ኢሳት ዜና:- ሐምሌ ፳ (ሀያ)ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
የአቡነ ጳውሎስ 20ኛ ዓመት በዓለ-ሲመት ሐምሌ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ምሽት በሼራተን አዲስ
ለሁለተኛ ጊዜ በተከበረበት ጊዜ ይፋ የሆነውንና በፓትርያርኩ ስም በ 200 ሚሊዮን ብር ወጪ ሊገነባ የታሰበውን
ሆስፒታል በበላይነት እየተቆጣጠሩ እንዲያስፈፅሙ ነው ሚኒስትር ቴዎድሮስ የተሾሙት።
በዚሁ በሸራተን በተካሄደው የፓትርያርኩ በዓለ-ሲመት ዝግጅት ላይ፤ የክብር እንግዳ የነበሩትን ምክትል ጠቅላይ
ሚኒስትሩን አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን እና ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖምን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት
ታድመዋል።
ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ ታዋቂ ሰዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እጅግ በርካታ እንግዶች በታደሙበት
በዚህ ዝግጅት ላይ የተደረገው የራት ግብዣ የተዘጋጀውም፤ በፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት እና “ራእይ ለትውልድ” በተባለ
አካል ነው ።
ለበዓለ ሢመቱ ለኅትመቶች፣ ለቲ- ሸርቶች፣ ለፖስተሮችና ለራት ግብዣው ዝግጅት ጭምር ወጪ የሆነው፤ ከፓትርያሪኩ ጽህፈት ቤትና “ከስፖንሰር ሽፕ “ ነው መባሉ ተሰምቷል።
አዘጋጆቹ አካል ፤በበዓሉ ሰበብ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከሚሰበሰበው ገንዘብ፤ ሕገ ወጥ ጥቅም እያጋበሱ
መኾኑ ታውቋል ያለው ደጀ-ሰላም፤ ይህም የበዓሉን ምንነትና ፋይዳ አደናጋሪ መልክ አስይዞታል ብሏል።
እንደ ድረ-ገፁ ዘገባ ፤አቡነ ጳውሎስ- ራዕይ ለትውልድ ከተባለው ድርጅት ጋር ግንኙነት የፈጠሩት፤ በቤተ-ክርስቲያን በማይታወቀው የልዩ ፅህፈት ቤታቸው መዋቅር አማካይነት ነው ። ፓትርያርኩ፤ ከተጠቀሰውና 20ኛ ዓመት በዓለ ሲመታቸውን ካከበረላቸው ድርጅት ጋር በሥራ ስም የጥቅም ግንኙነት
እንዲፈጥሩ ጉልህ ሚና የተጫዎቱትና አሁንም እየተጫዎቱ ያሉትም፤ እነ ወይዘሮ እጅጋሁ በየነ መሆናቸውም ተነግሯል።
በሸራተኑ ዝግጅት ላይ በአቡነ ጳውሎስ ስም የተሰየመ የኤድስ፣ የቲቢ እና የካንሰር ሕሙማን ማገገሚያ ማእከል
በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚገነባና የግንባታ ሥፍራውን የማፈላለግ ሥራ እየተሠራ መኾኑ የተገለጸ ሲሆን፤የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ የማዕከሉን ግንባታ በበላይነት እንዲቆጣጠሩ አቡነ ጳውሎስ ሾመዋቸዋል።
ከዚህም ባሻገር የአቡነ ጳውሎስን ሥራዎች ይዘክራል የተባለ የኻያ አምስት ደቂቃ ፊልም ለዕይታ በቅቷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኀይለ ማርያም ደሳለኝ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር
“ክቡርነታቸው በሀገራችን የልማት ጉዳይ ከመንግሥት ጋራ እየሠሩ መኾኑን እንገልጻለን፤ . . . የአክራሪነትን
አደጋ በተመለከተ መንግሥታችን ፤እዚህ ከተገኙትም፤ ካልተገኙትም የሃይማኖት ተቋማት ጋራ አብሮ ይሠራል” ብለዋል።
ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማስከተልም የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች
ፅህፈት ቤት እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ባደረጉት ንግግር፤ ፓትርያርኩ በኢትዮጵያ
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባላቸው የሊቀ መንበርነት ሓላፊነት ፤ለሰላም አብረዋቸው መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ
ገልጸዋል።
የ“ራእይ ለትውልድ” የተሰኘው ተቋም ተወካይም ደግሞ፦ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የኦርቶዶክሳውያን ብቻ
ሳይሆኑ፤ የመላው ኢትዮጵያውያን አባት ናቸው፤ በስማቸው የኤድስ፣ የካንሰር እና የቲቢ ማገገሚያ ማእከል ለመገንባት
የዲዛየን ሥራው ተጠናቋል” ብለዋል።ማዕከሉ በ200 ሚልዮን ብር እንደሚገነባና ለመሠረት ሥራው ብቻ አምስት መቶ ሺሕ ብር እንደሚያስፈልግ ተወካዩ ገልፀዋል።
በመቀጠልም አቡነ ጳውሎስ ፦ “ራዕይ ለትውልድ በስማችን የተሰየመውን ማእከል ለመገንባት መነሣቱ የሚመሰገን
ነው፤ ማእከሉን ሁላችንም እንደምንጠቀምበት ማሰብ አለብን፤ እግዚአብሔር አምላክ ለመልካም ሥራ ሁሉ እንድንተባበር
አዞናል፤ በስሜ ለተሰየመው ማእከል ግንባታ የበላይ ተቆጣጣሪ እንዲኾኑ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተሾመዋል” ብለዋል።
በዚህን ጊዜ ማዕከሉን እንዲመሩ በፓትርያርኩ የተሾሙት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኀኖም፦ “የተሰጠኝን ሓላፊነት አልቀበልም አልልም፣ እቀበላለኹ፤ ከራእይ ለትውልድ ጋራ አብሬ እሠራለኹ፡፡” በማለት ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment