Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Monday, December 31, 2012

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቁጣቸውን እየገለጹ ነው በሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ከአገር መባረር ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቁጣቸውን እየገለጹ ነው

http://ethiopia.ecadf.netdna-cdn.com/Amharic/wp-content/uploads/2012/12/gubaye-ethiopian-orthodox-300x224.jpg?84cd58
ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ከብፁዓን አበው ጋር
ሐራ ዘተዋሕዶ

  • ሊቀ ካህናት ለጉባኤው መግለጫ ይቅርታ እንዲጠይቁ ለሰዓታት ጫና ተደርጎባቸዋል
  • ‹‹አጀንዳዬ ሃይማኖታዊ ነው፤ የሠራኹት ስሕተት ይኹን የምጠይቀው ይቅርታ የለም !!››
  • የሰላምና አንድነት ጉባኤው መግለጫ እንደሚያወጣ ይጠበቃል
  • መንግሥት በወሰደው ርምጃ የመንበረ ፕትርክና ዓላሚዎቹ ጳጳሳት እጅ እንዳለበት ታምኖበታል
 በተወሰኑ ጳጳሳት ግፊትና በመንግሥት የደኅንነት ኀይሎች ርምጃ ትላንት ምሽት ከኢትዮጵያ ተገደው እንዲወጡ የተደረጉት ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ከጥቂት ሰዓታት በፊት አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ደርሰዋል፤ በሰላምና አንድነት ጉባኤው አባልም አቀባበል እንደተደረገላቸው ታውቋል፡፡ 


በሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ላይ ስለተፈጸመው ተግባር መረጃው የደረሳቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአሁኑ ወቅት በጉዳዩ ላይ እየመከሩበት ሲኾን ርምጃውን አነሣስተዋል፤ ግፊት አሳድረዋል በተባሉ ግለሰቦችና ጳጳሳት ላይ ጠንካራ አቋም ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ ጳጳሳቱን ያሳተፈውና ለመንግሥት ጣልቃ ገብነት ማረጋገጫ ተደርጎ የተወሰደው ይኸው ርምጃ የማክሰኞውን የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ እንዳያጋግለው ተፈርቷል፡፡

በቀዳሚው የዜና ዘገባችን እንዳስነበብነው÷ ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ትላንት ከሰዓት በኋላ ፒያሳ ከሚገኘው ቤታቸው ወደ ቦሌ ለስብሰባ ቀጠሮ ብለው ከወጡ በኋላ ነበር ታግተው ቆይተው በዚያው ‹‹ትኬት ተቆርጦላቸው›› ተገደው እንዲወጡ የተደረገው፡፡ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ዋነኛው ሰው የኾኑት ልኡኩ በግዳጅ እንዲወጡ ከመደረጋቸው በፊት እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ባገቷቸው የደኅንነት ኀይሎች በተለያዩ ጥያቄዎችና ተጽዕኖዎች ሲዋከቡ እንደነበር ተገልጧል፡፡ ረቡዕ ዕለት አዲስ አበባ በደረሱበት ወቅትም ሊቀ ካህናትና አብረዋቸው የነበሩት ሌላው ልኡክ በልዩ ክፍል እንዲገቡ ተደርጎ ጥብቅ ፍተሻ እንደተካሄደባቸው ታውቋል፡፡

ሊቀ ካህናት በደኅንነት ኀይሎች ቁጥጥር ሥር በቆዩባቸው ሰዓታት የሰላምና አንድነት ጉባኤው ታኅሣሥ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ላወጣው ‹‹በዘለፋ የተሞላ፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት የተዳፈረ፣ የአስታራቂነትን መርሕ የጣሰ ነው›› ለተባለው መግለጫ ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠይቁ ከፍተኛ ጫና ተደርጎባቸው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ 

ቅ/ሲኖዶሱ የዕርቀ ሰላም ልኡካኑን ማሳሰቢያ ችላ ብሎ አስመራጭ ኮሚቴ በመሠየሙ ሳቢያ በዳላሱ የሰላም ጉባኤ የተደረሰበትን ስምምነት ለማስከበርና የዕርቀ ሰላም ሂደቱን ከዕንቅፋት ለመጠበቅ የወጣ ነው የተባለውን መግለጫ እንደሚያምኑበት በማስረገጥ በአቋማቸው የጸኑት ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ÷ ‹‹አጀንዳዬ ሃይማኖታዊ ነው፤ የሠራኹት ስሕተት ይኹን የምጠይቀው ይቅርታ የለም፤ ያሻችኹን ርምጃ መውሰድ ትችላላችኹ!!›› ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

‹‹በዕርቀ ሰላም ስም የፓትርያሪክ ምርጫውን ጊዜ በማራዘም የፖሊቲካ ዓላማን የማራመድ፣ ብጥብጥ የመፍጠር የተቃውሞ ኀይሎች አጀንዳ አለ፤›› ብሎ የሚያምነው መንግሥት ‹‹ዕርቀ ሰላሙን እደግፋለኹ›› ቢልም ምርጫውን አስቀድሞ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ የዕርቅና ሰላም ሂደቱ በተጓዳኝ ወይም ከምርጫው በኋላ ሊካሄድ እንደሚችል አቋም መያዙ ይነገራል፡፡ በመንግሥት እምነት ‹‹ዕርቁ ይቅደም›› የሚሉ ወገኖች ‹‹የሥልጣን ተሻሚዎችና ጥቅመኞች›› እንጂ የሰላምና አንድነት ወዳዶች አይደሉም፡፡ ይህን የመንግሥት አቋም የተቀበሉና በዚህ አቋም ሥር ተግነው የመንግሥትን አካላት የሚገፋፉ ግለሰቦችና በመንበሩ ለመቀመጥ የሚያልሙ ጳጳሳት በሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ላይ ለተወሰደው ርምጃ የበኩላቸውን ሚና መጫወታቸው ነው የተገለጸው፡፡

ከመንግሥት ጋራ ያላቸውን የጠበቀ ትስስር በመጠቀም ለርምጃው ግንባር ቀደም ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ሁለት ጳጳሳት በዋናነት የተቀሩት ሦስቱ በደጋፊነት ተጠቅሰው ስማቸው የደረሰን ቢኾንም ለጊዜው ከመግለጽ ተቆጥበናል፡፡ ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ከአገር እንዲወጡ ከመደረጉ በፊት በሰላም ልኡክነታቸው ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ እንዳይገቡ የተላለፈባቸው እገዳ በቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ይኹን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደማይታወቅ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ዕርቀ ሰላሙን በሚመለከት የሚታየው ተጽዕኖ ዙሪያ መለስ ነው፡፡ የቅ/ሲኖዶሱ የዕርቀ ሰላም ልኡካን በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ተወክለው የአስመራጭ ኮሚቴውን መቋቋም በመቃወም በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ መግለጫ መስጠታቸው ለማስጠንቀቂያ ዳርጓቸዋል፡፡ ልኡካኑ ወደ አገር ቤት ከመመለሳቸው ሦስት ቀናት በፊት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተጠርተው ከተጨማሪ መግለጫ እንዲቆጠቡ ጫና የተደረገባቸው ሲኾን ለልኡካን ቡድኑ በጸሐፊነት የተመደቡት ንቡረ እድ ኤልያስ ከኤምባሲው ሰዎች ጋራ ያረቀቁት ነው በተባለው የተቃውሞ መግለጫ ላይም እንዲፈርሙ መገደዳቸው ተገልጧል፡፡ 

 በተመሳሳይ ኹኔታ ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› በማለት የሚዲያ መግለጫ የሰጡና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የሚታወቁ አገልጋዮችም በደኅንነት ወከባ ውስጥ መሰንበታቸው በየጊዜው ስንዘግብ ቆይተናል፡፡ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ወይም የሰላምና አንድነት ጉባኤው በተፈጸመው ተግባር ላይ መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment