Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Friday, October 19, 2012

ኢትዮጵያ ከመሀይምነት ባልተላቀቁ ሰዎች ብዛት ከዓለማችን ሶስተኛ ናት ተባለ

Ethiopia

ኢሳት ዜና:-በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲ ፒ)፤ ከመሀይምነት የተላቀቁ ሰዎች ብዛትን በተመለከተ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ ኢትዮጵያ ከዓለማችን በርካታ አገራት ከመጨረሻ ሶስተኛ መሆኗን ይፋ አደረገ።
 
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ከሶስተኛ አለም አገራት ውስጥ አጥንቶ ይፋ ባደረገው በዚህ ጥናት፤ በኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ህዝብ ውስጥ፤ 28 በመቶው ብቻ ፊደል የቆጠሩና መጻፍና ማንበብ የሚችሉ ናቸው ብሎ፤ ከዓለም አገራት መጨረሻ ከተቀመጡት ከማሊና ደቡብ ሱዳን ቀጥሎ፤ ኢትዮጵያ ከመጨረሻ ሶስተኛ ናት ብሏል።

በዚህ ጥናት መሰረት፤ ህዝቦቻቸውን በበቂ ሁኔታ በማስተማር ከህዝብ ቁጥራቸው 99.9 በመቶ በማስተማር ኩባ አንደኛ፤ ህንድ 74.1 በመቶ የተማረ ህዝብ በመያዝ 2ኛ ስትሆን፤ በኢትዮጵያ 28 ከመቶ ብቻ ከአጠቃላዩ ህዝብ ውስጥ ከመሀይምነት የተላቀቀ ነው። ኢትዮጵያ ከ184 አገራት ውስጥ 182ኛ ሆና ነው በ3ኛ ደረጃ የተፈረጀችው።


በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጥናት መሰረት፤ ኒጀርና ቡርኪናፋሶ የህዝባቸውን 28.7 በመቶ በማስተማር፤ 180ኛ ደረጃ ላይ ሲመደቡ፤ ቻድ 33.6 አስተምራ 179ኛ፤ ሶማሊያ ደግሞ 35.9 በመቶ በማስተማር 178ኛ ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን በተነደፈው የልማት መርሀ ግብር መሰረት በርካታ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፤ ትምህርትም ተስፋፍቷል ቢልም፤  ከመሀይምነት የተላቀቀው ህዝብ ቁጥር 28 ከመቶው ብቻ መሆኑ፤ የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ መሰረታዊ ችግር እንዳለበት ጠቋሚ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

በቀደመው መንግስት አስተዳደር በዓለማቀፍ ድርጅቶች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ 60 ከመቶው የኢትዮጵያ ህዝብ ማነበብና መጻፍ መቻሉ ታውቋል። ለዚህም የቀድሞው መንግስት የጸረ-መሀይምነት ዘመቻ አስተዋጽኦ በማድረጉ አለማቀፍ ተሸላሚ እንደነበር ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment