕገወጥ መንገድ እንዲቆም ይደረጋል፤ አቤት ቢልም ሰሚ የለም፡፡

አንዳንዱ ድሮውንም አጭበርባሪ እንጂ ኢንቨስተር አይደለም፤ የባንክ ብድር ወስዶ በዚያው ይጠፋል፡፡ ምክንያቶቹ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ተስተጓጉለው ስለቀሩት ግን አይነገረንም፡፡ ተጠያቂነትም የለም፡፡ የሚነገረው በባለሀብት ችግር ስለተደናቀፈው እንጂ በመንግሥት አካላት ስለተደናቀፈው አይደለም፡፡

ምናልባት እዚህ ላይ ብዙ ተቃራኒ ሐሳቦች ይቀርቡ ይሆናል፡፡ ሥራ ላይ ያልዋሉትን፣ እናለማለን ብለው ያላለሙትንና አጥረው ያስቀሩትን መንግሥት እየቀማ አይደለም ወይ የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ ይችላል፡፡ መልሳችን ግን ግልጽ ነው፡፡ በመርህ ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ ሳይሆን ‹‹እንደ ሰው›› የተለያየ ነው፡፡ 

ጨርሶ ሳያለማ የተቀመጠ የሚፈራ ሆኖ ይታያል፡፡ ለምን አጥረህ ተቀመጥክ በማለት እኩል ከመዳኘትና በእኩል ዓይን ከማየት ይልቅ፣ ከአጥርም አጥር ይመረጥና ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ አጥር›› እና ‹‹ልማታዊ አጥር›› ተብሎ ይለያል፡፡ ደፈር ያለና ለምን እንዲህ ሆነ የሚል ካለም ባለ አጥሩ ደፋር ሆኖ የመንግሥት አካል ግን ፈርቶ ሲለማመጥ እናስተውላለን፡፡ በመርህ ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ ሳይሆን ‹‹ገጠመኝ›› እና ‹‹እንደ ገንዘቡ›› ሆኗል፡፡

ልማት ሊካሄድ ነው ሲባል ለልማት የሚሆን መሬት ይሰጣል፡፡ ለልማት የሚሆን መሬት ሲሰጥ አርሶ አደሩ ካሳ ተሰጥቶሃል ተብሎ በብዛት ይነሳል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አርሶ አደሩ በካሳ ያገኛትን ገንዘብ ይጨርስና ጐዳና ላይ መዋል ይጀምራል፡፡ መሬቱም ወይ አልተገነባበት ወይ የመስኖ እርሻው እንዳይቀጥል ተደርጓል፡፡ ታጥሮ በቀረው መሬት ምክንያት በመጨረሻ ልማት አይኖርም፤ አርሶ አደሩም ተፈናቅሎ የትም ይወድቃል፡፡ ይህ ድርብ ጉዳት ይሆናል፡፡

ለልማት ከተመደቡ መሬቶችና ዕቅዶች 70 በመቶ ያህሉ ከልማት ተስተጓጉለው የሚቀሩበት ሁኔታ በአንዳንድ አካባቢዎች በግልጽ እየታየ ነው ያለው፡፡

ይህ ችግር ለመኖሩ ልዩ ጥናትና ምርምር የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ ዞር ዞር ብሎ አካባቢን ማየት ብቻ ይበቃል፡፡ ባለሀብቶችን ሰብስቦ ችግሩ ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ብቻ ጉዱን ዘክዝኮ ያወጣዋል፡፡ ችግሩ ተነግሯል፡፡ በሚገባ ተዘርግፏል፡፡ ችግሩ ያለው ግን ችግሩን የሚያውቀው የሚመለከተው መሥርያ ቤትና ባለሥልጣን ዕርምጃ ባለመውሰዱ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር አቤት የሚባልበት ቦታ አለመኖሩ ነው፡፡ መብት ሲረገጥ አቤት ቢባል ‹‹ጥሪ አይቀበልም›› ይሆናል መልሱ፡፡ እንባ ይፈሳል ‹‹ሶፍት›› የሚያቀብል እንኳን የለም፤ እንዳይፈስ የሚጠብቅ ይቅርና፡፡

አንዳንድ ጊዜ የመሥርያ ቤቶች ችግር፣ ጣጣና ፍዳቸው ወደ ሕዝቡ ሲወረወር ይታያል፡፡ ሹሙ ግምገማ ላይ ስለሆኑ፣ ከዕረፍታቸው አልገቡም እየተባለ ለወራትና ለዓመታት ውሳኔ አጥተው የሚንገላቱ የሕዝብና የልማት ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡ ጉዳዩን የሚያውቅ ሹም ተቀየረ ተብሎ አዲስ መጪው እስኪለምድ ድረስ እየተባለ፣ ለጉዳዩ መፍትሔ የሚሰጥ ጠፍቶ ልማት ተሰናክሎ ሲቀር በግልጽም በብዛትም እየታየ ነው፡፡

ጉቦ አልሰጥም በማለቱ አንተማ የእኛ አይደለህም ተብሎ የሚበደለው በርካታ ወገን እንዳለ ሆኖ፣ በአቅም ማነስ ብቻ ውሳኔ የሚሰጥ ጠፍቶ እየደረሰ ያለው የልማት መደናቀፍም በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡

ልማት ሲስተጓጐል ባንኮች ያበደሩትን አያስመልሱም፡፡ በልማት አማካይነት ሊያገኙት ያሰቡትን ጥቅም አጥተው ወደ ሐራጅ ሲሯሯጡ ይታያል፡፡ ባለሀብት አልምቼ አገር ጠቅሜ ራሴም እጠቀማለሁ ብሎ ያቀደው ህልም ተጨናግፎበት ሲያለቅስ ይስተዋላል፡፡ ከውጭ የመጣ ኢንቨስተር ከደላላ ጋር ክርክር ገጥሞ በየፍርድ ቤቱ ሲንገላታ ይታያል፡፡ ሥራ አገኛለሁ ብሎ ተስፋ ያደረገ ወገን ፋብሪካው ሥራ አልጀመረም፣ ተዘግቷል፣ ግንባታው ተቋርጧል፣ እየተባለ ተስፋው ሲሟሽሽ ይገኛል፡፡ በየኢንቨስትመንት መሥርያ ቤቶች የተመዘገቡት አኅዞች ፌዝ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ጥብቅና ፈጣን ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ በተለይም በእርሻና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ምን ያህል ኢንቨስተሮች ተመዘገቡ? ምን ያህሎቹ ሥራ ጀመሩ? የሚለውን በግልጽ ጥናት ሊያካሂድበትና ሊያውቀው ይገባል፡፡ በአኅዝና በተገኘው ገንዘብ ልክ በሚገባ ሊያውቀው ግዴታ አለበት፡፡ በባንክ፣ በሥራ ዕድል፣ በውጭ ምንዛሪና በአጠቃላይ በልማት ላይ ያስከተለውን እንቅፋትና ጫና ሊረዳውና ለሕዝብ ግልጽ ሊያደርገው ይገባል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአንድ የኢንዱስትሪ አካባቢ 29 በመቶ የሚሆነው ብቻ ሥራ ላይ ውሎ 71 በመቶ መክኖ ቆሞ የቀረበት ሁኔታ ይታያልና፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ግንባታ የተካሄደባቸው የልማት ሥራዎች ሊቋረጡ አይገባም ብለው በግልጽ ለሕዝብ ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ግንባታ ተካሂዶባቸውና ማሽኑም መጥቶላቸው ተገጣጥመው ሥራ ሊጀምሩ ሲሉ፣ ምክንያቱ ሳይታወቅ አቁሙ ተብለው ሁሉም ነገር ቆሞ ሲቀር ግን፣ ለምን ብሎ የሚጠይቅ የመንግሥት መሥርያ ቤት እንኳ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ጥፋት የፈጸመን መሥርያ ቤት ወይም ግለሰብ ለይቶ በማወቅ ተጠያቂ ማድረግ ይቅርና ለሙከራ ያህል እንቅስቃሴ ሲደረግ እንኳን አይታይም፡፡ አይሰማም፡፡

በአጠቃላይ የለማውን ብቻ እያየን የተደናቀፈውን ለማየት ዓይናችን ተከልሏል፡፡ ጥቂት የተጠቀመ አድናቂና አሞጋሽ ሲነገርለት እንጂ ተበድሎ እንባ የሚያፈሰው አልሚ ወገን አድማጭና እንባ አባሽ ተነፍጓል፡፡ በአጠቃላይ አገራችን ልትጓዝበት በምትችለው የልማት መንገድ ላይ ጉቦ፣ አቅም ማነስ፣ የተጠያቂነት መጥፋትና ከፍተኛ ፀረ ልማትነት እንቅፋት እየፈጠሩ ናቸው፡፡

Source Reporter: ተጠያቂነት ጠፋ! ሕዝብ ተገፋ!

No comments:

Post a Comment