Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Friday, October 19, 2012

ቂል የያዘው ሰይፍ

(ፕሮፌሰር መስፍን):-
Sibhat Nega
በቅርቡ አቶ ስብሐት በአደረገው ቃለ መጠይቅ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተሾመው ወያኔ ዱሮም አስቦበት ወንበሩን ከአማርኛ ተናጋሪዎችና ከኦርቶዶክስ አማኞች ለማጽዳት በተዘጋጀበት እቅድ ነበር ብሎአል፤ ልብ ላለው አነጋገሩ በሁለት በኩል ስለት ያለው  ነው፤ ከፊት ለፊት የተሰነዘረው አማርኛ ተናጋሪውንና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማኙን ለመምተር ነው፤ ቂል የሚያደርገው አማራ የሚባል ጎሣ ቢኖርም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት በአማርኛ ተናጋሪዎች ታጥሮ ትግሬንና ኦሮሞን፣ ወላይታንና ጉራጌን፣ ሌሎችንም የማይነካ መስሎት ከባድ ስሕትት ላይ መውደቁ ነው፤ ከሁሉም በላይ እሱን የሚያህል ሰው የተክለ ሃይማኖትን ታሪክ አለማወቁ ያሳዝናል፡፡

አማራንና የኦርቶዶክስ ተከታዮችን መትሮ ሲመለስ ደግሞ ሰይፉ የሚቀላው ወላይታንና ጴንጤነትን፣ ምናልባትም እስልምናን ይሆናል፤ አቶ ስብሐት በፊት ለፊት የተናገረው ገና የዛሬ ሀያ አንድ ዓመት ‹‹እንዳያንሰራራ አድርገን አከርካሪቱን እንሰብረዋለን›› ተብሎ ያለቀለትን አማራ ዛሬ ወንበር ማጣቱን ለማብሰር አልነበረም፤ ይህ በጣም ግልጽና ከማንም ያልተሰወረው እውነት ነበር፤ ስውር ዓላማም አለው፤ ያንን ብዙ ሰው አይገነዘበውም ይሆናል፤ በአቶ ስብሐት አነጋገር ውስጥ ዋናውና ተንኮልን ያዘለው ዓላማ ወንበሩን የያዘው ዋናው የወላይታ ጴንጤ ሲሆን ምክትሉ ደግሞ እስላም መሆናቸውን ለመናገር ያለው ፍላጎት ላይ ነው፤  
 
ከአቶ ስብሐት ነጋ በቀር የአዲሶቹን ሹሞች ዘርና ሃይማኖት ከጉዳይ ያስገባ ያለ አይመስለኝም፤ አቶ ስብሐት በፊት-ለፊት ዓላማው ተስፈንጣሪ ተራማጅ ሲመስል በስውሩ የተንኮል ዓላማው ግን ኋላ-ቀር ወግ-አጥባቂ ይሆናል፤ በዘርና በሃይማኖት ላይ ሲያተኩር ዋናውን ቁም-ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትሉ ሰዎች፣ ከዚያም ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ፈጽሞ ዘንግቶታል፤ ለእኛ ትልቁ ነገር ይህ ነው፤ በሁለታችን መሀከል ያለው ልዩነት ስብሐት ኢትዮጵያውያንን የሚያዛምዳቸውን ሁሉ አያይም፤ እኔ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን የሚለያያቸውን ሁሉ አላይም፡፡
መጥፎ ልማድ

 (አንድ አድርገን ጥቅምት 7 2005 ዓ.ም)፡- የዛሬ ዓመት ግድም ቅዱስ ሲኖዶስ መርጦ ያስቀመጣቸውን ብጹአን አባቶቻችንን አቶ ስብሐት ተነስቶ የስድብ ውርድብኝ ሲያወርድባቸው ቤተክርስትያኒቱንም ሆነ አባቶችን ወክሎ መናገር የደፈሩ አባቶችን አልተመለከትንም ፤ “ቤተክርስትያኒቱ በጳጳሳቱ አማካኝነት ገደል አፋፍ ላይ ናት” ፤ ጳጳሳት እንዲህ ናቸው…” በማለት አቦይ ስብሐት ሲናገር መልስ የሰጠ አካል አልነበረም ፤  ሰውየው ሳይናገር ሳይሆን ተናግሮ እንደሚያስብ የሚያውቁት ይናገራሉ ፤ 
 
ይህ የመሰለው ያለአግባብ ዘለፋ በምዕመኑ ዘንድ የሚያሳድረውን የውስጥ መሰበር ማንም አልተመለከተውም ፤ አፉን ለከፈተ ሁላ ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ ብጹአን አባቶች መልስ ይስጡ እያልን ሳይሆን ከአንድ ትልቅ የሚባልና የመንግስትን ቁልፍ ቦታ የያዘ ሰው ያለ አግባብ ንግግር በቤተክርስቲያን እና በአባቶች ላይ ሲናገር ግን ዝም ተብሎ መመልከት ያለበት አይመስለንም ፤ የተሰደቡት አባቶች ብቻ ሳይሆኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች ጭምር መሆናቸው መዘንጋት የለበትም ፤ ዝምታችንን ጥቅሙንና ጉዳቱን በአግባቡ ያወቅነው አይመስለንም ፤ “ዝም አይነቅዝ” የሚለው የሀገራችን ብሂል የሚባልበት ቦታ እንዳለ ሁላ ዝምታም የሚነቅዝበት ውሎ አድሮም ችግር የሚያመጣበት ሁኔታም እንዳለ መዘንጋት መቻል የለብንም ፤ 
በየጊዜው ከመንግስትም ይሁን ከተለያዩ አካላት የሚነሱትን ዘለፋዎች እና ስም ማጥፋቶች በጊዜው መልስ መስጠት ካልቻልን ውሎ አድሮ የምንሰጠው ምላሽ ውሃ ያዘለ ላይሆን ይችላል የሚል እምነትም ስላለን ጭምር ነው ፤ እስከ አሁን ድረስ ቤተክርስቲያኒቱ ስትሰደብ ዝም ፤ ጳጳሳቱ ሲሰደቡ ዝም ፤ ማህበራት ስማቸው  ሲጠፋ ዝም ፤ ምዕመኑም ስም እየተሰጠው ሲንገላታ ዝም ካልን ነገ ህዝቡ ላይ የሚያመጣው Psychological impact ሊናጤነው ይገባል ፤ ሰው ዝም ሲል ሁለት አይነት ምልከታ አለው አንድም “ጉዳዩ አያገባኝም ፤ ጉዳዬም ጉዳዬ አይደለም” በማለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውስጡ እየተቃጠለና በነገሩ እየተንቦገቦገ አቅም ስለሌለው ብቻ ዝም ማለቱ ነው ፤ ብዙዎች በየትኛው ውስጥ እንዳሉ ማወቅ አዳጋች አይሆንም፡፡ 

No comments:

Post a Comment