ኢሳት ዜና:-ከኢህአዴግ ኢንዶውመንት ድርጅቶች አንዱ እንደሆነ የሚታወቀውና ራሱን “የግል ራዲዮ ጣቢያ”
በማለት የሚጠራው ራዲዮ ፋና “ኢትዮፒካሊንክ” በሚል ርእስ በኤፍ ኤም የሚያሰራጨው ፕሮግራም ከአቶ መለስ ዜናዊ፤
ዜና ዕረፍት ዘገባ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ቁጣ ታገደ፡፡
አቶ መለስ፤ ዜና ዕረፍታቸው በይፋ በመንግስት
ከተነገረ በኃላ እስከቀብር ዕለት ድረስ የጣቢያው መደበኛ ፕሮግራሞች ታጥፈው የነበረ ቢሆንም የኢትዮፒካሊንክ
አዘጋጆች ቅዳሜ ነሐሴ 19 ቀን 2004 ዓ.ም ከአቶ መለስ ሕልፈተ ሕይወት ጋር በተያያዘ ልዩ ፕሮግራም እንዳላቸው
በመግለጽ ጣቢያውን አስፈቅደው ያስተላለፉት ፕሮግራም በተለይ የአቶ መለስ ዜናዊን ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍንን
አስቆጥቷል፡፡
በዝግጅቱ ” የአቶ መለስን መርዶ በስካይፒ ለመጀመሪያ ገዜ ለቤተሰብ ያረዳችው ልጃቸው ስመሃል መሆኗን፣አቶ መለስ ለቤተሰቦቻቸው ጊዜ እንዳልነበራቸው ” የሚያትቱ ዘገባዎች ቀርበው ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ዘገባ በወቅቱ ትኩስ ሐዘን ላይ የነበሩትን ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ከማሰቆጣቱም በላይ “መረጃውን ከየት አመጣችሁት” የሚል ቁጣ አዘል ጥያቄን አስነስቷል፡፡
የወ/ሮ
አዜብ ቁጣ በስልክ የወረደባቸው የጣቢያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወልዱ ይምሰል ወዲያው ፕሮግራሙን ማገዳቸው
ታውቋል፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት አዘጋጆቹ ባስተላለፉት ፕሮግራም ውስጥ ግድፈት እንደሌለ በማስረዳት በተደጋጋሚ
ለጣቢያው ኃላፊዎች ቢያስረዱም ምላሸ ማግኘት እንዳልቻሉ ምንጫችን ገልጸዋል።
ኢትዮፒካሊንክ
የተሰኘው የመዝናኛ ፕሮግራም እነአቶ ብርሃኔ ንጉሴን ጨምሮ አራት ሰዎች ከፋና ኤፍኤም የአየር ሰዓት ገዝተው ላለፉት
አምስት ዓመታት ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን በተለይ ቅዳሜ ምሸት የሚያቀርቡት “ውስጥ አዋቂ” የተሰኘ ፕሮግራም ብዙ
አድማጮች እንደነበረው ታውቋል።
ምንጮቻችን እንደጠቆሙት የኢትዮፒካሊንክ አዘጋጆች ጥፋተኛ ነን ብለው ባይምኑም ጣቢያውንና የአቶ መለስን ቤተሰቦችን ይቅርታ በመጠየቅ ፕሮግራሙን ለማስቀጠል ማቀዳቸው ተሰምቷል፡፡
No comments:
Post a Comment