ኢሳት ዜና:- ግንቦት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
በያዝነው ወር ሀሉም ነገር መጨመሩን ከተለያዩ
አካባቢዎች የሚገኙ ዘጋቢዎቻችን ገልጠዋል። በአማራ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ጤፍ እስከ 1300 ብር በመሸጥ ላይ
ነው። በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋም የጤፍ ዋጋ መጨመር እንጅ መቀነስ አላሳየም። የበቆሎ እና ሌሎችም ለምግብ
ፍጆታነት የሚውሉ ሸቀጦች ተነጻጻሪ ጭማሪ አሳይተዋል። የዘይት ዋጋ ባለበት ቢቆይም፣ ስኳር እና ሻይ ቅጠል ጭማሪ
አሳይተዋል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ 4 ብር የነበረው አንድ ባኮ ሻሂ ቅጠል ወደ 8 ብር ከፍ ብሎአል።
አሁን
የሚታየው የእህል ዋጋዎች ጭማሪ እንደሚቀጥል የተለያዩ የከተማ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ገበሬው በማዳበሪያ እዳ መያዙ፣
ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በግዳጅ እንዲያዋጣ መታዘዙ እና በቂ እህል አለኖሩ የእህል ምርት ዋጋን ከሚጨምሩት
ምክንያቶች ተርታ ተሰልፈዋል። መንግስት የእህል ዋጋ አሁን ካለበት መጠን እንዳያልፍ 8 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ
ለማረጋጊያ መግዛቱንና ከዚህም ውስጥ 3 ሚሊየን ኩንታል ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ተናግሯል።
መጪው
የክረምት ጊዜ እንደመሆኑ በመላ አገሪቱ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ባየለበት በአሁኑ ጊዜ
ማእከላዊ ስታትስቲክስ በሚያዚያ ወር የዋጋ ግሽበቱ መቀነሱን የሚያሳይ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። መስሪያ ቤቱ እንዳለው ያለፈው ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 29 ነጥብ 8 ነው።
በሚያዚያ ወር 2004 ዓ.ም የተመዘገበው የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ የዋጋ ግሽበት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ36 ነጥብ 3 በመቶ ጭምሪ እንዳሳየ ከአገራዊ የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ የምግብ ዋጋ ግሽበት ጋር ሲነጻጻር ደግሞ በ45 ነጥብ 5 በመቶ መጨመሩን አመልክቷል። በተመሳሳይ ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ግሽበት በ23 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሷል።
በበያዝነው
አመት በሚያዚያ ወር የምግብ ዋጋ ግሽበት ከአምናው ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጻር በ36 ነጥብ 7 በመቶ አድጓል።
በአገሪቱ ውስጥ ለታየው የዋጋ ግሽበት መጨመር ዋነኛ ምክንያት የሆነው የእህል ዋጋ በ45 ነጥብ 8 በመቶ መጨመሩ
ነው። ያሳለፍነው ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ቀደም ብሎ ከነበረው የመጋቢት ወር ጋር ሲነጻጸር በ2 ነጥብ 1 ዝቅ ማለቱን ኤጀንሲው ገልጧል። በኢትዮጵያ የሚታየው የዋጋ ንረት የህዝቡን ብሶት እየጨመረው እንደሚገኝ መገናኛ ብዙሀን እየዘገቡት ይገኛሉ።
No comments:
Post a Comment