Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Friday, May 3, 2013

አንድ ፦ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ: By መስፍን ወልደ ማርያም

በአለፉት ሠላሳ ዓመታት በኢትዮጵያ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ እንደኢሳት (የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዥንና ራዲዮ) ያለ ኃይል የትኛውንም የኢትዮጵያ አገዛዝ አጋጥሞት አያውቅም፤ በመሠረቱ የኢሳት መሣሪያነት ከባህል ውጭ ቢሆንም የባህል ይዘት አለበት፤ ይህንን ወደኋላ አመለክታለሁ፤ ወደድንም ጠላንም የኢትዮጵያ ታሪክ በመሠረቱ ሁሌም በኃይል ላይ ቆሞ በኃይል የሚሽከረከር ነው::  

በአለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ የመጡት አብዮተኞች ሁሉ ይህንን በመሠረታዊነት የመክሸፍ ምንጭ የሆነውን የጉልበት አምልኮት እንደዓላማም እንደመሣሪያም ይዘው የተነሡ ናቸው፤ ዛሬም ቢሆን ተሸናፊዎችም ሆኑ አሸናፊዎች አብዮተኞች የሚያወሩትና የሚጽፉት ከጉልበተኛነት ከረጢታቸው ሳይወጡ ጥፋታቸውን እንደልማት፣ አላዋቂነታቸውን እንደብልህነት በማድረግ ራሳቸውን አታልለው ሌላውን ለማታለል እየሞከሩ ነው::


አንድም የከሸፈ አብዮታዊ መሪ ያለጠዋሪ ልጅ የቀሩትን እናቶችና አባቶች፣ የብልጣብልጦች መሣሪያ ሆነው እንደወጡ የቀሩትን ወጣቶች በኃላፊነትን ተቀብሎ በእውነት የሚዘክራቸው የለም፤ እነዚያ በየሜዳው በጥይት ነደው ጅብና አሞራ የበላቸው ወጣቶች እንደማንም ሰው ሕይወትን ለማጣጣም የሚያስችሉ ሌሎች ዓላማዎች ነበሩአቸው፤ ዛሬ ‹‹መስዋእት ሆኑ›› እየተባለ ይነገርላቸዋል፤ ዶሮን ሲያታልሏት ዓይነት ነው፤

 ይህንን የሚሉት የራሳቸውን ሕይወት እየሳሱለት ጠብቀው በሌሎች ሕይወት ጉልበተኞች ለመሆን የተመኙት ናቸው፤ በወጣቶቹ አጥንት ላይ ጉልበተኛነታቸውን የተከሉት አጥንቱ እየቆረቆራቸው ይባንናሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፤ በወጣቶቹ አጥንት ላይ ከአሜሪካ የመጣ ድርብርብ ፍራሽ ስላነጠፉበት አጥንቱ መኖሩንም አያስታውሱትም፤ ዛሬም የሚሳሱለትን ሕይወታቸውን በሰፊ ግምብና በታጠቁ ወጣቶች አጥር ይጠብቃሉ፤

 በአንጻሩ በምኞት የቀሩት ከንፈራቸውን እየነከሱ ከጠርሙስ ጋር ይታገላሉ፤ ከምኞት ባርነት ወጥተው ለንስሐና ለነጻነት ገና አልበቁም፤ ለንስሐ ሳይበቁ የሞቱም አሉ፤ የመክሸፍ ክፉነት እውነትን ፊት-ለፊት የመጋፈጥ ወኔ ሳያገኙና ንስሐ ሳይገቡ ከነኃጢአት በወጣቶች ደም ተጨማልቆ መሞት ነው፤ የከሸፈውን እንዳልከሸፈ፣የከሰረውን እንዳልከሰረ፣ተሸንፎ የተንኮታኮተውን እንዳልተሸነፈ እያደረጉ የሬሳ ቀረርቶ ማሰማት የማይሰለቻቸው ሞልተዋል፤ ወደፊት መግፋት የሚቻለው ሬሳ ሬሳን ተሸክሞ ሳይሆን፣ ስሕተትን አርሞ የሞተውን ቀብሮ ነው።

በሃይማኖታዊ ቋንቋ ንስሐ አለመግባት ማለት ጥፋትንና ስሕተትን አለማመንና በቅብብሎሽ ለሚቀጥሉት ትውልዶች ማስተላለፍ ነው፤ ጥፋቱንና ስሕተቱን የማይቀበል ከነጥፋቱና ከነስሕተቱ ዕድሜውን ይጨርሳል፤ ለልጆቹም የሚያወርሰው ያንኑ ጥፋቱንና ስሕተቱን ነው፤ ዓይን ያለው ያያል፤ ይህንን የጥፋት ውርስና ቅርስ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ወስነን ካየነው ጉዳቱ በጣም የሚያንስ ይመስላል፤ በማኅበረሰብና በአገር ደረጃ ካየነው ግን ጉዳቱ ከባድ ነው፤ ከኋላችን የሚመጡት ሁሉ የሚቀድሙን በሌላ ምክንያት አይደለም፤ 

ከሃምሳና ስድሳ ዓመታት በፊት ከናይጂርያ፣ ከጋና፣ ከማላዊ፣ ከታንዛንያ፣ ከኬንያና ከኡጋንዳ እየመጡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ወጣቶች ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ አገሮቻቸውን ሲያገለግሉ ነበሩ፤ በኬንያ እንደሮበርት ኡኮ ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበረ፤ በታንዛንያ እንደጆርጅ ማጎምቤ ለብዙ ዘመናት በተለያዩ አገሮች አምባሳደር ነበር፤ በዚያን ዘመን ለነዚህ የአፍሪካ አገሮች የተረፈችው ኢትዮጵያ ዛሬ ከእነሱ በታች መሆንዋ ቆሞ ከመቅረት የመጣ ነው፤ ቆሞ መቅረቱ ደግሞ ስሕተትንና ጥፋትን እያዘሉና እሹሩሩ እያሉ ከመንከባከብ የሚመጣ ነው፤ 

እውነተኛ መልካችንን የምናይበት መስታዋት ሳይኖረን ብዙ ምዕተ-ዓመታት አለፉ፤ አቧራ ሲጠራቀም ከጊዜ ብዛት ተራራ ይሆናል፤ ትንሽ ጉድጓድ ከጊዜ ብዛት ረጅም ገደል ይሆናል፤ ትንሹ ቁስል ከዋለ ካደረ የቆላ ቁስል ይሆንና እንቅልፍ ይነሳል፤ በአንድ ቦታ ላይ አንድ እንቅፋት ደጋግሞ የሚመታው ሰው ረዳት ያስፈልገዋል፤ አለዚያ አንድ ቀን ያው እንቅፋቱ ይገድለዋል።

ኢሳት ለኢትዮጵያ አዲስና ኢትዮጵያዊ አብዮትን የሚያውጅ ይመስላል፤ እስከዛሬ አብዮት የምንለው ሁሉ የተለያዩ አገሮችን የታሪክ ውራጅ በግድ ኢትዮጵያን ለማልበስ የሚሞክር ነው፤ 1967 ሶሺያሊዝም አዲሱ ሃይማኖት መሆን ሲጀምር በጎንደር በማኅበረ ሥላሴ ኅብረተሰባዊነት (ሶሺያሊዝም) አለ ብዬ ብናገር ውራጅ ሶሺያሊዝምን የሚያመልኩ ብዙ ዘለፋ አወረዱብኝ፤

አሁንም ቢሆን ውራጅ ከመዋስ ገና አልወጣንም፤ የልመና ስልቻችንን ተሸክመን አንዴ በአሜሪካ በር፣ አንዴ በሩስያ በር፣ አንዴ በቻይና በር ላይ እንቅለሰለሳለን፤ ልመና ባህል ነው፤ ለጌታ ማደርም ባህል ነው፤ ሆኖም ሁለቱም ዘዴዎች እድገትንና መሻሻልን አያመጡም፤ መሻሻልን የሚያመጡ ቢሆኑም የሚያስከትሉት ጉዳት ከሚሰጡት ጥቅም የበዛ ነው፤የሚገኘው ግዑዝ ጥቅም የአእምሮና የመንፈስ ውድቀትን በማስከተል ዋጋን ያስከፍላል፤ ይህ ሁሉ ጉዳይ በነጻነትና በሙሉ ልብ ክርክርን የሚጋብዝ ነው፤ ኢሳት ለዚህ ጥሩ መድረክ ሊሆን ይችላል፤ ይሆናል ለማለት ብችል ደስ ይለኝ ነበር።

ይቀጥላል—————–

No comments:

Post a Comment