ኢሳት ዜና:- “እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በንብረት ውርስ ምክንያት መከራከር አንፈልግም፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ
ፍርድ ቤት ከዛሬ በኋላ እንዳልቀርብ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ይሰጥልኝ፤” ሲል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፍርድ ቤትን
ጠየቀ።
በፈጠራ የሽብርተኝነት ወንጀል ተከሶ የ18 ዓመት እና ፅኑ እሥራትየተፈረደበት ጋዜጠኛ እስክንድር
ነጋ፣ ዓቃቤ ሕግ እንዲወረስ ስለጠየቀበት ንብረት ቤተሰቡም ሆነ እሱ መከራከር እንደማይፈልጉ ለፍርድ ቤቱ
ያስታወቀው ትናንት ነው።
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፦” በሽብርተኝነት አዋጁ በተቀመጠው አንቀጽ መሠረት፣
በሽብር ወንጀል የተቀጣ ግለሰብ ንብረት መወረስ እንዳለበት ያዛል ስለሚል የአንድነቱ አመራር የአንዷለም አራጌ፣
የጋዜጠና እስክንድር ነጋና የጋዜጠኛ አበበ በለው ንብረት ይወረስልኝ ብሏል።
ንብረታቸው እንዲወረስ ከተጠየቀባቸው ፍርደኞች መካከል በዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ የተወሰነበት አንዱዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ትናንት ፍርድ ቤት የቀረቡት አብረው ነበር።
በፌዴራል
ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው የነበሩት የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ አንዱዓለም
አራጌና ባለቤታቸው ዶክተር ሰላም አስቻለው፣ እንዲወረስባቸው የተጠየቀውን አንድ የቤት መኪና በሚመለከት ተቃውሞ
እንዳላቸው ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
የአቶ አንዱዓለም አራጌ ባለቤት ዶክተር ሰላም ለፍርድ ቤቱ
ባቀረቡት የተቃውሞ ደብዳቤ፤ እንዲወረስባቸው የተጠየቀው የቤት መኪና፣ በዕድሜ ልክ ለተቀጡት ባለቤታቸው ስንቅ
ማመላለሻና ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ማድረሻና መመለሻ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡
ሌላው ዓቃቤ ሕግ ፦”ንብረቱ ይወረስልኝ” በማለት ጥያቄ ያቀረበበት በሌለበት ጥፋተኛ ተብሎ በ15 ዓመታት ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ የተወሰነበትና በአሜሪካ የሚኖረው ጋዜጠኛ አበበ በለው ነው።
ዐቃቤ
ህግ በጋዜጠኛ አበበ በለው ንብረት ጉዳይ ባለድርሻ ይሆናሉ ያላቸውን የባለቤቱ አድራሻ ማግኘት አለመቻሉንም
ለፍርድ ቤቱ በማስታወቅ <<ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት >> ሲል አመልክቷል፡፡ ይሁንና ጋዜጠኛ አበበ በለው ቀደም ሲል በጉዳዩ ዙሪያ በሰጠው አስተያዬት ኢትዮጵያ ውስጥ ይወረሳል የተባለው ቤት የሱ ንብረት እንዳልሆነ አስታውቋል።
መንግስት
ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ኢትዮጵያ ውስጥ ንብረት ያላችሁ በውጪ የምትኖሩ ሰዎች አርፋችሁ ካልተቀመጣችሁና
መንግስትን ከተቃወማችሁ ንብረታችሁ ይወረሳል ለማለት እንደሆነ ያመለከተው ጋዜጠኛ አበበ፤ ቤቱ የሱ አይደለም እንጂ
ቢሆን እንኳ ስለፍትህ እና ስለ ነፃነት ሲል ከለሚያደረገው ትግል ለንብረት ሲል ሊያፈገፍግ እንደማይችል ማስታወቁ
አይዘነጋም።
በትናንቱ የፍርድ ቤት ውሎ ከ አንዷለም በመቀጠል ተናጋሪ የነበረው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
ከተቀመጠበት የተከሳሾች መቀመጫ ሳጥን ውስጥ ቆሞ የሚያቀርበው ሐሳብ እንዳለው ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት
በማግኘቱ ጥያቄውን በአጭሩ አቅርቧል።
“እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በንብረት ውርስ ምክንያት መከራከር አንፈልግም፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ፍርድ ቤት ከዛሬ በኋላ እንዳልቀርብ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ይሰጥልኝ፤” በማለት ፡፡
ፍርድ
ቤቱ የሁሉንም ወገኖች ሐሳብ ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ውሳኔ፣ ለአቶ አበበ በለው ባለቤትና ለጋዜጠኛ እስክንድር
ባለቤት መጥርያ እንዲደርሳቸውና መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ በማዘዝ፣ የሚቀርበውን መቃወሚያ ለማየትና ውሳኔ
ለማስተላለፍ ለኅዳር 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
No comments:
Post a Comment