ኢሳት ዜና:-ከተጀመረ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን የያዘውና180 አባላት ያሉት የኢህአዴግ ም/ቤት ጉባዔ በሞት በተለዩት
የግንባሩ ለቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ ምትክ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ሊቀመንበር አድርጎ ሲመርጥ የብአዴኑን
ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል አድርጎ መምረጡን ምንጮቻችን ጠቆሙ፡፡
ጉባዔው በዛሬው ውሎው በገጉት
ሲጠበቅ የነበረውን የግንባሩን ሊመንበር ምርጫ ያከናወነ ሲሆን አዲሱ ተመራጭ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የአገሪቱ
ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ምንጫችን እንዳለው በኢህአዴግ የእስከዛሬ ልምድ ግንባሩ ሊቀመንበር
ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆን ጠቁሞ ይህ ግን ተለምዶያዊ አሰራር እንጂ ሊቀመንበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል የሚል
በግንባሩ መተዳደሪያ ደንብም ሆነ የመንግስት ሕግ አለመኖሩን አስታውሶአል፡፡በዚህ መሰረት ግንባሩ ከሊቀመንበሩ ከአቶ
ኃይለማርያም ውጪም ሊመርጥ የሚችልበት ዕድል ዝግ አለመሆኑን ያስታወሰው ምንጫችን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን
የአቶ ኃይለማርያም መሾም አጠራጣሪ አለመሆኑን አመልክቶአል፡፡
ተሿሚዎቹ በመጪው ጥር ወይም የካቲት ወር
አራቱን ፓርቲዎች ማለትም ህወሃት፣ብአዴን፣ኦህዴድ፣ደኢህዴን ጉባዔ በማካሄድ እያንዳንዳቸው ዘጠኝ የሥራ አስፈጻሚ
ኮሚቴ አባላትን፣የቁጥጥር ኮሚሸን አባላትን፣እያንዳንዳቸው 45 አባላት ያሉት የም/ቤት አባላትን የሚመርጡ ሲሆን
የእያንዳንዱ የሥራ አስፈጻሚ አባላት የኢህአዴግን 36 የሥራ አስፈጻሚ አባላትን ይመሰርታሉ፡፡ ከፓርቲዎቹ ጉባዔ
በኃላ በመቀሌ ከተማ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የኢህአዴግ ዘጠነኛ ጉባዔ ላይ የግንባሩ ሊቀመንበርና ምክትል
ሊቀመንበር በድጋሚ ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢህአዴግ ስምንተኛ ድርጅታዊ ጉባዔ በአዳማ ከነሃሴ 28
እስከ መስከረም 4 ቀን 2003 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን በሕገደንቡ መሰረት ቀጣዩ ጉባዔ ከሁለት እስከ ሁለት ዓመት
ከስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድና የአመራር ምርጫም በየሁለት ዓመቱ እንደሚከናወን ይደነግጋል፡፡ በዚሁ
መሰረት በያዝነው መስከረም ወር ጉባዔውን ማካሄድ ቢቻልም የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ግን ጉባዔው ከስድስት ወራት
በኃላ እንዲካሄድ ከሳምንት በፊት ባደረገው ስብሰባ ተስማምቶአል፡፡ይህ ውሳኔ ምናልባት አዲሶቹ አመራሮች
እንደሚፈለገው ውጤታማ ባይሆኑ ቶሎ ለመቀየር ዕድል ለማግኘት ሲባል ሆን ተብሎ የተደረገ ሳይሆን እንደማይቀር
ምንጫችን ጠቁሟል፡፡
የአቶ መለስ ዜናዊ ዜና ዕረፍት በይፋ ከተነገረ ዛሬ 25 ኛ ቀኑ ሲሆን በእነዚህ ቀናት አገሪቱ ያለ ጠ/ሚኒስትር በማን እንደምትመራ እንኳን ሳይታወቅ መቆየቷ የሚታወቅ ነው፡፡የአቶ ሀይለማርያም እና የአቶ ደመቀ መኮንን መመረጥ ብአዴን አሸናፊ ሆኖ መውጣቱን የሚያሳይ ነው በማለት ምንጫችን ገልጧል። አቶ ሀይለማርያም በምን ያክል ድምጽ እንደተመረጡ ለማወቅ አልተቻለም።
ዛሬ
ማምሻውን በሒልተን ሆቴል መግለጫ የሰጡት የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ
ሬድዋን ሁሴን የአገሬቱ ጠ/ሚኒስትር እና ምክትል ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና አቶ ደመቀ መኮንን
እንደሚሆኑ ጠ/ሚኒስትሩ ፓርላማው ሲከፈት ቃለመሃላ እንደሚፈጽሙ ተናግረዋል፡፡በዕረፍት ላይ ያለው የኢትዮጽያ ፓርላማ
በሕገመንግስቱ መሰረት በአበሻ አቆጣጠር በመስከረም ወር መጨረሻ የመጀመሪያው ሰኞ ተከፍቶ የዓመቱ ሥራውን
ይጀምራል፡፡
No comments:
Post a Comment