Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Friday, June 29, 2012

ከሳሾቼ እንድጠጣው የሚፈልጉትን የግፍ ጽዋ በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ሲል አቶ አንዱአለም አራጌ ተናገረ

ኢሳት ዜና:- ሰኔ ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
የአንድነት ፓርቲ ም/ል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆነው አቶ አንዱአለም አራጌ ይህን የተናገረው ፣ የጥፋተኝነት ውሳኔ ለማስተላለፍ ዛሬ በዋለው ችሎት ላይ ነው። የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ የተከታተለው ዘጋቢያችን  እንደገለጠው  የከፍተኛው  ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት በሽብር ወንጀል የተከሰሱትን ሁሉንም ተከሳሾች ጥፋተኞች ብሎአቸዋል። 


 ከ9 ነኛ እስከ 24ኛ ባሉት ላይ የጥፋተኝነቱ ውሳኔ የተላለፈው በሌሉበት እና የመከላከያ መልሳቸው ባልተሰማበት ሁኔታ ነው። የመሀል ዳኛው እንዳሻው አዳነ፣ ቀኝ ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ እና ግራ ዳኛ ሁሴን ይመር 3 ሰአት ከ40 ደቂቃ ላይ የተሰየሙ ሲሆን አቃቢ ህጎች ቴዎድሮስ ባህሩ፣ አንተነህ ጌታቸው ፣ ዘረሰናይ ምስግናውና እና ብርሀኑ ወንድማገኝ እንዲሁም የተከላካይ ጠበቆች የሆኑት አቶ ተመስገን ደርበው፣ አቶ አበበ ጉታ እና የመንግስት ተቀጣሪ ጠበቃ አቶ ሳሙኤል አባተ ተገኝተዋል።

የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ የአመራር አባላት የሆኑት አቶ አንዱአለም አራጌ እና አቶ ናትናኤል መኮንን፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና የመኢዴፓ ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ በተከሰሱበት አንደኛ፣ ሁለተኛ እና አራተኛ ክሶች ጥፋተኛ ተብለዋል። አቃቢ ህግ ሁሉም ተከሳሾች በጋራ ወንጀል በመንቀሳቀሳቸው እና ከፍተኛ የሀገር ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ እስከ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት ከብዶ እንዲፈረድ የቅጣት ሀሳብ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ አቃቢ ህግ ያቀረበውን ክስ በሙሉ አጽድቆ የተቀበለ እና ተከሳሾችን ጥፋተኛ ብሎ የፈረደ ሲሆን በአንጻሩ ተከሳሾች አቃቢ ህግ ያቀረበባቸውን ክስ ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኞች ናቸው ሲል ውሳኔ ሰጥቷል። የአንዱአለም፣ ናትናኤል፣ እስክንድር እና አበበ ቀስቶ ጠበቃ አቶ ተመስገን ደርበው እና አቶ አበበ ጉታ ደንበኞች ራሳቸው የቅጣት ውሳኔ እንዲሰጡ መጠየቃቸውን ተከትሎ  ፣ ፍርድ ቤቱ  የአቶ አንዱአለምን ንግግር ለመስማት ተገዷል። አቶ አንዱአለም ” እኔ ምንም የፍርድ ቅጣት ሀሳብ የለኝም፣ ለልጆቼና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ዴሞክራሲና ነፃነት እንደሚገባን በማመን አቅሜ በፈቀደው መጠን ታግያለሁ፡፡ 

ይኼን በማድረጌ በማንም ላይ በክፋት አልተነሳሁም፤ ይኼን በማድረጌ ህግ ጥሼ አላውቅም፤ ይኼን በማድረጌ በደሃዋ ሃገሬ ጥቅም ላይ አልተነሳሁም፤ ይሄን በማድረጌ ፈጣሪዬን፣ የኢትዮጵያን ህዝብም ሆነ ህሊናዬን የሚያሳዝን አንዳች ነገር ፈፅሜያለሁ ብዬ አላምንም፡፡ ፍፁም ሰላም ይሰማኛል፡፡ እኔን እዚህ ያቆመኝ የነፃነት ናፍቆት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶችም ፍትህን ለምኜ ስነፈግ ይኼ የመጀርያዬ አይደለም፡፡ ከሳሾቼ እንድጠጣው የሚፈልጉትን የግፍ ፅዋ በፀጋ ከመጠጣት ውጪ ባልፈረፀምኩት ወንጀል ማቅለያ የመጠየቅን አማራጭ ህሊናዬ ስላልተወልኝ አዝናለሁ፡፡

ፍርድ ቤቱ በመቀጠል የሚናገሩትን ጋዜጠኛ እስክንድ ነጋን ፣ ፣ ናትናኤል መኮንንና ክንፈሚካኤል በረደድን ንግግር ሲጀምሩ አስቁሟቸዋል።  ጋዜጠኛ እስክንድር ” እባካችሁ ዳኞች የሚጠብቀን ፍርድ እስከ ሞት የሚያስቀጣ በመሆኑ አቃቢ ህግን በግልጽ ችሎት አነጋግራችሁ እኛን እድሉን አትንፈጉን፣ 2 ደቂቃ ብቻ ልናገር ፣ የፍትህ ሚዛኑን ጠብቁ፣” በማለት ቢናገርም ዳኞች በፖሊስ እንዳይናገር አስቁመውታል። ፍርድ ቤቱም የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት ለሀምሌ 6 ቀን 2004 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።በችሎቱ ላይ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች፣ የአሜሪካን አምባሳደር ጨምሮ የበርካታ አገራት ዲጽሎማቶች እና የእስረኞች ቤተሰቦች ተገኝተዋል። 

ተከሳሾችን ሁሌም እንደሚደረገው በጓሮ በር በኩል ወጥተው በጓሮ በር በኩል ተመልሰዋል። ሂውማን ራይትስ ወች የጸረ ሽብር ህጉ ሀሳብን በነጻነት የመግለጥን መብት ለመደፍጠጥ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ፣ የፍርድ ሂደቱን እና ውሳኔውን ክፉኛ ተችቶአል። ለጋሽ አገራት ውሳኔውን እንዲያወግዙና የፍትህ ስርአቱ እንዲሻሻል ጫና እንዲያደርጉ ጠይቋል። የሂውማን ራይትስ  የአፍሪካ ም/ል ዳይሬክተር የሆኑት ሊስሌ ሊፍኮው የኢትዮጵያ መንግስት መጠነኛ የሚባሉ ትችቶችን እንኳን ለመታገስ አቅም እያጠረው እንደመጣ ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment