Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, July 18, 2012

የአቶ መለስ የጤንነት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል

ኢሳት ዜና:- ሐምሌ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ላለፉት 2 ሳምንታት የኢትዮጵያውያንን ትኩረት ስቦ የቆየው የአቶ መለስ ዜናዊ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ የመከላከያ፣ የፖሊስ እና የደህንነት አባላት ማንኛውንም እንቅስቃሴ በንቃት እንዲከታተሉ ታዘዙ::

 የኢሳት የአዲስ አበባ ዘጋቢ አንድ የፌደራል ፖሊስ የአመራር አባልን በመጥቀስ እንደዘገበው  የፌደራል ፖሊስ እና የደህንነት አባላት የአቶ መለስን የጤና ሁኔታ ተከትሎ በዋና ከተማዋ ወይም በዋና ዋና የክፍለሀገር ከተሞች ሊነሱ የሚችሉ ችግሮችን በፍጥነትና በቅልጥፍና መቆጣጠር የሚያስችል ” የአንድ ለአምስት” የጥቃት አመካከት ስልት ተግባራዊ እንዲሆንና ፖሊሶችም በዚሁ መሰረት ልምምድ እንዲጀምሩ ትእዛዝ ተላልፎአል።


በአሁኑ ጊዜ በአቶ መለስ ዜናዊ የተፈጠረውን የስልጣን ክፍተት ለመሙላት አቶ ስዩም መስፍን በዋና ተዋናይነት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ዘጋቢያችን ገልጧል። በህወሀት መንደር ውስጥ ያለው ግራ መጋባት እንደቀጠለ ባለበት በዚህ ወቅት፣  አቶ ስዩም ዋና ዋና የሚባሉ ነባር የህወሀት ካድሬዎችንና የመከላከያ አመራሮችን በማግኘት አገር የማረጋገቱን ስራ እንዲሰሩ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው ።

ለሳምንታት ዝምታን መርጠው የቆዩት የዲፐሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትም የስልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር በሚል ከመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ከአንዳንድ የተቃዋሚ ድርጅት አመራሮች ጋር መነጋገር መጀመራቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የአቶ መለስ ህመም ለህይወት አስጊ መሆኑን አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን መዘገብ የጀመሩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ዛሬ ሊሰጠው አቅዶ የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰርዟል። ይሁን እንጅ አቶ በረከት የአቶ መለስን መታመም ለኤኤፍ ፒ አረጋግጠዋል። ኤኤፍ ፒ አንድ ዲፕሎማትን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የአቶ መለስ የጤና ሁኔታ እጅግ አሣሳቢ  ደረጃ ላይ ደርሷል። አቶ በረከት ግን አቶ መለስ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አቶ ሽመልስ ከማል ሰሞኑን ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ” እንዲህ አይነቱን ወሬ የሚያስወራው ውሸት መፈብረክ ባህሪው የሆነው ድርጅት ነው” በማለት ኢሳትን መክሰሳቸው ይታወሳል። መንግስት፤ የአቶ መለስን መታመም ያመነው፤ከሁለት ቀናት በፊት አዲስ አበባ በተካሄደው በ 19 ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት በምስጢር የተያዘውን የመለስ መታመም ጉዳይ በአደባባይ ይፋ ካደረጉት በሁዋላ ነው።

ሪፖርተር ዛሬ ባወጣው ዘገባ ደግሞ አቶ መለስ የውጪ  ህክምናቸውን ጨርሰው  በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ  ይመለሳሉ፣  ይሁንና  ወደ አገራቸው ቢመለሱም በቶሎ ሥራ አንደማይጀምሩ ገልጧል።

አቶ መለስ በከባድ ህመም እየተሰቃዬ እንደሚገኙ በርካታ ሚዲያዎችና ድረ-ገፆች በቤልጅየም  ህክምና ከሚከታተሉበት  የሴንት ሉክ ሆስፒታል የሚገኙ ምንጮችን እየጠቀሱ  በዘገቡበት  በአሁኑ ወቅት፤  ዘግይቶ ስለ መለስ ጤንነት ሁኔታ የዘገበው ሪፖርተር ፦”ለ21 ዓመታት ያለዕረፍት ከፍተኛ የአገር ኃላፊነትን ሲወጡ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሕመማቸውም ምክንያት ካለባቸው የሥራ ጫና ብዛት የመጣ መሆኑ ተጠቁሟል” ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተወሰኑ ጊዜያት ካለባቸው ከባድ ኃላፊነት ርቀው ዕረፍት እንዲያደርጉ በሐኪሞቻቸው መመከራቸውን ምንጮች አክለው እንደገለጹለትም ጋዜጣው ጠቁሟል፡፡
]
ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቶ መለስን በሚታከሙበት ሆስፒታል ሄደው እንደጎበኟቸው የጠቀሱት የጋዜጣው ምንጮች፤ አምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስ እስካሁን ድረስ ከጎናቸው ሆነው እያስታመሟቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ጋዜጣው፤በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ግርማ ብሩ፣ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሥዩም መስፍን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚታከሙበት ቦታ ሄደው እንደጎበኛቸው  አመልክቷል።

ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉት የግንቦት7 ራዲዮ ዘጋቢዎች ግን አቶ መለስ አሁንም እጅግ አደገኛ በሆነ የጤና ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ፣ ወደ ኢትዮጵያም አለመመለሳቸውን ገልጠዋል።
የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ አቶ መለስ  ህክምናቸውን ከሚከታተሉበት ከቤልጅየም ሆስፒታል ወጥተው ከትናንት በስቲያ ምሽት አዲስ አበባ እንደገቡ ገልጦ ነበር።

ኢሳት ዛሬም ሴት ሉክ ሆስፒታል በተደጋጋሚ ቢደውልም፣ የአቶ መለስ ስም በበሽተኞች ስም ዝርዝር ውስጥ የለም የሚል መልስ አግኝቷል። ሁሉም የሆስፒታሉ ሰራተኞች የአቶ መለስን ስም ሲሰሙ  ወዲያውኑ “እዚህ የሉም” የሚል መልስ መስጠታቸው፣ የሆስፒታሉ ሰራተኞች በጥየቃ መሰላቸታቸውን ወይም ሆን ብለው መረጃውን እየደበቁ መሆናቸውን ያመለክታል በማለት የኢሳት ዘጋቢ ገልጧል።
ባለፈው እሑድ  በአዲስ አበባ በይፋ በተከፈተው 19ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያ  በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ተቀዳ ዓለሙ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ልዩ አማካሪ በአቶ ንዋይ ገብረ አብና በአምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ መወከሏ ይታወቃል።

ይሁንና አቶ መለስ ድነው ተመለሱም አልተመለሱም ከእንግዲህ ባላቸው የስልጣን ሀላፊነት ሊቀጥሉ እንደማይችሉ ሁሉም ወገን ያወቁት እና ያመኑበት ጉዳይ ሆኗል። ለዚህም ይመስላል ሪፖርተር በዚሁ ዘገባው፤ ስለተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዳይ ፤የህግ ባለሙያዎችን ማነጋገሩን ገልጿል።

“የሕግ ባለሙያዎች ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ -ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተክቶት  ይሠራል፣ ይህ የሚሆነው ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምፅ ያለው የፖለቲካ ድርጅት በምትኩ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከሚመርጥ ድረስ ነው” እንዳሉት ጋዜጣው ጠቁሟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በ5ኛው የአፍሪካና የቻይና የትብብር ጉባኤ ላይ ለመገኘት አቶ ሀይለማርያም ወደ ቻይና አቅንተዋል። አቶ ሀይለማርያም አቶ መለስን በመተካት ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። አቶ መለስ ካይሮ ውስጥ ተደርጎ በነበረው  የ4ኛው የአፍሪካና የቻይና ጉባኤ ላይ ተገኝተው እንደነበር ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment