እንደ መነሻ
በ1983 ዓ.ም. ወርሃ ግንቦት መንግስታዊ ስልጣን በሃይል የተቆጣጠረው ኢህአዴግ፣ ከጥቂት ወራት በኋላ ሃያ ሁለተኛ ዓመቱን ይደፍናል:፡ በእነዚህ አመታት አገዛዙ ያነበረውን ስርዓት በሶስት የዘመን ክፍፍሎች (Historical Periodization) ወይም ገፅታዎች ከፍለን (በጊዜ እና በግለሰቦች ላይ በተመሰረተ መስፈርት) ማየት እንችላለን፡፡ ከ1983 እስከ 1993 ዓ.ም-‹‹ቡድናዊ››፣ ከ1993-2004 ዓ.ም-‹‹ግለሰባዊ›› እና ከ2005…? ዓ.ም-‹‹ቡድናዊ›› በሚል፡፡
ከ1983-93
በእነዚህ አመታት ስርዓቱ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የፖለቲካ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የሚል ተስፋ ከውስጥም ከውጭም ተጥሎበት ነበር፡፡ ይህንን ተስፋ ያጠናከረው በኃይል የወደቁት ቀደምት ስርዓታት በአዋጅ ያገዷቸውን፤ ማንኛውም ሰው በመረጠው የፖለቲካ አመለካከት መደራጀት እና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽን መብቶች በአዋጅ በመፍቀዱ ነው፡፡ ከዚህ ክልከላ መሻር በኋላም በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች መፈጠራቸው እና ነፃነታቸው ገደብ አልባ የነበረ ለቁጥር የሚያታክቱ የግል ፕሬሶች እንደ አሸን መፍላታቸው፣ እንዲሁም ለትችት ከተጋለጡት ጥቂት አንቀጾቹ በቀር የተወደሰለት ህገ-መንግስት መጽደቅ እና የመጀመሪያው ምርጫ መካሄድ በለውጡ ላይ የተጣለውን ተስፋ ያጠናከሩ አዎንታዊ ክስተቶች ነበሩ፡፡
በአናቱም ምንም እንኳ የመጀመሪያዎቹ አስር አመታት በህወሓት የበላይነት ላይ የተመሰረተ አስተዳደር የነበረ ቢሆንም፣ ስርዓቱ የጋርዮሽ አመራርን (Collective leadership) የሚከተል መሆኑ በበጎ እንዲታይ አድርጎት ነበር (ይህ የሆነው ድርጅቱ በትጥቅ ትግሉ ዘመን በዚህ መልኩ በተቃኘ መተዳደሪያ ደንብ ይመራ ስለነበረ ነው)፡፡ በዚህ የፖለቲካ ጨዋታ ህግ መሰረትም ለሁሉም የሀገሪቱ ጉዳይ (ለኦሮሚያ፣ ለአማራ፣ ለደቡብና ለሌሎችም ክልሎች) የህወሓት አመራር በጋራ ያቅድ፤ በጋራ ይወስንም ነበር፡፡ በተለይ አቦይ ስብሃት ነጋ፣ መለስ ዜናዊ፣ ተወልደ ወ/ማርያም፣ ስዬ አብርሃ፣ አለምሰገድ ገ/አምላክ፣ አባይ ፀሐዬን የመሳሰሉ በርዕዮተ-ዓለም ትንተና የተራቀቁ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላት በውሳኔዎች እና በሚወጡ አዳዲስ አዋጆች ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ነበሩ፡፡
የተቀረው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴም ቢሆን ‹‹ተናግሮ የሚሰማ›› ከመሆኑም ባሻገር በስብሰባዎች ላይ ሳይቀር ያላመነበትን ሃሳብ በግልፅ የመተቸትና የመቃወም አቅም ነበረው፡፡ በእርግጥ ይህ በህወሓት የአመራር አባል የተያዘው ቡድናዊ አስተዳደር አክራሪ ብሄርተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ ‹‹የተዘጋች ቤተ-መቅደስ›› ተብላ በፖለቲካ ተንታኞች የምትተቸው የአልባንያ ሶሻሊስታዊ አስተዳደር አቀንቃኝ መሆኑ ስርዓቱ ወደ ስልጣን በመጣበት የመጀመሪያዎቹ ዓመት ተስፋ ተጥሎባቸው ለነበሩ የፖለቲካ ማሻሻያዎች መምከን ዋነኛ ምክንያት ነበር፡፡
ከ1993-2004
ይህ ዘመን ህወሓት/ኢህአዴግ ወደ መለስ፤ የማዕከላዊ መንግስት መዋቅርም ወደ አንድ ግለሰብ የበላይነት የተቀየረበት ተብሎ ሊመደብ የሚችል ነው፡፡ በዚህ ወቅት የነበረው የስርዓቱ ገፅታ በአንድ ‹‹ጠንካራ ሰው›› (Strong man) ላይ የተመሰረተ ቢሆንም በጥቅሉ ዓመታዊው የሀገሪቱ ገቢ እድገት ያሳየበት፣ የመንግስት መቀመጫ አዲስ አበባም የተሻለ መሰረተ-ልማት የተካሄደባት ወቅት ነው፡፡ በተለይም የምርጫ 97 ‹‹ሱናሚ›› የፈጠረው ድንጋጤ ገዥውን ፓርቲ ህዝብን ለማዳመጥ (ምንም እንኳ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የተገደበ ቢሆንም) የመሞከር ፍላጎት አሳይቷል፡፡
አቶ መለስ ለፒ.ኤች.ዲ ማሟያ ባዘጋጁት ጥናት ላይ ከማንችስተር እስከ ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲዎች ድረስ የተከራከሩበትን የ‹‹ልማታዊ መንግስት›› ፅንሰ ሀሳብን ወደ መሬት ለማውረድ ፍላጐት ያሳዩበትም ወቅት ነበር፡፡ ሃሳቡን ይበልጥ ለማስረፅ ከህልፈታቸው በኋላ በእርሳቸው እንደሚዘጋጅ በተነገረለት የፓርቲያቸው የንድፈ ሃሳብ መተንተኛ በሆነው ‹‹አዲስ ራዕይ›› መጽሔት ላይ የምዕራቡ ዓለም መሪ ሃሳብ በሆነው የሌብራል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ላይ የተመሰረተውን የነፃ ገበያ ፍልስፍና ‹‹ቆሞ ቀር›› ሲሉ ተችተው፤ በተቃራኒው ‹‹ከየትኛውም መብት በፊት ዳቦን ያስቀድማል›› የሚሉትን የእስያን በተለይም የቻይናን ገዥ ሃሳብ ‹‹ሩቅ አዳሪው የእስያ ኢኮኖሚ›› በማለት ከማቆለጳጰስ አልፈው፣ መንግስታቸው በዚህ መስመር የሚጓዝ በመሆኑ የዴሞክራሲው ጥያቄ ብዙም እንደማያሳስባቸው፤ እንዲሁም ‹‹ሀገሬን ማተራመስ ይፈልጋሉ›› ያሏቸውን የኒዮ-ሊበራሊስቶች ክፉ ስራ እንደሆነ በመጥቀስ በአደባባይ ተከራክረዋል፡፡
የሆነ ሆኖ ስርዓቱ ለአስር አመት ከተጓዘበት ከህወሓት ጉልበታዊ የጋርዮሽ አስተዳደር ወጥቶ ወደ አንድ ፈላጭ ቆራጭ ግለሰብ የመቀየሩ መግፍኤ ‹‹የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት›› የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ከተማሪነት ዘመናቸው ጀምሮ የትግራይ ብሄርተኝነትን ያቀነቅኑ ለነበሩት አብዛኞቹ የህወሓት አመራር አባላት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት በየትኛውም የዓለማችን ሀገራት ባሉ ጎረቤት ሀገራት መካከል ሊኖር በሚገባው የግንኙነት ማዕቀፍ ስር ገብቶ የሁለቱንም ጥቅም በማስከበር እንዲቀጥል የወሰዱት አቋም በአቶ መለስ አልተወደደላቸውም፡፡
እንዲሁም ከሳህል በረሃ አንስቶ በኢትዮጵያ ሀብት ኤርትራን የአፍሪካ ሲንጋፖር ለማድረግ በማለም እንቅስቃሴ ለጀመረው የኤርትራ መንግስት፣ ድንገቴው የኢትዮጵያ እርምጃ የፈጠረበት ብስጭትን ‹‹በግዛት ይገባኛል ጥያቄ›› ለማወራረድ ያደረገውን ወረራ ‹‹በምን አይነት ሁናቴ ማስተናገድ አለብን?›› የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ ከአቶ መለስ በቀር ጠቅላላ የህወሓት አመራር አንድ አይነት አቋም መያዙ መለስን ቂም አስቋጥሯል፡፡
በተለይም ልዩነቱን ተከትሎ ከህወሓት የወጣው ቡድን የአቶ መለስን በአንድ ወገን ከኤርትራ
መወለድን በማስጮኽ የሄደበት መንገድ የጦርነቱ ጉዳይ ፋታ የማይሰጥ ባይሆን ኖሮ፣ ስልጣናቸውን እስከ ማሳጣት የሚደርስ ‹‹አዳሪ ስጋት›› ውስጥ ከትቷቸው ነበር፡፡ እናም የኤርትራን ወራሪ ኃይል ከኢትዮጵያ ድንበር በማባረር ካተኮሩ ጓደኞቻቸው ጋር ከፈጠሩት ግጭት በበላይነት ለመውጣት ያዘጋጁትን ቼዝ፣ ጦርነቱ በቆመ ማግስት በመተግበር ባልጠበቁት ሁናቴ ቡድናዊውን የህወሓት አመራር አፈራርሰው ስልጣኑን ጠቀለሉት፡፡ ከዚያ በኋላ እስከ ዕለተ-ሞታቸው የማይገፋ እና የማይደረስባቸው ብቸኛው መሪ ሆነው ዘለቁ፡፡
መወለድን በማስጮኽ የሄደበት መንገድ የጦርነቱ ጉዳይ ፋታ የማይሰጥ ባይሆን ኖሮ፣ ስልጣናቸውን እስከ ማሳጣት የሚደርስ ‹‹አዳሪ ስጋት›› ውስጥ ከትቷቸው ነበር፡፡ እናም የኤርትራን ወራሪ ኃይል ከኢትዮጵያ ድንበር በማባረር ካተኮሩ ጓደኞቻቸው ጋር ከፈጠሩት ግጭት በበላይነት ለመውጣት ያዘጋጁትን ቼዝ፣ ጦርነቱ በቆመ ማግስት በመተግበር ባልጠበቁት ሁናቴ ቡድናዊውን የህወሓት አመራር አፈራርሰው ስልጣኑን ጠቀለሉት፡፡ ከዚያ በኋላ እስከ ዕለተ-ሞታቸው የማይገፋ እና የማይደረስባቸው ብቸኛው መሪ ሆነው ዘለቁ፡፡
አቶ መለስ በጋርዮሹ አመራር አባላት መካከል የተፈጠረውን ችግር ከፓርቲያቸው ህገ-ደንብ ውጪ ሄደው ቢፈቱትም በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከጎናቸው የነበሩት ምዕራባውያን ‹‹ቡራኬ›› አልተለያቸውም፡፡ ምክንያቱም የምዕራቡ ዓለም ፍላጎት ጥቂት የፖለቲካ መሻሻሎች ይደረግ ዘንድ ጫና እየፈጠሩ ጥቅማቸውን ማስከበር በመሆኑ፤ መለስ ያውም ‹‹አክራሪ ሶሻሊስቶች›› ከሚል ፍረጃ ጋር ስላፈራረሱት የጋርዮሽ አመራር እና ስለጣሱት የህወሓት መተዳደሪያ ደንብ የሚያለቃቅሱበት ፍላጎቱም ጊዜውም አልነበራቸውም፡፡
በእርግጥ አቶ መለስ በራስ ተነሳሽነት ‹‹ቀጣዩ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ይደረጋል››፣ ‹‹የብሄር አደረጃጀትን ተደግፎ የቆመው ኢህአዴግም ከግንባር ወደ ወጥ ፓርቲ ይቀየራል››፣ ‹‹የፕሬስ ነፃነትም ከዚህ በተሻለ ይከበራል››… ሲሉ ቃል ገብተው ነበር፡፡ በተጨማሪም የተባረሩት የህወሓት የጋርዮሽ አመራር አባላት በሌሎቹ የግንባሩ ፓርቲዎች ላይ ከመደጋገፍ ይልቅ ተፅዕኖ የማሳደር ፖሊሲን ከማራመድ አልፈው ‹‹ጠባብ ብሄርተኞች›› እንደነበሩ በማጎን ለጠቀለሉት ስልጣን ቅቡልነት ከእነብአዴን ሙሉ ድጋፍ ለማግኘት ተጠቅመውበታል፡፡
ከ2005…
ከአስራ አንድ አመት በላይ በሀገሪቱ ብቸኛው ጠንካራ ሰው የነበሩት የአቶ መለስ ዜናዊ ህይወት ድንገት በማለፉ፣ ኢህአዴግ ያለ ጊዜው ሶስተኛውን ምዕራፍ (ገፅታ) እንዲገልጥ የተገደደ ይመስላል፡፡ አዲሱን ገፅታም ተከትሎ አስተዳደሩ ከአንድ ሰው ወደ ጋርዮሻዊ አመራር ተቀይሯል፡፡ እናም በመለስ ዘመን አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው የቆዩ ጥቂት የአመራር አባላት፣ በመለስ ህልፈት ማግስት ካደሩበት የተናጥል አገዛዝ ነፃ ወጥተው የራሳቸውን ቡድናዊ አመራር መመስረት ችለዋል፡፡ በዚህ ጽሁፍም አሁን ያለው መንግስት በአቶ መለስ ይመራ ከነበረው አስተዳደር የወረሳቸውን ባህሪያት እና በቀጣይ ሊገጥመው የሚችለውን ተግዳሮት ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
አሮጌው አቁማዳ…
የንፅፅራችን አንዱ ተጠየቅ የሚያተኩረው ከመለስ በኋላ የተደረጉ የፖለቲካ ማሻሻያዎችን (ካሉ) መፈተሽ ነው፡፡ በእርግጥ ሁለቱም አምባገነን አገዛዝን የሚከተሉ ቢሆንም የመጨረሻውን ውጤት የማይቀይር፣ ነገር ግን አንዳቸው ከሌላቸው የተለየ የራሳቸው የሆነ መገለጫዎች አሏቸው፡፡ መለስ በዘመናቸው ያነበሩት አስተዳደር ጉልበት የገነነበት ቢሆንም ‹‹ብልጣ ብልጥ አምባገነንነት›› ተብሎ ሊመደብ የሚችል ነው፡፡ የዚህ ማሳያው እርሳቸው የሚፈልጉትን ህገ-ወጥ ድርጊት የሚተገብሩት በቀጥታ ህጉን በመደፍጠጥ ሳይሆን በእጅ አዙር በመሆኑ ነው፡፡
ይህንን የአቶ መለስ ስልት የሚተቹ የፖለቲካ ተንታኞች ‹‹ስልጣኑን ለሚቀናቀ እና ህዝባዊ ጥያቄ ለሚያነሳ፣ እንዲሁም ተቃዋሚዎቹን እና ጠንካራ ነፃ ፕሬሶችን ለማፈን የሚወስደውን ህገ-ወጥ እርምጃ አዋጆች እና ህጎችን ጠምዝዞ ከመተርጎም አልፎ በተቋሞችም የሚጠቀም›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ለዚህ ድምዳሜያቸው በማሳያነት የፀረ ሽብር፣ የፕሬስ፣ የመያዶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አዳዲስ ህጎች በዋናነት ይጠቅሳሉ፡፡
ከዚህ በታቃራኒው በአቶ መለስ ማለፍ ያንሰራራው የህወሓት ኃይል ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት ወደ ነበረው የጋርዮሽ አመራር የተመለሰ ቢመስልም፣ መለስ ይከተሉት ከነበረው ብልጣ ብልጥ (ህግን የሚያጣቅስ) አምባገነን አካሄድ ወጥቶ በግልፅ ያሻውን የሚያደርግ፣ ለህግ እና ለተቋማት ህልውና የማይጨነቅ የሚመስልባቸው ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ ምናልባት በዚህ ኃይል ላይ ተፅእኖ የፈጠረበት ‹‹መለስ ስልጣኑን ያቆየው በማፈን እና በማሰር ነው›› የሚል አመለካከት በመውረሱ ይመስለኛል፡፡ (በነገራችን ላይ ከ1983-1993 ዓ.ም ድረስ በነበረው የህወሓት ጋርዮሻዊ አመራር እና ከመለስ ህልፈት በኋላ ወደ ስልጣን በወጣው የህወሓት አመራር መካከል ተመሳስሎዎች ቢኖሩም መሰረታዊ ልዩነቶች አሉ፡፡
የቀድሞው ብሄርተኛነቱ አሁን ካሉት በእጅጉ የከረረ ነው፤ እንዲሁም ሁሉም የትጥቅ ትግሉ መሪዎች የነበሩ ሲሆን፣ ብዙዎቹ የአሁኖቹ የአመራሩ አባላት በትጥቅ ትግሉ ዘመን አመራር ያልነበሩ እና ያልታገሉ ልሂቃኖች መሆናቸው ይታወሳል) በጥቅሉ ሲታይ ስርዓቱ በመለስ ዘመን ከነበረው ‹‹አስመሳይ››ነት ወጥቶ ምክንያታዊ ወዳልሆነ ጉልበተኝነት ማዘንበሉን ከሚያመላክቱ ነጥቦች ውስጥ የመጀመሪያው የእስልምና እምነት ተከታዮች እያቀረቡ ያለውን ‹‹የሃይማኖት ነፃነት ይከበር›› ጥያቄን ለማፈን አዲሱ አስተዳደር የሄደበት የጉልበት መንገድ ነው፡፡ ምንድር ነው የሆነው? በቀጥታ የእንቅስቃሴው አባሪ ናቸው ሲሉ የፈረጇቸውን ሰዎች ሰብስበው በማሰር የእመቃ እርምጃ ወሰዱ፡፡
በግልፅ እንደሚታወቀው የእስልምና እምነት ተከታዮች አስራ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ መስርተው በቤተ-እምነታቸው ጥያቄያቸውን ማቅረብ የጀመሩት ከታህሳስ 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ሆኖም መለስ ከአደባባይ ከራቁ ወይም ‹‹ህይወታቸው አልፏል››፤ ‹‹የለም! በደህና ሁኔታ ህክምናቸውን እየተከታተሉ ነው›› የሚሉ ውዝግቦች በይፋ መሰማት ከጀመሩ በኋላ (ሐምሌ 15 ቀን 2004 ዓ.ም.) መንግስት የሃይል እርምጃ ከመውሰድም አልፎ የእንቅስቃሴውን መሪዎች ‹‹በአሸባሪነት›› ወንጅሎ አስሯል፡፡ ‹‹የእምነቱ ተከታዮች ከሀይማኖታዊ ጥያቄዎች አልፈው ወደ ፖለቲካዊ አመፅ የመቀየር አዝማሚያ አሳይተዋል›› የሚል መከራከሪያ እንዳይቀርብ እንኳ እንቅስቃሴው የኮሚቴው አባላት ከታሰሩ በኋላም፣ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ፍፁም ሰላማዊ ከመሆኑም በተጨማሪ ከተነሳበት አውድ ሳይወጣ መቀጠሉ ነው፡፡
ይህ ጥንቃቄም ስርዓቱ ለህገ-ወጥ እርምጃው መከራከሪያ ሊያቀርብ የሚችልበትን ክፍተት አልተወለትም (ምናልባት የአፈሳ እስሩ በመለስ ዘመን ቢሆን ኖሮ ይህንን ያህል ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ፣ ይህንን ያህል የፀጥታ አስከባሪ ተሰዋ ወይም ተጎዳ፣ ንፁሀኖች ጉዳት ደረሰባቸው፣ የሀገሪቱን ስርአት በኃይል ለማፍረስ የመንግስትን እንቅስቃሴ አደናቀፉ፣ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች የሆኑት የአረብ ሀገራት እና ህገ መንግስቱን በኃይል ለመናድ የሚሞክሩ ኃይሎች በእንቅስቃሴው ውስጥ አሉበት… ሲሉ ወንጅለው መንግስት እና ሃይማኖት መለያየታቸውን የሚገልፀውን የህገ-መንግስት አንቀጽ በማብራራት ህጋዊ ለማስመል የሚያቀርቡት መከራከሪያ አያጡም ነበር፡፡
ሆኖም አሁን ያለው አስተዳደር በዚህ ደረጃ ወርዶ ለይምሰል እንኳ መከራከር አለመቻሉ በአካሄድ ላይ ያለውን ልዩነት የሚያሳይ ይመስለኛል) ሌላው በመለስ ዘመን ከነበረው ብልጣ ብልጥ (አስመሳይ) አምባገነንነት የተለየ መሆኑን የሚያመላክተው፣ በዛው በሐምሌ ወር በሀገሪቱ የፕሬስ ታሪክ የመጀመሪያ በሆነ መልኩ ‹‹ፍትህ ጋዜጣ››ን መጀመሪያ ማተሚያ ቤቱ ቅድመ-ምርመራ በማድረግ እንዳይታተም አድርጎ ካሳደረ በኋላ በማግስቱ የፍትህ ሚንስቴር አቃቢያን ህግ ወደ ማተሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ በመግባት፣ ህገ-መንግስቱ በአንቀፅ 29 ቁጥር 3 የሚከለክለውን ቅድመ-ምርመራ በመጣስ ያልታተመውን ጋዜጣ ካነበቡ በኋላ እንዲታተም አድርገው የወረሱበት መንገድ ይጠቀሳል፡፡
ከዚህ በኋላም አዲሱ አስተዳደር በፈጠረው የማሸበር እርምጃ እና ተቋማት ላይ ባሳደረው ተፅእኖ ከፍትህ በተጨማሪ ፍኖተ-ነፃነት፣ ነጋድራስ፣ ሰለፊያ፣ ተው-ቱል ኢስላም የተባሉ ጋዜጦች፣ እንዲሁም የሙስሊሞች ጉዳይ፣ አል-ኢስላም እና መርያም የተሰኙ መጽሔቶች ከህትመት ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ እነዚህ በአደባባይ የተፈፀሙ ህገ-ወጥ ድርጊቶች አዲሱ አስተዳደር እንደ መለስ ዘመን ለይስሙላ እንኳን ለህጋዊነት ያለመጨነቁን ያመላክታል፡፡ በአጠቃላይ ማሳያዎቹ በመለስ መንግስት እና በወራሾቻቸው መካከል ያለው ተመሳሳይነት የውጤት እንጂ ያካሄድ ያለመሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ሆኖ ስርዓቱ ዛሬም ድረስ የተረጋጋ አይመስልም፡፡
ያለመረጋጋቱ ማሣያዎች
በባለፈው የመፅሄቱ ህትመት እንደ ዘረዘርኩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ህገ-መንግስታዊ ስልጣን ከህግ ውጪ ተሸራርፎ ለሌሎች ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ስልጣን መሰጠቱ ያለመረጋገጋቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሌላው ህገ-መንግስቱ በግልፅ ሃይማኖት እና መንግስት የተለያዩ መሆናቸውን መደንገጉ እየታወቀ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ያሳዩት ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ በጫና ከሀገር እና ከሀላፊነታቸው እንዲባረሩ የተደረጉትን የኦርቶዶክስ እምነት ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ሀገራቸው መጥተው የቀድሞ የጵጵስና ወንበራቸውን እንዲረከቡ የፃፉት ደብዳቤን መጥቀስ ይቻላል፡፡
መቼም ፕሬዚዳንቱ ይህ ጉዳይ የእምነቱ የበላይ የሆነው የሲኖዶሱ ሀላፊነት ብቻ እንደሆነ አይጠፋቸውም፡፡ ከሲኖዶሱ እውቅና ውጪም ፓትርያርኩን ወደ ስልጣን ለማምጣት መሞከር ህገ መንግስቱን የሚፃረር አካሄድ መሆኑን ያውቃሉ፡፡ እናም ይህንን እርምጃ ሲወስዱ ሊከተል የሚችለው የፖለቲካ ክስረትንም ሆነ ትርፍ ሳያሰሉ ነው የገቡበት ማለቱ ያስቸግራል፡፡
በእኔ እምነት ፕሬዚዳንቱ ደብዳቤውን የፃፉት ፍቃድ የሚጠይቁት ወይም ሊያማክሩት የሚችሉ ማዕከላዊ መንግስት ባለመኖሩ ይመስለኛል፡፡ በአቶ መለስ ዘመን ቢሆን ይህንን አይነት ኢ-ህገ-መንግስታዊ ስራ ይሰራሉ ብሎ ማመን ከባድ ነው፡፡ ጉዳዩን ከለጠጥነው ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ‹‹አይዞህ›› ያላቸው አንድ ሀይል ከጀርባቸው ሊኖር ይችላል እስከማለት ድረስ መጠርጠር ይቻላል፡፡ በአናቱም የእርሳቸው ድርጊት ይፋ ከሆነ በኋላ ‹‹ተሳስቼአለሁ›› ብለው መልሰው ደብዳቤውን እንዲስቡ ወይም ይቅርታ እንዲጠይቁ የተጫናቸው ሌላ ሀይል አለ ማለትም እንችላለን፡፡
ይህንንም ኃይል ህወሓት ነው ብሎ መገመትም ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንቱ ተመልሰው ወደ ስልጣናቸው እንዲመጡ የጠየቁት በህወሓት የተባረሩ ፓትርያርክ ከመሆናቸው አኳያ፣ ጣልቃ ገብነቱ በቀጥታ የሚላተመው ከህወሓት የቀድሞ እርምጃ ጋር መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሃሳብ በቀላሉ ወደ መሬት ስናወርደው የሚኖረው ትርጓሜ፣ ፕሬዚዳንት ግርማ ሀይል ያለው የተረጋጋ ማዕከላዊ መንግስት አለ ብለው ቢያስቡ ኖሮ እንዲህ አይነቱን የድፍረት ስራ ባልሰሩ ነበር የሚል ይሆናል፡፡
ሶስቱ ተግዳሮቶች
አዲሱ መንግስት በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ለመሻገር አዳጋች የሚሆኑበት በዋናነት ሶስት ተግዳሮቶች ይጠብቁታል፡-
፩
የመጀመሪያው ተግዳሮት በተለይም ከታችኛው ማህበረሰብ የሚነሳ ኢኮኖሚን መሰረት የሚያደርገው ነው፡፡ ይኸውም ከቀን ቀን ቁጥሩ እያሻቀበ ያለው ስራ አጥነት፣ አስከፊ ድህነት፣ የኑሮ ውድነት፣ እየተባባሰ የመጣው የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እጥረት…. ለአዲሱ መንግስት የመረጋጊያ ጊዜ የማይሰጡ ተግዳሮቶች መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ችግሮች በአቶ መለስ ዘመንም ነበሩ፡፡ ሆኖም የመለስ አስተዳደር በ‹‹ጠንካራ ሰው›› ላይ የተመሰረተ ስለነበረ ችግሮቹን ተከትሎ የሚነሱ ጥያቄዎችን በእንጭጭነታቸው በካድሬዎቹ ተፅእኖ ማኮላሸት፣ የመከላከያ ወረዳዎችን ጥሰው አደባባይ የወጡ (የመምህራንን የደሞዝ ጭማሪ የመሳሰሉ) ጥያቄዎችን ደግሞ በኃይል ማፈኑ ተሳክቶለታል፡፡ በአናቱም የተለያዩ ማስቀየሻ ስልቶችን (የትራንስፎርሜሽን እቅድ፣ የተለያዩ የግድብ ስራዎች፣ የአነስተኛ ስራ ፈጠራ መስክ…) በመጠቀም ጊዜ መግዛት የቻለበት ሁናቴ ነበር፡፡
ለአዲሱ መንግስት ምናልባት የቀረው ብቸኛ የመጫወቻ ካርታ አቶ መለስ በስልጣን ዘመናቸው በአለም አቀፍ መድረክ ሳይቀር የእነ ቻይናን ተሞክሮ እየጠቀሱ ያቀነቅኑት የ‹‹ልማታዊ መንግስት›› መከራከሪያን ከሚገባው በላይ ማጎን ነው፡፡ በእርግጥ ይህንንም ቢሆን አጥብቆ ለመያዝ አሁንም የግድ ፓርቲው በአንድ ጠንካራ ሰው መመራት ይኖርበታል፡፡ ሆኖም በመሬት ባለው እውነታ መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ የግንባሩን ኃይል ጠቅልሎ የሚይዝ ጉልበታም ሰው ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም መለስ በዘመናቸው ማዕከላዊነትን በማጥበቅ ስልጣኑን ጠቅልለው ከያዙ በኋላ ከእርሳቸው በመቀጠል፣ ሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ‹‹ተፅእኖ ፈጣሪ›› ሊባል የሚችል የፓርቲያቸው የአመራር አባል እንዳይኖር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም በመለስ ሞት ማግስት፣ ለመለስ ከልክ ያለፈ አገር አቀፍ አድናቆት እንዲፈጠር መደረጉ እና እጅግ የገዘፉ ታላቅ ሰው እንደነበሩ ለማስመሰል መሞከሩ በእንዲህ አይነት የጭንቅ ጊዜ አንድ ‹‹ጠንካራ ሰው›› እንዳይወጣ እንቅፋት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ መላምቶቹ ሁሉ ከሽፈው ጠንካራ ሰው መውጣት ቢችል እንኳ፣ በመለስ የሙት መንፈስ የተገነባው የእርሳቸው ‹‹የማይደረስበት ታላቅ መሪነት›› ጋር መላትም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀስ በቀስ ‹‹የመለስ ራዕይ›› የተባለውን እያደበዘዘው ይሄዳል፡፡ በዚህ ትንተና መሰረት በቀጣይ ከላይ የተጠቀሱት እና መሰል ጥያቄዎች ወደ ጠረጴዛው የሚቀርቡ ከሆነ ለአዲሱ መንግስት ሁለት አማራጭ ብቻ የሚኖረው ይመስለኛል፡፡ በፍቃዱ ስልጣኑን መልቀቅ አልያም በጎርፉ ተጠራርጎ መወሰድ፡፡፡
፪
ሁለተኛው ተግዳሮት ከራሱ ከኢህአዴግ የሚነሳ ነው የሚሆነው፡፡ ይኸውም አራቱ ፓርቲዎች በግንባሩ ውስጥ ያላቸውን አሰላለፍ ይመለከታል፡፡ ህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደኢህዴን እንደየቅደም ተከተላቸው ከላይ ወደታች የሚወርድ ባልተፃፈ የፓርቲው ህገ-ደንብ ተስማምተው የተቀበሉት የፖለቲካ ጉልበት አላቸው፡፡ ይሁንና በአባል ድርጅቶች ውስጥ ይህ ሁኔታ እንደ ከዚህ ቀደሙ በነበረበት እንዲቀጥል ያለመፈለግ አዝማሚያ መታየቱ ለኢህአዴግ በራሱ ላይ የተጠመደ ጊዜ የሚቆጥር ቦንብ እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡የውስጥ ትግሉን ይበልጥ ሊያከረው የሚችለው ህወሓት ለሃያ አንድ አመት የተለያዩ መንግስታዊ መዋቅሮችን በመጠቀም ይዞ ያቆየውን የበላይነት፣ ከዚህ በኋላም ለማስቀጠል የሚያደርገው ሙከራ የአቶ መለስን ህልፈት ተከትሎ (‹‹ስማዊ›› ቢሆንም) ሌሎቹ አባል ድርጅቶች ከፍተኛ የመንግስት ስልጣንን የመቃመስ እድል ማግኘታቸው እንደ ቀድሞ የተመቻቸ ላይሆንለት መቻሉ ነው፡፡
ከሁሉም የከፋ የሚሆነው የእዚህ አይነት ፉክክሮች እየጠነከሩ በሄዱ ቁጥር መንግስት ፖሊሲዎችንም ሆነ እቅዶችን በሚፈለገው ፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚኖረው አቅም በእጅጉ የተዳከመና የተበጣጠሰ መሆኑ ነው፡፡ በልማታዊ መንግስት ኃልዮት መሰረት ከአገሪቱ በአጠቃላይ የሚሰበሰበው ገቢ በማዕከላዊ መንግስት ስር ተጠራቅሞ ‹‹ልማታዊ›› ወደሚባሉት የፖሊሲ ትግበራዎች ፈሰስ ይደረጋል፡፡ ይህ በአቶ መለስ ዘመን በከፊልም ቢሆን የተሳካ የነበረ ቢመስልም፣ የተለያዩ የኃይል ቡድኖች ባሉበት የኃ/ማርያም መንግስት ይህ ስለመከወኑ እጅግ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ በተለይም እንደአሁኑ ተቋማዊ የስልጣን ተዋረዶች ሳይጠበቁ ሲቀሩ የሚከሰተው ቅጥ-ያጣ ሙሰኝነት ‹‹ልማታዊ›› የሚባሉትን ተግባራት ሁሉ ያደናቅፋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አቶ መለስ ተቆጣጥረውት የነበረው የስርዓቱ ልሂቃን ጥቅመኝ ግንኙነት አፈትልኮ ከወጣ ሁኔታዎችን የከፋ ያደርጋቸዋል፡፡
በተጨማሪም በኃይል መተናነቁ የተሸነፉ የሚመስሉት ብአዴን እና ኦህዴድ እንዲሁም በሩቁ የቆሙት አጋር ድርጅቶች ፌደራሊዝሙ ከምር እንዲተገበር ቢጠይቁ ራሱን የቻለ አደጋ ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም ብሔርን መሰረት አድርጎ የተዋቀረ የፌደራል ስርዓት ህልውናውን ከፈተና ለማዳን ያለው አማራጭ አስተማማኝ ዴሞክራሲ፣ አሊያም ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስትን መመስረት ብቻ ነውና፡፡ ወቅታዊው የኢህአዴግ ፖለቲካ ደግሞ ለሁለቱም አማራጮች የተመቸ አይደለም፡፡ የሆነ ሆኖ ከላይ አንድ እና ሁለት ተብለው የተጠቀሱት የስርዓቱ ፈተናዎች ወደ መከላከያ እና ፖሊስ ሰራዊት ተቋማት የሚዛመቱ ከሆነ ደግሞ የአርማጌዶውን ቀን በእጅጉ ያቀርቡታል፡፡
፫
ሶስተኛው ተግዳሮት ደግሞ ከሀገር ውጭ ሊመጣ የሚችል ነው፡፡ ይህ ተግዳሮት በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መንግስትን እንደጠላት የሚቆጥሩት ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ግብፅን የሚመለከት ነው፡፡ እነዚህ ሀገራት በቀጥታ እና ቀጥታ ባልሆነ መንገድ በአዲሱ መንግስት ላይ ለመፍጠር የሚሞክሩት ጫና ቀላል አይሆንም፡፡ሶስቱም ሀገራት የተለያየ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ የኢትዮጵያ መንግስትን በተመለከተ ተመሳሳይ አቋም ለመያዝ አይቸገሩም፡፡ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ጥንካሬ ያላት ግብፅ የውስጧን የቤት ስራ እስክትጨርስ ለይደር ያቆየችው ‹‹የአባይ ግድብ›› ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ለየለት ጦርነት አምርታ ከነበረችው ኤርትራም ሆነ፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ከይዞታቸው ከተባረሩት የሶማሊያ አሸባሪዎች ጋር በጋራ እንድትሰራ የምትገደድበት ገፊ ምክንያት ነው፡፡
ሁለተኛው የውጭ ተግዳሮት ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው አዲሱ መንግስት፣ አቶ መለስ ያደርጉት እንደነበረው ምዕራባውያንን አሳምኖ እርዳታ እና ብድር ለማግኘት የሚያስችል ዲፕሎማሲያዊ ብልጠት ያለው አለመሆኑ ነው፡፡ ምዕራባውያን በተለምዶ እንደ አሰራር የሚጠቀሙበት ልማድ ሊደራደሩት የሚችሉት ወሳኝ ሰው ወይም ቡድን የግድ መፈለጋቸው ነው፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ አውድ ደግሞ ይህንን መስፈርት አሟልቶ ከሀገራቱ ጋር በመደራደር ብድርና እርዳታ ማስገኘት የሚችል ከፊት የወጣ ኃይል ወይም ‹‹ስትሮንግ ማን›› የለም፡፡
በእነዚህ አበዳሪ ሀገራት ያልተፃፈ ህግ፣ ተበዳሪ ሀገር “Policy predictability” (የፖሊሲ ተገማችነት) አለው ለማለት የሚያስችል የተረጋጋ ተቋማዊ ስርዓት ሊኖረው ግድ ነው፡፡ የአቶ መለስ አስተዳደር ለረዥም አመታት በስልጣን ላይ የቆየ በመሆኑ ይህ ችግር አልነበረበትም፡፡ ምዕራባውያኑም በቀላሉ በቀጣዩ አመት ኢትዮጵያ የሚኖራት ፖሊሲ ምን አይነት ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚችሉባቸው ገፊ ምክንያቶች ነበራቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ መለስ ቢኖሩ ኖሮ እንኳን የሚቀጥለው ዓመት ፖሊሲ ላይ ሊኖር የሚችል መሸጋሸግም ሆነ የፖሊሲ ግብ ቀርቶ የ2007ቱን ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጤትን መገመቱ ከባድ አይደለም፡፡ ከልምድ ያውቁታል፡፡
ሆኖም አዲሱ መንግስትን በተመለከተ በሚቀጥለው አመት ‹‹እንዲህ ሊያደርግ ይችላል›› ወይም ‹‹ይህንን አይነት ፖሊሲ ይከተላል›› ብሎ ለመገመት የሚያስችል ግብአት ዛሬ ላይ ማግኘት አይቻልም፡፡ እናም ይህ አይነቱ መለኪያ ባልተሟላበት አበዳሪ ሀገራት ገንዘብ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ይታወቃል፡፡
ስጋት የዋጠው ተስፋ
ኢህአዴግ በቀጣይ እነዚህን ተግዳሮቶች አልፎ ሊወጣ የሚችልባቸው ሁለት አማራጮች አሉት፡፡ ይኸውም የአቶ መለስ ህልፈት በተነገረ ማግስት የትግል ጓዳቸው የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ በአሜሪካን ሀገር ከኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ‹‹የአቶ መለስ አለመኖር ወይንም ህልፈት ትልቅ የፖለቲካ ክፍተት በኢህአዴግ ውስጥ ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ይህን በመገንዘብ የፖለቲካ አካሄድ ክለሳ በማድረግ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ ችግሮችን ሊያሽር የሚችል፣ ህዝቦችን በጋራና በአንድነት ሊያሰባስብ የሚችል እርምጃ ካልወሰደ እስካአሁን ድረስ ሲጠራቀሙ የቆዩ ችግሮች ደርሰውበት አገሪቱን ችግር ውስጥ ሊከታት ይችላል›› ያሉትን ምክር በመቀበል፣ ያለምንም ማመንታት ጥብቅ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ኢህአዴግ ለዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ የሆኑ ህጎችን ማውጣት፣ ወይም በተጨባጭ መተግበር፣ የምርጫ ፖለቲካውን ጨምድዶ የያዘውን ስውር እጅ ማንሳት፣ ያለቅድመ ሁኔታ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትይዩ ተቀራርቦ መነጋገር እና የፖለቲካ አውዱን ማስፋት፤ በያዝነው ዓመት ሚያዝያ ወር የሚካሄደውን የአዲስ አበባ እና የአካባቢ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች ሁሉ ተአማኒ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ማመቻቸት… በግንባሩ ላይ ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችን ይቀንሳል፡፡ (በነገራችን ላይ ገዥው ፓርቲ ቀጣዩ ምርጫን አስመልክቶ ሰላሳ ሶስት ፓርቲዎች በጋራ ያቀረቧቸውን አጀንዳዎች መግፋቱና ‹‹የስነ-ምግባሩን ደንብ ካልፈረመ አልወያይም›› በማለት መድረክን ወደ ጎን በመግፋት መቀጠሉ የፖለቲካ ማሻሻያውን ተስፋ ሩቅ ያደርገዋል)::
በተጨማሪም የፕሬስ ነፃነትን በሚታይ መልኩ ከምርጫ 97 በፊት ወደነበረበት እንዲመለስ ማድረግ፣ ወይም ከዚያ የተሻለ ነፃነት እንዲኖራቸው ዕድል መስጠት፤ የፀረ-ሽብር ህጉን ጨምሮ በአፋኝነታቸው የሚተቹ አዋጆችን በሙሉ ማንሳት፣ ተቋማት ነፃ እንዲሆኑ መፍቀድ፣ የህሊና እስረኞችን መፍታት እና የመሳሰሉትን ማሻሻያዎች ማድረጉ ስጋት ለዋጠው አዲሱ አመራር ተስፋ የሚሰጥ ብቸኛ አማራጭ ይመስለኛል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ‹‹በመቃብራችን ላይ ነው›› መባል ከተጀመረ ግን ፈረንጅኛው እንደሚለው ‹‹እውነቱ ግድግዳው ላይ ተፅፏል››፡፡
No comments:
Post a Comment