Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, June 20, 2012

መኢአድ በሰሜን ጐንደር የሚገኙ ሁለት አመራሮቹ የደረሱበት አለማወቁን ገለፀ -አንደኛው በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ታስሮ ይገኛል

By Feteh News paper, no. 192
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በሰሜን ጐንደር ወረዳዎች የሚገኙ አራት የፖለቲካ አመራሮቹ ግንቦት 23 እና 24/2004 ዓ.ም.በፖሊስ በሀይል ተወስደው የደረሱበት እንደማይታወቅ እና ሌላ አባልና አመራሩ በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጣቢያ እንደሚገኙ ፓርቲው ማረጋገጡን ለፍትሕ ገልጿል።

አቶ መለስ አሽሬ የጭልጋ ወረዳ መኢአድ ም/ቤት ሰብሳቢ ግንቦት 23 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ከመኖሪያ ቤታቸው ከ10 በላይ በታጠቁ የፌዴራል ፖሊሶች በሀይል ተወስደው የደረሱበት አለመታወቁ ተገልጿል። 

አቶ ስለሺ ጥጋቤ የጃናሞራ ወረዳ የመኢአድ ም/ቤት ሰብሳቢ ከላይ በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት ከመኖሪያ ቤታቸው ደባርቅ ከ10 በላይ በሆኑ የታጠቁ የፌዴራል ፖሊሶች በሀይል ተወስደው ለሁለት ቀናት የደረሱበት ሳይታወቅ ቀርቶ ነበር። ሆኖም ከግንቦት 25/2004 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጣቢያ እንደሚገኙ ትክክለኛ መረጃ ማግኘታቸውን የፓርቲው ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ታሪኩ ለፍትሕ ተናግረዋል። አያይዘውም ‹‹ለአቶ ስለሺ ምግብና አልባሳት ማቀበል እንጂ በአካል አግኝተን ማነጋገር አልቻልንም። ፖሊስ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ገልፆልናል›› ብለዋል፡፡

አቶ ታድሎ ተፈራ የሰሜን ጐንደር መኢአድ ጽ/ቤት የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሲሆኑ ግንቦት 24 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ከመኖሪያ ቤታቸው ጐንደር ከተማ በሀይል ተወስደው የደረሱበት አልታወቀም። አቶ ካሳሁን አክሊሉ የተባሉ የበክረ-ፅዮን በወቅን ከተማ የፓርቲው አደራጅም ከሚኖሩበት ከተማ በየጊዜው ያለማቋረጥ እንደሚደበደቡ፣ እንደሚታሰሩ፣ እንደሚዘረፉ፣ ቤታቸው እንደሚበረበር እና ሀብት ንብረታቸው እንደሚቀማ ምንጮች ለፍትሕ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአለሳ ጣቁሳ ወረዳ የቀድሞ የመኢአድ ፓርቲ አባል ነበሩ የተባሉት አቶ አይችሉም አያልም ባለፈው ወር ዘመድ ለመጠየቅ በሚል ምክንያት አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ዘመዳቸው የሆኑት አቶ አብርሃም ጌጡ ጊዜያዊ ስራ ካስጀመሯቸው በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ሰኞ ዕለት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ በፌዴራል ፖሊሶች ተይዘው ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

‹‹አይችሉም ተከራይቼ ከምኖርበት መኖሪያ ቤት አብሮኝ መኖር ጀምሮ ነበር፡፡ በዕለቱም ምሳ ለመብላት ወደ ቤት እያመራ እያለ ዘጠኝ ፌዴራል ፖሊሶች ይዘውት የእኔን ቤት ሰብረው በመግባት የተለያዩ መጽሐፍቶቼንና የፓርቲ ፕሮግራሞችን በመያዝ ወደ ማዕከላዊ ይዘውት ሄደዋል›› ያሉት አቶ አብርሃም፣ ስንቅ ከማቀበል ውጪ ተጠርጣሪ ዘመዳቸውን በአካል ማግኘትና ማነጋገር እንዳልቻሉ ለፍትሕ አስረድተዋል።

ጉዳዩንም ለማጣራት ወደ ሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ በተደጋጋሚ ስልክ ደውለን ነበር፡፡ ስልኩን በማንሳት ያነጋገሩን የመረጃ ባለሙያም ዝርዝር ጉዳዩን ካደመጡን በኋላ ወደተጠቀሱት ወረዳዎች ደውለው ያለውን ትክክለኛ መረጃ አጣርቼ እደውላለሁ ቢሉም በድጋሚ ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡

No comments:

Post a Comment