ኢሳት ዜና:- ሰኔ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
በአንዋር መስጊድ ለጁማ ሶላት የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን ጥያቄያቸውን በጽናት እና በቁጭት አቅርበዋል። ድምጻችን ይሰማ፣ መጅሊስ አይወከለንም፣ ምርጫው በመስጊዳችን ይሁን፣ ህገ መንግስቱ ይከበርና የመሳሰሉትን መፈክሮች አሰምተዋል። መንግስት መጪው የመጂሊስ ምርጫ በቀበሌ እና በመስተዳድር ቦታዎች እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ምርጫው በቀበሌ መሆኑ፣ የኢህአዴግ ደጋፊዎችና ተማኞችን መልሶ ወደ መጅሊስ አመራር የሚመጣ ነው በማለት ይቃወማሉ። በዛሬው ተቃውሞ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ተገኝተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በስዊድን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሙስሊሙን ጥያቄ በመደገፍ የተቃውሞ ሰልፍ አደርገዋል።
በስቶኮልምና አካባቢዋ የሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ዛሬ፣ ሰኔ 22፣ 2004ዓም ባዘጋጁት ሰልፍ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን የተገኙ ሲሆን ፣ ሙስሊሞቹ መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆም፣ በአወልያ የተጀመረውን የመብት ጥያቄ እንዲመልስ እንዲሁም የአህባሽ አስተምህሮ እንዲቆም ጠይቀዋል።
ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ያነሱት የመብት ጥያቄ ህገመንግስታዊ በመሆኑ መንግስት አፋጣኝ መልስ እንዲሰጥ ያ ካለሆነ ግን በጥያቄያቸው እንደሚገፉበት ተናግረዋል። የሙስሊሙ ተወካይ “አገር ማለት በቋንቋ፣ በባህል፣ በተስፋ፣ በደስታና በመከራ ተሳስሮ የሚኖር ህዝብ የያዘች፣ ፍቅሯ በአጥንትና በስጋ ገብቶ የማይደመሰስ እናት ናት” በማለት ተናግረው፣ ነብዩ ሙሀመድ በመከካለኛው ምስራቅ አካባቢ ፍትህ በጠፋበት ወቅት የተከታዮቻቸውን ህልውና ለማስጠበቅ ይችሉ ዘንድ ወደ አገራችን እንዲሰደዱ አዘዋቸዋል ” በማለት አስታውሰዋል።
በወቅቱ አገራችን የተመረጠችበት ዋናው ምክንያት የነበረው አስተዳደር ፍትሀዊ መሆኑ ነው ያሉት ተወካዩ ፣ በዚህ የታሪክ ስደት አገራችን የመጀመሪያዋ የስደተኞች አገር ብቻ ሳትሆን፣ ሀሳብን የመግለጽ፣ የእምነት ነጻነት ተዘርቶ የበቀለባት፣ ያበበባት፣ ያፈራባት አገር ያዳርጋታል ብለዋል። ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ያነሱትን የመብት ጥያቄ በመደገፍ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያንም በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ተገኝተዋል።
No comments:
Post a Comment