Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Monday, December 31, 2012

ቅዱስ ሲኖዶሱ የማን ነው? የእኛ ነው ወይስ?

(ከመልዕክተ ተዋሕዶ - ዘሮኪ/ PDF)፦ እንግዲህ ላለፉት 20 ዓመታት ከችግራችን ጋር ተወልዶ፥ ያደገው መንግሥት ፥ አቋሙን በግልጽ አሳውቆናል።  “ነገ ልትዳሪ ነው ሲሏት፥ ካልታዘልኩ አላምንም እንዳለችው ሙሽራ መሆኑ ይብቃን፥ እርማችንን እናውጣ። ስለ ነገ እናስብ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን እናስብ፥ ስለ አባቶቻችን እናስብ። የግዴታ ማክሰኞን መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም።
 
ቅዱስ ሲኖዶስ በመጪው ማክሰኞ  በሚያደርገው ስብሰባ ላይ፥ ካስታወሰን መልዕክታችንን መነጋገር ያለብን፥ ዛሬንና ነገ ብቻ ነው። የመንግሥትን አቋም ባይገርመንም የሚጠበቅ ስለሆነ ሰምተነዋል። የቅዱስ ሲኖዶስ ግን ማክሰኞ ይለይለታል። ቅዱስ ሲኖዶስ የማነው ወይ የኛ የኦርቶዶክስያዊያኑ ነው! አለበለዚያ፥ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለመንግሥት ነው። እንደኔ እንደኔ  የቅዱስ ሲኖዶስም ቢሆን፥ ግልጽ ይመስለኛል።  ይህንን ለመረዳት፥ ወደ ፊት ሁለት ቀን ጠብቆ ማየት ሳይሆን፥ ወደ ላ ብዙ ዓመታትን ማስታወስ ይበቃል። 
 
ያለፉትን ሁለት ሶስት ሳምንታት ብቻ እንኳን ስርመረምሩ፥ እውነታው ቅዱስ ሲኖዶስ ከመንግሥት ፍላጎት ውጪ አንድ ቀን እንኳን በነጻ አስተሳሰቡ ውሎ ማደር እንዳልቻለ ግልጽ ነው። ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የቅዱስ ሲኖዶስ አካሄድን ነቅፈው፥ መሆን ያለበትን ተናግረው ውለው ሳያድሩ የደንነት ክፍሉ ኃላፊ “ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ ዝም ነው ሰኟቸው። በግዴታም ፈረሙ። ነገ ወደ አገር መግቢያ የላችሁም ተባሉ። ተስማሙም። ይህ በቂ አይመስላችሁምን? ጠብቀን እንስማው፥ ካላችሁ ግን ፥ ታገሱ።
የተዋሕዶ ልጆች፥ ዛሬ ቅዱስ አትናቴዎስ፥ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፥ ኢትዮጵያዊው ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ፥ በአካል የሉም። ማን እነሱን ይሁን? ቡዙ የምንወዳቸው፥ የምናደንቃቸው ብጹአን ሊቃነ አልነበሩምን እንዴ? የት ሄዱ? ቢያንስ ካሉን ሊቃነ ጳጳሳት አንዳቸውስ !! እንኳን፥ ስለፍቅርና የቤተ ክርስቲያን አንድነት፥ በአደባባይ መናገር ይፍሩ? የተዋሕዶ ልጆች፥ ስለ አንቀጽ 39፣ ወይም ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፥ ስለ ኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት፣ወይም ዘረኝነት እኮ አይደለም ጥያቄው! ያንን ያነሳ እማ መድረሻም የለውም። 
 
ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት መናገር ብቻ!! በግልጽ ቤተ ክርስቲያን አንድ ትሁን ማለት፤ ከፓትርያርክ ምርጫ በፊት ዕርቀ ሰላም ይውረድ ማለት፤ የፈረሰው ይስተካከል፥ የጠመመው ይቅና፥ ብሎ መናገር፥ መመስከር አስፈርቷቸዋል። በእናንተ ፍርሀት የተነሳ፥ ነገ መሥዋዕትነት ሊከፍሉ የተዘጋጁ፥ የተዋሕዶ ልጆች ያሣፍሯችኋል። ዛሬ እናንተ ለቤተክርስቲያናችሁ ብትቆሙ፥ ነገ ከእናንተ ጋር ቆመን ዋጋ ብንከፍል ያምርብን ነበር። ግና፥ ይህ የሚሆን አይመስለኝም።
ከዚህ በኋላ መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያለን ሁሉ፥ በየሰበካችን ነገ በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየት ይጠበቅብናል። ምን ብናደርግ ይሻላል? የሚሰሙ ብፁዓን አባቶች አሉ ብሎ የሚያምን በስልክም፣ በኢሜልም እንዲሁም በአካል ተገኝቶ ያስረዳ። ሌላው፥ መላው ሰባያነ ወንጌል መምህራን ነገ ይህንን ጉዳይ አንስታችሁ ምን ማረግ እንደሚሻል፥ ተወያዩ። መምህራኑ ዝም ካሉ ደግሞ፥ ምእመናን ጠይቁ፥ መብታችሁ ነው። 
 
በየኤምባሲውና የመንግሥትና የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ባሉበት፥ አቤቱታችሁን አሰሙ። ሰላማዊ ሰልፎች ከቤተ ክህነቱ ቢሮ ጀምሮ እስከ ሊቃነ ጳጳሳቱ መኖሪያ ድረስ፥ ይደረጉ። ማበረ ቅዱሳንም ሆነ ሌሎች መንፈሳያን ማበራት ከቤተ ክህነቱ ጋር ያላችሁ ግንኙነት እንዳይበላሽ በመጋት መደረግ የሚገባውን ሳትዘገዩ ዛሬ አድርጉት! ያለበለዚያ የእናንተም አስፈላጊነት አጠያያቂ ይሆናል። ትምህርተ ወንጌልን ማዳረስ፣ ገዳማትን ማጠናከር፣ አረጋያንን መርዳት፣ መምህራንን በሚያስፈልጋቸው መርዳት የሚቻለው ቤተ ክርስቲያን ሕልውናዋ ተጠብቆ፥ አንድነቷ ተከብሮ ሲገኝ ብቻ ነው። አር ባይነት በታሪክ ያስወቅሳል። ያስፈርድማል።
ለምርጫ ራሳችሁን ያዘጋጃችሁት አባቶቻችን ልብ ግዙ። እነ ብፁዕ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ እነ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ወዘተ የቤተ ክርስቲያንን ችግር ከውስጥም ከውጭም ሆናችሁ አይታችሁታል። ይህ ኃላፊ ወቅት አያታላችሁ። ነገ ይቆይ እንጂ፥ በኦርቶዶክሳያን መዋዕትነት፣ይነጋል።
በዚህ አጋጣሚ፥ ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ፣ መልአከ መንክራት ቀሲስ አንዱዓለም፣ ዲያቆን አንዱዓለም፣ ቀሲስ ፋሲል ወዘተ ከገለልተኛው ወገንና በውጭው ዓለም የሚገኙትን አባቶች፥ የወከሉትን በአጠቃላይ፥ በመላው የሰላምና አንድነት ኮሜቴ ስም፥ ላደረጉት ታሪክ ማይረሳው፥ ቤተ ክርስቲያን የማትረሳው ትልቅ አርአያነት ያለው ሥራ እግዚአብሔር አምላክ በሰማያት ዋጋችሁን ይክፈላችሁ እላለሁ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment