በምዕራፍ ብርሃኔ, Reporter
‹‹የእኔ የሒሳብ ቀመር ስህተት መሆኑ ከተረጋገጠ በዓለማችን ላይ ከ100 ዓመታት በላይ ሲሠራበት የቆየውን የጋውስን የሒሳብ ቀመር ስህተት እንደሆነ ይረጋገጣል ማለት ነው፤›› ያለው የ17 ዓመቱ ወጣት ናኤል ኃይለማርያም ነው::
‹‹የእኔ የሒሳብ ቀመር ስህተት መሆኑ ከተረጋገጠ በዓለማችን ላይ ከ100 ዓመታት በላይ ሲሠራበት የቆየውን የጋውስን የሒሳብ ቀመር ስህተት እንደሆነ ይረጋገጣል ማለት ነው፤›› ያለው የ17 ዓመቱ ወጣት ናኤል ኃይለማርያም ነው::
ናኤል
የ11 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር ማንኛውንም ትንሽ ቁጥርን ከማንኛውም ትልቅ ቁጥር ላይ ለመቀነስ አልያም ደግሞ
ከማንኛውም ትልቅ ቁጥር ማንኛውንም ትንሽ ቁጥርን ለመቀነስ የሚያስችል የሒሳብ ቀመርን (ፎርሙላን) የፈጠረው::
ነገሩ የተጀመረው እንዲህ ነው:: ናኤል ከስድስተኛ ክፍል ወደ ሰባተኛ ክፍል ሲያልፍ በነበረው የክረምት ወቅት ላይ
በዚያን ጊዜ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የነበረው ታላቅ ወንድሙ የፍሬድሪክ ጋውሰ ቲዮሪን Sn=A1+A2+A3+…+An
የሚለውን የሒሳብ ቀመር ተጠቅሞ ከ1 እስከ 100 ያሉትን ቁጥሮች እንዲደምርለት ይጠይቀዋል::
በቀመሩ መሠረት ቁጥሮቹን መደመር የጀመረው ናኤል፣ እስከምሽቱ ድረስ ቢሞክርም ውጤቱን ለማምጣትና መጨረስ ግን አልቻለም ነበር:: ‹‹ከተኛሁ በኋላም የማሰላስለው የድምሩ ውጤት ስንት ይሆናል የሚለውን ነበር:: ውጤቱን ለማምጣት ጓጉቼ ስለነበርና እንቅልፌም እምቢ ስላለኝ ከአልጋዬ ተነሥቼ ቁጥሮቹን መደመር ቀጠልኩ::
በመጨረሻም በመደመርያ ማሽን የታገዘው ጥረቴ ስኬታማ ሆኖ መልሱን ለማወቅ ችያለሁ፤›› ያለው ናኤል፣ የራሱን ቀመሩን ለመፍጠር መንደርደሪያ የሆነውን ምክንያት አስታውሷል:: ከዚያም በኋላ ታዳጊው የራሱን ቀመር መፍጠር እንደሚችል በራስ የመተማመኑ ስሜት አይሎ የራሱን ቀመርን ለመሥራት ተፍ ተፍ ማለቱን የተያያዘው::
ከዚያም
ከ157 ዓመታት በላይ ሲሠራበት የቆየው የፍሬድሪክ ጋውስ ቲዮሪ ተቃራኒ የሆነውን ቀመር
En=A1-(A2+A3+…+An) እና Tn=An-(An-1+An-2+…+An) የሚለውን ቀመር የፈጠረው:: ናኤል
የቀመሮቹን መጠርያ En እና Tn የሚለውን ስያሜ ከእናቱ ኤደንና ከአባቱ የቤት ስም ታታ ከሚለው እንዳወጣው
ገልጿል:: ከአንደኛ ክፍል እስካሁን ድረስ በልደታ ካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው
ናኤል ቀመሩን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ሦስት ተከታታይ ዓመታት ወስዶበታል:: በናኤል በሁለቱ ቀመሮች ስር ስድስት ቀመሮችንም የሠራ ሲሆን እንደሚባሉም አስረድቷል::
የናኤል ቀመሩን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአራት ኪሎ ካምፓስ በሒሳብ ዲፓርትመንት ለሚገኙ ምሁራን መጋቢት 15 ቀን 2004 ዓ.ም. አቅርቧል:: ቀመሩን ለማየትና ለመገምገም የተሰበሰቡት ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮችም የታዳጊው ቀመር አዲስ እንደሆነ መስክረው ቀመሩ ላይ ምንም ዓይነት ስህተት እንደሌለው ገልጸዋል:: በዕለቱ ከነበሩት ምሁራን መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የሒሳብና ኮምፒውተር ሳይንስ ፋከልቲ ዲን የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ጉታ አንዱ ናቸው::
ዶ/ር ብርሃኑም ‹‹ናኤል ቀመሩን የሠራበት እያንዳንዱ አካሔድ ትክክልና በመጨረሻ ላይም የሚደርስበት ድምዳሜ ፍጹም ትክክል ነው፤›› ብለዋል:: ዶክተሩ እንዳብራሩት ከሆነ የናኤል ቀመር በከፍተኛ ደረጃ የተሠራ ከመሆኑም በላይ፣ አንድ የቅድመ ምረቃ ለመመርቂያው ሊሠራ የሚችለውን ዓይነት ሳይንሳዊ ጽሑፍ ታዳጊው ጽፏል:: የቀመሩ (ሒሳቡ) ርዕስ፣ ቀመሩን ያስረዳበት መንገድ፣ የቀመሩ ጥልቀት፣ ሎጂካል (ተጠየቃዊ) የሆነው የቀመሩ ፍሰትና በቀመሩ መሠረት ተሠርተው የሚገኙት የመጨረሻዎቹን ውጤቶች ለማምጣት የተጠቀማቸው መንገዶች በጣም ጥሩ እንደሆኑ ዶክተሩ አያይዘው ገልጸዋል::
ዶ/ር ብርሃኑ በተጨማሪም እንዳብራሩት ከሆነ እርሳቸውንም ሆነ ሌሎቹን ምሁራን ይበልጥ ያስደመመው፣ ናኤል የቀመሩን ዝርዝር ሁናቴ ለታዳሚው ሲያቀርብ ከቀመሩ መነሻ ጀምሮ እስከ ድምዳሜው ድረስ አንድም ስህተት በሌለው ሳይንሳዊ በሆነ በጥሩ አገላለጽ ቀመሩን መሥራቱ ነበር:: ‹‹ሒሳብ ከፈሩት የሚሸሽ ከደፈሩትና ከቀረቡት ደግሞ የሚቀርብ ትምህርት ነው፤›› የሚለው ናኤል፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተገኝቶ የቀመሩን ፍሰት ለምሁራኑ ባስረዳበት ወቅት የቀመሩ ስሌት ትክክል በመሆኑ ስህተት እንደሌለውና ቀመሩም ፍጹም አዲስ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችሏል::
ናኤል በመጪው ሰኔ 18 ቀን 2004 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚካሔደው ዓለም አቀፍ የሒሳብ ምሁራን ስብሰባ ላይ አዲሱን ቀመሩን ያቀርባል:: በዕለቱም ዓለም አቀፍ የሒሳብ ምሁራን የስብሰባው ተሳታፊ ይሆናሉ:: ‹‹የዓለም አቀፍ የሒሳብ ምሁራን ስብሰባን ያዘጋጁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአሜሪካ የሚገኘው ቴምፕል ዩኒቨርሲቲ በጋራ ሆነው ነው:: የናኤል ሥራ በፕሮግራሙ ላይ ቀርቦ ማረጋገጫ ከተሰጠው በኋላ በኤክስፐርቶችና በሒሳብ ምሁራኑ ቀመሩ ይታያል::
ከዚያ በኋላ ናኤልም ሆነ ምሁራኑ ቀመሩ
ላይ የሚጨምሩትም ይሁን ማስተካከል የሚፈልጉት ነገር ካለ ያ እንዲሆን ይደረጋል:: በመቀጠልም ወደፊት በሚካሔዱ
ትልልቅ የሒሳብ ስብሰባዎችና መድረኮች ላይ ቀመሩ እንዲተዋወቅ ይደረጋል:: ይህ ከሆነ በኋላ የቀመሩ ሁኔታ በደንብ
ታይቶ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካትቶ ለማስተማርያነት ይሆናል ወይ የሚለው ጉዳይ በቀጣይ የሚታይ ይሆናል፤›› ሲሉ
ዶ/ር ብርሃኑ ገልጸዋል::
ናኤል የሒሳብ ቀመርን መፍጠር የቻለ ታዳጊ ነው:: ሁሉንም የሒሳብ ፈተናዎቹን ሲሠራ በ15 ደቂቃ ውስጥ ያጠናቅቃል:: ይህ ፍጥነቱ ግን የሒሳብ ውጤቱ መቶ ከመቶ እንዳይሆን ምክንያት ቢሆንበትም ሁልጊዜ ከ80 እና ከ85 በላይ እንደሚያመጣ ተናግሯል:: ናኤል የሒሳብ ቀመርን መፍጠር መቀጠል የሚፈልግ ሲሆን፣ የራሱን ቀመር ‹‹የሒሳቡ ልኡል›› ተብሎ ከሚጠራው ከፍሬድሪክ ጋውስ ጋር የማወዳደር ሞራል ያለው ታዳጊ ነው:: ናኤል ፍጹም ፍላጐቱ በሆኑት ኮምፒውተርና ሶፍትዌር ነክ የሆኑ ሥራዎች ላይ የተለያዩ ፈጠራዎችን በተጨማሪም ለመሥራት አቅዷል::
No comments:
Post a Comment