Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Friday, May 3, 2013

የእነአንዱአለም እና እስክንድር ነጋ ነገር በጠቅላይፍ/ቤት (ወሰንሰገድገብረኪዳን)

ሰበር ዜናውን ከስፍራው የዘገበው ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን፤ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የነበረውን የችሎት ሂደት በዝርዝር ዘግቧል። ከዚህ ቀጥሎ እናቀርባለን። 

“ሀገሬን ሀገሬን – የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላ፣ ታሳዝነኛለች”
– አዝማሪ

 ሌሊት ሌሊት እንደ “ዳዊት ደጋሚ” ስለማመሽ ጠዋት ጠዋት ተጋድሜ ማርፈድ ልማዴ ነበር፡፡ ዛሬ ዕለተ ሐሙስ ሚያዝያ 26 ቀን 2005 ዓም፣ ካለወትሮዬ በጠዋት ከዕንቅልፌ ተነሳሁ፡፡ እናም ወደ ጠቅላይ ፍ/ ቤት አመራሁ።ዕለቱን እያሰብኩ፡፡


የዛሬው ሐሙስ በክርስትና አማኞች ዘንድ በተለየ መልኩ የሚታሰብ ቀን ነው፡፡ ክርስቶስ ትህትናን በተግባር ያስተማረበት ቀን ነው፡፡ የሐዋርያዎቹን እግር ዝቅ ብሎ ያጠበበት ቀን፡፡ በልማድም ቢሆን ሐሙስ የቀን ቅዱስ ነው ይባላል፡፡ ስለዚህም ከእነ አንዱአለም አራጌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የይግባኝ ማመልከቻ “የተቀደሰ” ዜና እሰማለሁ የሚል ሃሳብ ተሞልቼ ነበር 6 ኪሎ ወደሚገኘው ጠ/ፍ ቤት በእግሬ ያቀናሁት፡፡

በእግሬ ያመራሁት ተከሳሾቹ ከማረሚያ ቤት የሚመጡት አርፍደው ነዉ በሚል እሳቤ ነበር፡፡ ነገር ግን ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ እስረኞቹ ችሎት ገብተው ተቀምጠዉ ነበር፡፡ ወዲያው ከእስረኞቹ ውጪ ችሎቱን ለመከታተል የመጡ ሁሉ ከክፍሉ እንዲወጡ ተደረገ፡፡ ችሎቱ ውስጥ አንዱአለም አራጌ እና እስክንድር ነጋ እንዲሁም በሌላ መዝገብ የተከሰሱ ሌሎች 3 እስረኞች ከአጃቢዎች ቀሩ፡፡ በእነ አንዱአለም መዝገብ ተከሰው ይግባኝ የጠየቁት ሌሎች እስረኞች በስፍራው አልታዩም፡፡

እኛ ኮሪደር ላይ ተሰባስበን ለምን ሌሎቹ እስረኞች እንዳልመጡ እየተወያየን ደቂቃዎች በደቂቃዎች ላይ ነጎዱ፡፡“አንተ የኔ ጀግና ነህ፡፡ ብትሞትም በእውነትህ ኮርተህ ሙት!” ሰርካለም ፋሲል

“ሀገሬን ሀገሬን – የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላ፣ ታሳዝነኛለች”

3 ሰዓት ከ50 ደቂያ ሲል ናትናኤለ መኮንን እና ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) አንድ አንድ እጃቸውን በካቴና ታስረው ከውጪ ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ ኮሪደር ላይ ችምችም ብሎ በሚጠብቃቸው ሰው መሃል እያለፉ አንዱ በግራ እንዱ በቀኝ እጁ እየጨበጡኝ አልፈው ወደ ችሎት ገቡ፡- በፖሊስ ታጃበው፡፡ 3 ሰዓት ከ55 ደቂቃ፤ ዳኞች ወደ ችሎት ገብተው ቦታቸውን ያዙ፡፡ ወዲያው ታዳሚ እንዲገባ ፈቀዱ፡፡ ጥቂት ለችሎቱ በር በቅርበት የቆሙ ታዳሚዎች ገቡ፡፡ የደሃ ሳሎን የምታክለው(ደሃ ሳሎን አለው እንዴ?)

ችሎቷ ወዲያው ጢም አለች፡፡ 4 ሰዓት የግራ ዳኛው አንድ እስረኛ ጠሩ፡፡ እናም ውሳኔያቸውን በቃል ቅልብጭ አርገው ተናገሩ – በነፃ፡፡ በሌላ ክስ የታሰረውን ሁለተኛ ተከሳሽ ጠሩ – በነፃ፡፡ እኔ ከጠቀመጥኩበት ወንበር ጀርባ ያሉ ሁለት ሴቶች ወደመሬት ተደፍተው በደስታ አለቀሱ፡፡ መደሰት እንጂ ማዘን አይገባም ብለን ገፋፍተን “አስወጣናቸው፡፡” የቀጣዩን የእነ እስክንድርን መዝገብ ውሳኔ ለመስማት እየቋመጥን፡፡

“ሀገሬን ሀገሬን -የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላ፣ ታሳዝነኛለች”

የመጀመሪያዎቹ መዝገቦች ፍርድ ሲነበብ እኔ በዚያች ጠባብ አዳራሽ ውስጥ ተደራርቦ የተቀመጠውን ሰው ሆን ብዬ ቆጠርኩ፡፡ የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ቦታ አጥታ ከእኔ ጋር አንድ ወንበር ተዳብላ ተቀምጣለች፡፡ ሌሎችም ሰዎች እንደዛው፡፡ ብቻ በዚያች ጠባብ ችሎት ውስጥ ከተሳሾች፣ ከጠበቆች፣ ከእስረኞችና ከችሎት አስከባሪዎች ውጭ 48 ሰው ታፍጓል፡፡ ሌላው ሰው በቦታ ጥበት ኮሪደር ላይ ተኮልኩሏል፡፡ የመሃል ዳኛው ከፊት ለፊታቸው ተደጉሶ የተቀመጠውን ፋይል እየነካኩ በለሠለሰ አንደበት “እንግዲህ እናንተ ፍ/ቤቱን … ውሳኔ መቀበል አለባችሁ አሉ፡፡

በአንድ ወንበር ላይ ተፋፍገን የተቀመጥነው እኔና ሰርካለም እርስ በርስ ተያየን፡፡ ዳኛው ቀጠሉ “በዚህ መዝገብ የቀረበው ክስ በባህሪው ከሌሎች መዝገቦች የሚለይና ውስብስብነት ያለው ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 652/2001 በመሆኑ፣ ሕጉ የተቃኘበትን መርህ መቃኘትን” እንደሚጠይቅ አብራሩ፡፡ 

በዚህ መሰረት በአምስት የይግባኝ ፋይሎች የቀረቡትን አቤቱታዎች ተያያዥነት ያላቸው በመሆናቸው ፍ/ቤቱ በአንድ ላይ በጥልቀት መርምሮ ዉሳኔ መስጠቱንና ገለፁ፡፡ በቅድሚያ የአቃቤ ሕግን ክስ፣ ቀጥሎም የይግባኝ ባዮችን አቤቱታ፣ ከዚያም በከሳሽና በተከሳሽ ወገኖች የቀረቡትን ምስክሮችና ማስረጃዎችን ይዘት በመመርመር ፍ/ቤቱ የሰጠውን ትንታኔና ውሳኔ በንባብ እንደሚያሙ አሳውቁ፡፡

“ሀገሬን ሀገሬን- የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላኝ፣ ታሳዝነኛለች”


ከእኔ በስተቀኝ የተቀመቡት ዕድሜአቸው ወደ ሰባዎቹ የሚጠጋ ጎስቋላ እናት ዳኛው የሚያነቡትን ነገር በቅጡ የተረዱት አይመስሉም፡፡ አንዴ ወደ እኛ፣ አንዴ ወደተከሳሶቹ እየተንጠራራሩ ያያሉ፡፡ እንደዘበት ሸብ ያደረጉት ሻሻቸውን አልሮ የወጣውን ሽበታቸው እየደባበሱ ቁና ቁና ይተነፍሳሉ፡፡ ገፅታቸው ላይ አንዳች ድካምና የሕመም ስሜት የሚነበብባቸው እኚህ እናት ምቾት አልተሰማቸውም፡፡ ዳኛው ንባባቸውን ከጀመሩ ድፍን አንድ ሰዓት አልፏል፡፡ ድንገት ወደቀኝ ዞር ስል ሴትዮዋ የሆነ ስሜት ስልም ሲያደርጋቸው አየሁ፡፡

ሰርካለምን በክርኔ ጎሽመ አድርጌ ወደሴትየዋ ጠቆምኳት፡፡ እጆቺን በእኔ ላይ አሸጋግራ “አይዞዎት” እያለች ጎናቸውን ጨመቅ ጨምቅ፣ አሸት አሸት አደረገቻቸው፡፡ ወዲያው የእፎይታ ትንፋሽ በረዥሙ ተንፍሰው “ነቃ” አሉ፡፡ የክንፈሚካኤል እናት መሆናቸውን ነገረችኝ እየደባበሰቻቸው፡፡ የእስረኛ ቤተሰቦች ከመላመድ ብዛት እርስ በርስ የሚበረታታበት ሕክምና መሆኑ ነው፡- አልኩ ለራሴ፡፡

“ ሀገሬን ሀገሬን- የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላኝ፣ ታሳዝነኛለች”

ዳኛው ንባባቸውን አላቋረጡም፡፡ “አንዱአለም አራጌን በሚመለከት፡- ሕገመንግስታዊ መብትን ሽፋን አድርጎ በመጠቀም፣ ከግቦት 7 ጋር ለሽብር ተግባር በመመሳጠር፣ ወጣቶችን ለሽብር ተግባር በማደራጀት፣ ለሽብር በመምራት… ወዘተ ናትናኤል መኮንን፡-እንዲሁ ወጣቶችን ወኪል አስተባባሪ በመሆን…. ክንፈሚካኤል ደበበ በህኑዕ የግንቦት 7 አባል በመሆን፣ በማሴር…. እስክንድር ነጋ በሕገመንግስቱ ለዜጎች የተሰጠውን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሽፋን በማድረግ የግንቦት ሰባትን ዓለማ ለማስፈፀም፣ በስብሰባና በፅሁፍ ሕዝብን ለአመፅ በመቀስቀስ፣ ለኢሳት መረጃ በማቀበል፣ ከጋዜጠኛ ፋሲል የኔ አለም ጋር በመመሳጠር..ወዘተ” መከሰሳቸውን መረጃና ምስክር የቀረበባቸው መሆኑን አተቱ፡፡

ሁሉም ተከሳሾች በተራ ቁጥር 1 በቀረበባቸው ክስ የሥር ፍ/ቤት ያሳለፈውን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚነቀፍ ሆኖ እንዳላገኘው ገለፁ፡፡ ሁለተኛው ክስ በአንደኛው ክስ ስር የሚጠቃለል በመሆኑ መሻሩንም አክለው አሳወቁ፡፡ በአጠቃላይ ሁሉም ተከሳሾች በ1ኛ እና በእራተኛ ክስ ጥፋተኛ ተብለው የተወሰነባቸው ውሳኔ የሕግ ስህተት እንደሌለበት አሳወቁ፡፡

ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው የተገኙበት አንቀፅ 17 እና 18 ዓመት እስራት በአጠቃላይ ድምር ወደ 34 ዓመት እስራት የሚደነግጉ ቢሆንም፣ በሃገሪቱ ከ25 ዓመት በላይ እስር ስለማይፈቀድ የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ እንዲፀና መወሰኑን ገለፁ፡፡ ይሁን እንጂ የሥር ፍ/ቤት ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ፍ/ቤት በመድፈር በተጨማሪነት የተላለፈበት የ5 ዓመት እስር እንዲሻር ሲሉ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡

“ሀገሬን ሀገሬን – የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላኝ፣ ታሳዝነኛለች”

የፍርዱ ውሳኔ ምንም ለውጥ እንዳላመጣ ቀድማ የተረዳችው ሰርካለም ፋሲል “እስክንድር ወንጀለኛ ነው ከተባለ፣ ወንጀሉ ሃገሩን መውደዱ ነው” ብለህ ፅፍ አለችኝ -በንዴት። “ግንቦት 7 የእስክንድርን እጅ የመጠምዘዝ ኃይል የለውም” አለችኝ በቁጭት፡፡

ችሎቱ ውሳኔውን አሳውቆ ዳኞች እንደተነሱ፣ ተከሳሾች ከፍርድ ሳጥን እየወረዱ ባለ እስክንድር እልሀ በተናነነቀው ስሜት ጮክ “አትጠራጠሩ እውነት ተደብቃ አትቀርም” አለ፡፡ ናትናኤል “የተከራከርነው ፍትህ እናገኛለን ብለን አይደለም፤ ፍትህ ወዳድ ስለሆንን ነው” አለ፡፡ አበበ ቀስቶ “ለማንኛውም እዚህ መጥታችሁ በእናንተ ኮርተናል” ሲል በችሎት የሰገኘውን ሰው አመሰገነ፡፡

 “አንተ የኔ ጀግና ነህ፡፡ ብትሞትም ሙት፣ በእውነትህ ኮርተህ ሙት!” አለች ሰርካለም እንባ እየተናነቃት፡፡ ወዲያው ፖሊሶች ታዳሚውን እየገፋፉ ከችሉት አስወጡ፡፡ በሌላኛው በር አንዱአለምና እስክንድርን አንድ ላይ፣ ክንፈሚካኤል እና ናትናኤልን በአንድ ላይ በካቴና አስረው፡- ወደ ቃሊቲ፡፡

“አንተ የኔ ጀግና ነህ፡፡ ብትሞትም ሙት፣ በእውነትህ ኮርተህ ሙት!” አለች ሰርካለም እንባ እየተናነቃት። ወዲያው ፖሊሶች ታዳሚውን እየገፋፉ ከችሉት አስወጡ፡፡ በሌላኛው በር አንዱአለምና እስክንድርን አንድ ላይ፣ ክንፈሚካኤል እና ናትናኤልን በአንድ ላይ በካቴና አስረው፡- ወደ ቃሊቲ፡፡ አይዞዎት እማማ፤ ወደፊት የሚመጣው አይታወቅም አልኳቸው ” የክንፈሚካኤልን እናት፡፡ በእኔ ቤት ማፅናናቴ ነው፡፡ 

“አዎ የሚመጣው አይታወቅም፣ ይኼስ ይመጣል ብሎ ማን አሰበ፡፡ እናንተ ወጣቶች ራሳችሁ አይዟችሁ፡፡ ታሰሩ፡፡ አይዞአችሁ፡፡ ግን አትሙቱ” አሉኝ የክንፈ እናት፡፡ “አይዟችሁ ታሰሩ! ግን አትሙቱብን!” የእኚያን እናት አባባል እያላመጥኩ ከዳኝ፡፡ እንባዬ መጣ፡፡ ዓይኔን እንዳያዩ ፊቴን አዞርኩ፡፡

“ሀገሬን ሀገሬን – የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላኝ፣ ታሳዝነኛለች”
አበቃ፡፡

No comments:

Post a Comment