ኢሳት ዜና:-ሰኔ ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
በነፍጥ ትግል የመንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረውና በአሁኑ ሰዓት ግን ኢህአዴግ በታገለበት መስመር
በመሄድ በትጥቅ እና በሁለገብ ትግል ለውጥ ለማካሄድ የተደራጁ የተቃውሞ ኃይሎችን በአሸባሪነት የሚፈርጀው ገዥው
ፓርቲ ኢህአዴግ ለቀድሞ ታጋዮቹ ላሳለፉት የትግል ዘመን ልዩ የጡረታ ተጠቃሚ የሚያደርግ ደንብ አወጣ፡፡በዚሁ ደንብ መሰረት አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሌሎች ታጋይ የነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሚኒስትሮች ም/ቤት ሰኔ 1 ቀን 2004 ዓ.ም ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባው የቀድሞ ታጋዮች የትግል ዘመን የጡረታ አገልግሎትን በተመለከተ ውሳኔ አሳልፏል፡፡በአቶ
ሙክታር ከድር የጠ/ሚ ጽ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ሚኒስትር ፊርማ ሰሞኑን የወጣው ሰርኩላር ደብዳቤ እንደሚለው
በሹመትና በሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛነት በመንግስት መ/ቤቶች በመሥራት ላይ የሚገኙ የቀድሞ ታጋዮች የአገልግሎት ዘመንን
አስመልክቶ ጥያቄ መቅረቡን ያሰታውሳል፡፡
በዚሁ መሠረት በጉዳዩ ላይ የሚኒስትሮች ም/ቤት ሰኔ 1 ቀን
2004 ዓም ተወያይቶ በመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ በሚሸፈኑ የተለያዩ የፌዴራልና የክልል የመንግስት መ/ቤቶች
በቋሚነት በመቀጠር ወይም በሹመት በመመደብ በማገልገል ላይ የሚገኙ የቀድሞ ታጋይ አባላት ቀደም ሲል በመከላከያ
ሠራዊት፣በፌዴራል ፖሊስና በማረሚያ ቤቶች ለተመደቡት የቀድሞ ታጋዮች በተወሰነው መሰረት አገልግሎቱ ወደ ትግሉ
ከተቀላቀለበት ጊዜ አኳያ ሶስት ዓመት እየተቀነሰ እንዲያዝላቸው ያዛል፡፡
በተጨማሪም ከመንግስት ሠራተኞች
ማኀበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር ታጋዮቹ ወደ ትግል ከተቀላቀሉበት ጊዜ አንስቶ እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም
ባሉት ጊዜያት ከፈጸሙት አገልግሎት ሶስት ዓመት እየተቀነሰ እንደአገልግሎቱ ዓይነት በወታደራዊ ወይም በሲቪል
በየወሩ መከፈል የሚገባው የአሰሪ መ/ቤትና የሰራተኛ ድርሻ የጡረታ መዋጮ ታሰቦ በመንግስት እንዲሸፈን ደንግጓል፡፡
እያንዳንዱ
የክልል አስተዳደር ካቢኔ ወይም የፌዴራል መ/ቤት ከፍተኛ ኃላፊ በዚሁ ውሳኔ መሰረት በትግል ላይ ያሳለፉትን ጊዜ
ለጡረታ ሊታሰብላቸው የሚገባቸውን የቀድሞ ታጋዮች ዝርዝር መረጃ በማጠናቀርና በማረጋገጥ ለመንግስት ሠራተኞች
ማኀበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ እንዲያሰተላልፍ በጥብቅ አዟል፡
በዚሁ ደንብ መሰረት በአሁኑ ሰዓት ዕድሜያቸው
ከ55 ዓመት በላይ ያሰቆጠሩትና ወደጡረታ እያዘገሙ የሚገኙትን አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ተፈራ
ዋልዋ፣በረከት ስምኦን፣ስብሃት ነጋና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ምንጮቻችን
አረጋግጠዋል፡፡ስማቸው እንዳይጠቀስ በጥብቅ ያስጠነቀቁ አንድ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ኢህአዴጎች
ያኔ ጫካ እያሉ ባንክ ለዘረፉበት፣በሸፍትነት የመንግስት ወታደር ሲገድሉ ለኖሩበት ከ17 ዓመታት በላይ ጊዜ ይህ
ትውልድ ከሚከፍለው ግብር ጡረታ ይቁረጥ ማለት የገዢው ፓርቲ ሰዎች ምንም አይነት ህሊና የሌላቸው መሆኑን ያሳያል
ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ለታጋዮች ካሳ ተብሎ የኮንዶሚኒየም ቤትን እና የገንዘብ ክፍያን ጨምሮ የተለያዩ
ጥቅማጥቅሞች የሰጠው የመለስ መንግስት፣ አሁን ደግሞ ታጋዮቹ ጫካ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ያሳለፉ የትግል አመታት
ተደምሮ በጡረታ እንዲያዝላቸው የሚደነግግ ህግ ማውጣቱ የአገሪቱን ህዝብ በጠራራ ጸሀይ መዝረፍ ነው ብሎዋል። እኝሁ
ባለስልጣን የኢህአዴግ ታጋዮች ለህዝቡ ያስገኙለት ነገር ምንድነው? በማለት ጠይቀው፣ ህዝቡ በዘሩ እንዲባላ፣
የአገሪቱ ሀብት በጥቂት የህወሀት ሰዎች እንዲያዝ ላደረጉበት ስራ የኢትዮጵያ ህዝብ ለጡረታቸውም ግብር እንዲከፍል
ውሳኔ መወሰን ከማንም መንግስት የሚጠበቅ አይደለም ሲሉ አክለዋል።
አንድ ሌላ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ
ሰው ደግሞ የኢህአዴግ ታጋዮች ስልጣን ከያዙበት ከ1983 ዓም ወዲህ ያለው ጊዜ ታስቦላቸው ጡረታቸው ቢረጋጋጥ
ባልከፋ፣ ጫካ የነበሩበት 17 አመታትም በጡረታ መልክ እንዲያዝላቸው መወሰን ግን ቀጣዩ መንግስት የሚቀበለው
አይሆንም ይላሉ። እኝሁ ሰው ኢህአዴግ ከነባር ታጋዮች የሚደርስበትን ተቃውሞ በመፍራት እንዲህ አይነት አሳፋሪ ውሳኔ
ለመወሰን መገደዱንም ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም በመከላከያና በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ ተቀጥረው ላገለገሉ ነባር ተጋዮች
ጫካ በነበሩበት ጊዜ የታገሉበት አመታት ለጡረታ እንዲያዝላቸው መወሰኑ ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment