By Fetehe.com, ርእሰ አንቀፅ
በኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ይመራ የነበረው አምባገነኑ የደርግ ስርዓት በኢህአዴግ መራሹ ጦር በሀይል ከተገረሰሰ እነሆ ከቀናቶች በኋላ ድፍን ሃያ አንድ አመት ይሞላዋል። ግንቦት ሃያ ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሶስት አመተ ምህረት።
የኮሎኔል መንግስቱ መንግስት ከስልጣን መውረድን ተከትሎ አዲሱ የኢህአዴግ መንግስት የቀድሞ መንግስት በአዋጅ የሻራቸውን ህዝባዊ መብቶች በአዋጅ እንደተፈቀዱ ይፋ አደረገ። ከዚህ ባሻገር በ1987ዓ.ም. በፀደቀው ህገ-መንግስት አብዛኞቹ መብቶች (ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች) ተካተቱና ዘላቂ ዋስትና አገኙ። ከእነዚህ ተፈቃጅ መብቶች አንዱ ኮሎኔል መንግስቱ በአዋጅ ደንግገውት የነበረው የሳንሱር /የቅድመ ምርመራ/ ስራን በአዋጅ መሻሩ መታወጁ ነው።
ይህንንም ተከትሎ በርካታ የፕሬስ ውጤቶች በህትመት ላይ ውለው ለማየት ተቻለ። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያሉት የህትመት ውጤቶች /በተለይም የጋዜጦች ቁጥር/ በእጅጉ አናሳ ነው። ይህ የሆነውም በራሱ ፍቃድ በሰጠው መንግስት የእጅ አዙር ጥቃት ነው። ነገር ግን የነበሩትን ነፃ ጋዜጦች እንዲዘጉ ሲያደርግ የተለያየ የመወንጀያ ህግ በማዘጋጀት እንጂ እንዲህ እንደዛሬው ጠራራ ፀሐይ ህገ- መንግስቱ መገርሰሱን ያረጋገጠውን ቅድመ ምርመራ /ሳንሱር/ በመመለስ አይደለም።
ይህ የህገ-መንግስት ጥሰት የተከሰተው በመንግስት የሚተዳደረው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሰሞኑን ለአሳታሚዎች ‹‹የህትመት ስራ ስታንዳርድ ውል›› በሚል ርዕስ በበተነው ሰነድ ላይ ከአስቀመጠው አንቀፆች ውስጥ ህገ- መንግስቱን የሚፃረሩ በመኖራቸው ነው። በተለይ ደግሞ በአንቀጽ 10- ‹‹ህግን የተላለፈ ይዘትን አለማተም›› በሚል ርዕስ የሰፈረው ሀሳብ እንዲህ ይላል፡- 10.1 አሳታሚ በአሳታሚው እንዲታተም የቀረበለት የፅሁፍ ስክሪፕት ሕግን የሚተላለፍ ስለመሆኑ ለማመን በቂ ምክንያት ካለው አላትምም የማለት መብት አለው።
10.2 አታሚ አሳታሚው የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህትመት ይዘት የማውጣት ዝንባሌ ያለው መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ካለው በማናቸውም ጊዜ ውሉን ለማቋረጥ ወይም ለመሰረዝ ይችላል። እነዚህ አንቀፆች በግልፅ ህገ መንግስቱን የሚፃረሩ ቢሆኑም ከመንግስት በኩል እስከአሁን ድረስ ምንም የተባለ ነገር የለም። ሁላችንም እንደምናውቀው መንግስት ተቃዋሚዎቹን እና ተቺዎቹን እስር ቤት ሲያስገባ ሁልጊዜም የሚሰጠው ምክንያት ተመሳሳይ ነው ‹‹ህገ መንግስቱን ለማስከበር ነው›› የሚል።
አሁን ደግሞ በስሩ የሚተዳደረው ተቋም በግልፅ ህገ- መንግስቱን ተፃርሮ አፋኝ ውል አቅርቦአል። ይህን እንድንል ያስቻለን በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 21 ንዑስ አንቀፅ 3(ሀ) ‹‹የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለለ መሆኑን›› በማስታወስ ነው። ከህገ-መንግስቱ በተጨማሪ ስለመገናኛ ብዙሃን ነፃነት የሚናገረው አዋጅም ተመሳሳይ አንቀፆች አሉት።
ህዳር 25 ቀን 2001 ዓ.ም. የወጣው ነጋሪት ጋዜጣ በአዋጅ ቁጥር 590/2000 ‹‹የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ›› በሚል ርዕስ በገለፀው መሰረት በክፍል አንድ በቁጥር አራት ላይ ‹‹መገናኛ ብዙሃን ነፃ ስለመሆናቸው›› በሚለው ርዕስ ስር እንዲህ ይላል፡- 1. የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት በህገ መንግሥቱ ዕውቅና አግኝቷል። ቅድመ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ ነው፡፡
እንግዲህ መንግስታዊው ተቋም ብርሃንና ሰላም ደግሞ ፅሁፉን አንብቤ ካልጣመኝ፣ ካልተመቸኝ ወይም ዝንባሌው ህግ የሚጥስ መስሎ ከታየኝ አላትምም፣ በማናቸውም ጊዜ ውሉን ለማቋረጥም የሚከለክለኝ የለም እያለ ነው። በአንድ ሳምንት ውስጥም ይህንን ውል ካልፈረማችሁ ጋዜጣችሁን አላትምም ሲል ከትላንት በስቲያ ለሁሉም ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ደብዳቤ ልኳል። ይሄኔም ነው እስከዛሬ ድረስ ‹‹ህገ-መንግስቱን አደጋ ላይ ሊጥሉ፣ ሊቃወሙ፣ ሊያፈርሱ….›› ሲያሴሩ ደረስኩባቸው እየተባለ የሚታሰሩ ተቃዋሚዎች እና ጋዜጠኞች ጉዳይ የእስራቸው ምክንያት ይበልጥ ግልፅ
የሚሆነው።
መቼም መንግስት ራሱን እንደ ጲላጦስ ነፃ አድርጎ ‹‹ጉዳዩ የአታሚውና የአሳታሚው ነው፣ እኔን አይመለከተኝም›› የሚል ቀልድ ይቀልዳል ብለን አናስብም። ምክንያቱም የሞያ አጋሮቻችንን ጨምሮ ፖለቲከኞችን ሲያስር ጆሮአችን እስኪደነቁር ድረስ የሚነገረን ‹‹ህገ መንግስቱን ለማስከበር ነው›› የሚል ምክንያት ነውና። ለዚህም ነው አሁን ብርሃንና ሰላም ከመንግስቱ ኃ/ማርያም የስልጣን እድሜ ጋር አብሮ ያከተመውን ‹‹ቅድመ ምርመራ››፣ ህገ መንግስቱን ጥሶ በስራ ላይ ሊያውል ሲሞክር መንግስት ህገ-መንግስቱን የማስከበር ግዴታውን ይወጣል ብለን የምናስበው።
ይህ ሁኔታ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በፍትህ እምነት የደርግን ሸንጎ የአንድ ፓርቲ ፓርላማን ጨምሮ የሚያስታውሰንን በብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታቶች የወደቀው የኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም አገዛዝ በሌላ ባርኔጣ እየተመለሰ እንደሆነ ነው። ምንም እንኳን በኢህአዴግ እና በደርግ መካከል ያለው ልዩነት ጠባብ ቢሆንም ኢህአዴግን ከደርግ የተሻለ የሚያደርገው ብቸኛ ምክንያት ቅድመ ምርመራ /ሳንሱር/ በአዋጅ እንዲሻር መድረጉ ነው።
ይኸውም ከ20 አመት የስልጣን ዘመኑ በላይ በማንም ሳይነካና ሳይሸረፍ ቆይቶአል። ዛሬ ግን ይህ መብት ቅርቃር ውስጥ ሊወድቅ ከአፋፍ ቆሟል። እናም በፍትህ ዕምነት የመንግስት አማራጭ ሁለት ብቻ ይሆናል። የመጀመሪያው ህገ-መንግስቱን ለመገርሰስ ቆርጦ የተነሳውን ብርሃንና ሰላምን ህገ-መንግስቱን እንዲያከብር ማስገደድ፣ አሊያም በብርሃንና ሰላም በኩል ህገ-መንግስቱን በትብብር ንዶ ሙሉ በሙሉ የኮሎኔል መንግስቱን ኃ/ማርያም አገዛዝ መመለስ። መንግስት የሚወስደውን አማራጭ በቀናቶች ውስጥ የምናየው ይሆናል፡፡
No comments:
Post a Comment