Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Tuesday, June 5, 2012

በጐንደር ፖሊስ የሟቾችን አስክሬን በመኪና መሬት ለመሬት አስጐተተ

 By Finote Netsanet news
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ጐንደር ዞን ታች አርማጭሆ ሳንጃ ከተማ በተኩስ ልውውጥ የተገደሉ ሁለት ሰዎች አስከሬን በመኪና ላይ ታስረው ከተማ ውስጥ መሬት ለመሬት መጐተቱን የዜና ምንጮቻችን ለዝግጅት ክፍላችን አስታወቁ፡፡ 

የዜና ምንጮቻችን እንደሚሉት “አቶ ሽንኩ ከፍያለውና አቶ ዳኛቸው አያሌው የተባሉ ሁለት ግለሰቦች ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸው መሬት ለመሬት ሲጐተት ውሏል”
ብለዋል፡፡ ምንጮች እንደሚሉት “አቶ ዳኛቸው አያሌው ከአንድ ግለሰብ ጋር በመጋጨቱ አካባቢውን ለቆ ሄዷል፡፡ ከመንግስት ጋር ፀብ አልነበረውም፡፡ ከዚያም ታጣቂዎች ሸፍተዋል በማለት ይገኛሉ የተባለበትን አካባቢ በመክበብ ተኩስ ከፈቱ፡፡ ሟቹም የተኩስ ልውውጥ እያደረጉ ሞቱ፡፡ መቀጠልም አስክሬናቸውን በመኪና ላይ አስረው በከተማ ውስጥ ከ8-11 መሬት ለመሬት ከጐተታቸው በኋላ መሐል አራዳ ላይ ጣሏቸው፡፡ ህዝብ እንዲመለከታቸው አደረጉ፡፡ አስክሬኑን ሲመለከቱ የመንፈስ ጭንቀት ተፈጥሮባቸው የጮሁ ያለቀሱ ሰዎች በፖሊስ ቆመጥ ተደብድበዋል” ይላሉ፡፡

በማያያዝም ሲናገሩ “የአቶ ዳኛቸው አያሌው አባት፣ እናትና አያትም በሥፍራው ነበሩ፡፡ አስከሬኑን ወስደው ለመቅበር ቢጠይቁ ተከልክለዋል፡፡ በ11 ሰዓት ላይ እግራቸው ላይ ገመድ አስረው ከፖሊስ ጣቢያ ጀርባ ዛፍ ላይ ሰቅለው ዘቅዝቀው አሳደሯቸው፡፡ በማግስቱ እንዲቀበሩ ሲወሰን ቤተሰብና የአካባቢው ህብረተሰብ ቤተክርስቲያን ለመቅበር ቢጠየቅ የአካባቢው ኃላፊዎችና ፖሊሶች ቤተክርስቲያን አይቀበሩም ብለው ከልክለው ሌላ ቦታ እንዲቀበሩ አድርገዋል፡፡” በማለት
በቅሬታ ይገልፃሉ፡፡

ምንጮች በመጨረሻም ሲናገሩ “የአካባቢው ህብረተሰብ እጅግ አዝኗል፡፡ በተለይ ከግድያው በኋላ ፖሊሶች በአስከሬኖቹ ላይ የፈፀሙት ድርጊት ከባህልና ወግ ያፈነገጠ ከሰብአዊ አስተሳሰብ የወጣ በመሆኑ እናዝናለን፡፡ ማንም ሰው በሠራው ወንጀል በሞትም ሊቀጣ ይችላል፡፡ አስክሬን ግን ክብር አለው፡ ፡ የቀብር ቦታም መከልከል ህገወጥ ተግባር ነው፡ ፡ አስክሬን ዘቅዝቆ ሰቅሎ ማሳደርስ ምን ማለት ነው? ይህንን ድርጊት የፈፀሙም ያስፈፀሙም በህግ ሊጠየቁ  ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የሳንጃ ከተማ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን ስለማይነሳ ዜናውን ለጊዜው ሚዛናዊ ማድረግ አልቻልንም፡፡

በተያያዘ ዜና በዚሁ በሰሜን ጐንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አብረሃ ጅራ ከተማ ዙሪያ “ለረጂም ዓመታት የቆየው የመሬት ግጭት አሁን በተባባሰ ሁኔታ ፍጥጫ መፍጠሩን” ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ምንጮቻችን እንደሚሉት “አካባቢው ከሱዳን ጋር ድንበር ነው፡፡ መንግስት የአካባቢውን መሬት ለሱዳኖች ማስረከብ ይፈልጋል፡፡ 

የአካባቢውን ህብረተሰብ ድንበሩን ለማስከበር ከሱዳኖች መሬቱን ሲከለከል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሱዳን ወግኖ የራሱን ዜጋ ይወጋል፡፡ በአካባቢው ያለው የመከላከያ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ለሱዳን ቆሞ ኢትዮጵያኖች ምንም ዓይነት የመከላከል ሥራ እንዳይሰሩ እያደረገ ነው፡፡” በማለት በአግርሞት ይገልጹታል፡፡

ምንጮች በመቀጠልም ሲገልጹ “ሰሞኑን መንግስት በተጨማሪ ለውጪ ዜጐችና ለባለሀብቶች ለመስጠት እቅድ ይዟል፡፡ ለእያንዳንዱ ገበሬ አንድ ሄክታር መሬት ብቻ ለመስጠት በማቀድ መሬት እያሸጋሸገ ነው፡፡ አንዱ ለፍቶ ያለሰለሰውን እርሻ ለሌላው ይመድባል፡፡ ገበሬው ግን አንዱ የአንዱን እርሻ ላለማረስ ቃል ተገባብቷል፡፡ የአካቢው ኃላፊዎች ግን እንዲያርስ እያስገደዱት ነው፡፡ በዚሁ ምክንያት ከሁለት ቀን በፊት ለሊት ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ፖሊስ ጣቢያውንናቀበሌ መስተዳደሩን ጽ/ቤት አቃጥለውታል፡፡ በዚህ የተነሳ የአካባቢውን ህብረተሰብ እየሰበሰቡ እያሰሩና እየደበደቡ ናቸው፡፡ የአካባቢውን ህዝብ ወደ መጥፎ  ድርጊት እየገፋፋት ነው፡፡ ህዝቡ በኩርፊያ ሥራቸውን በተጠንቀቅ ቆሞ እየተከታተለ ነው፡፡” ሲሉ ያብራራሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ “ፖሊስ ጣቢያውንና የቀበሌውን መስተዳድር ያቃጠሉት ምናልባትም ከመሬት ጋር በተያያዘ በሙስና የተነካኩ ግለሰቦች መረጃ ለማጥፋት የሠሩት ሥራ ነው፡፡” በማለት ጥርጣሬአቸውን ይገልፃሉ፡፡ ከመሬት ድልድሉ ጋር ተያይዞ የአካባቢውን መሬት ከሌላ ቦታ ለመቱ ሰዎች እየተሰጠ በመሆኑ የአካባቢው ሊቀመንበርና ቅሬታ ሰሚ በጉዳዩ ባለመስማማት አካባቢውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታ ሄደዋል” ይላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ መሬቱን የሚሸነሽኑት የመሬት አስተዳደሩና የወረዳው ፀጥታ ኃላፊውች ናቸው በማለት ይናገራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ግንቦት 20 ህዝቡ ከወጣ አይመለስም ተብሎ እንዳይከበር ሰሞኑን በደረሰን ዜና በዚሁ በሰሜን ጐንደር ተቃዋሚዎች
በህገወጥ መንገድ እየታሰሩ መሆናቸው ተጠቁሞአል፡፡

 ምንጮች እንደሚሉት “በምርጫ 2002 መኢአድን ወክለው ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተወዳዳሩ እየታሰሩ ናቸው፡፡ ከታሰሩት ውስጥ ታደለ ተፈራ የሰሜን ጐንደር የመኢአድ ም/ቤት ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ ስለሺ ጥጋቤ የጀናሞራ ወረዳ መኢአድ ኮሚቴ ሰብሳቢ መለስ አስሬ የጭልጋ ወረዳ መኢአድ ሰብሳቢ ሆነው ሲታገሉ የቆዩ ሲሆን ባለፈው ሐሙስና ዐርብ ምሽት በእያንዳንዱ ሰው ቤት ከአስር በላይ ፖሊሶች ተገኝተው ቤታቸውን እየበረበሩ አስረዋቸዋል፡፡” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ 

የእስረኞቹ ቤተሰቦች እንደሚሉት “ፖሊሶቹ የፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዳላሳዮቸውና ድርጊቱ ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪ በምሽት መከናወኑና እስረኞቹ የታሰሩበት ቦታ አለመታወቅ እንዳሳሰባቸው” ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል፡፡ እስረኞቹ ይገኙበታል ተብሎ የነበረው ደርጊ ፖሊስ ጣቢያና ጐንደር ፖሊስ ደውለን ለመጠየቅ ጥረት ብናደርግም ዜናውን ሚዛናዊ ማድረግ አልተቻለም፡፡

No comments:

Post a Comment