Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Thursday, June 7, 2012

አቶ መለስ ዜናዊ የህክምና ምርመራ ለማድረግ ብራሰልስ ገቡ

ኢሳት ዜና:- ግንቦት ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
አቶ መለስ ዛሬ በቤልጂየም ዋና ከተማ ብራሰል የተገኙት በህክምና ቀጠሮዋቸው መሰረት ነው። በአእምሮ እጢ በሽታ እንደተጠቁ የሚነገርላቸው አቶ መለስ፣  ብራሰልስ የገቡት  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑትን አቶ ብርሀነ ገብረክርስቶስን አስከትለው መሆኑን ከኢምባሲ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አምባሳደር ብርሀነ ከአቶ መለስ ጋር የመምጣታቸው ምክንያት ቀደም ሲል ለ10 አመታት ብራሰልስ በነበሩበት ወቅት የአቶ መለስን ህክምና ያመቻቹ ስለነበር ቀረቤታ አላቸው በሚል ነው። አቶ ብርሀነ ገብረክርስቶስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኢታ ሆነው ሲመደቡ፣ ዶ/ር ካሱ ኢላላ በእግራቸው እንዲተኩ የተደረጉት ለአቶ መለስ ባላቸው ታማኝነትና ህክምና ለመከታተል በሚመላለሱበት ወቅት ሚስጢር እንደሚጠብቁ ታምኖባቸው ነው።

አምባሳደር ብርሀኔ አምባሳደር ሆነው ብራሰልስ በነበሩበት ወቅት ይኖሩበት የነበረውን ቤት 360 ሺ ዩሮ በማውጣት በፈረንሳይ አገር በታወቁ የቤት ውስጥ ዲዛይነሮች አስውበው እንደነበረ ምንጮች ተናግረዋል። የአቶ መለስ የጤና ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሳሳቢ እየሆነ እንደመጣ ምንጮች ጠቁመዋል። አቶ መለስ ለመደበኛ ምርመራ በየሶስቱ ወሩ ብራሰልስ የግል ወይም ቻርተርድ አውሮፕላን ተከራይተው የሚመላለሱ ሲሆን ፣ የኢምባሲ ሰራተኞች እንኳ ስለ ጉዞአቸው ምንም አይነት መረጃ እንዳይኖራቸው ይደረጋል።

 ሆኖም ግን በኢምባሲው ውስጥ የሚሰሩ የተወሰኑ የአንድ ብሄር ተወላጆች አቶ መለስ ወደ ብራሰልስ ከማቅናታቸው በፊት  መረጃው አስቀድሞ እንደሚሰጣቸው የኢምባሲው ምንጮች ገልጠዋል። ከሁለት አመት በፊት የአቶ መለስን ብራሰልስ ለህክምና መመላለስ የግንቦት7 ራዲዮ በመዘገቡ ምክንያት አንድ የፊሊፒናዊ ዜግኔት ያላት የአምባሳደር ብርሀኔ ምግብ አዘጋጅና አንዲት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ ሚስጢር አሳልፋችሁ ሰጥታችሁዋል በሚል ተወንጅለው ከስራ መባረራቸው ተዘግቦ እንደነበር ይታወሳል።

አቶ መለስ ዛሬ ጠዋት ብራሰልስ ከገቡ በሁዋላ ሀኪማቸው ጋር እስከተገናኙበት ከሰአት በሁዋላ ድረስ ቀደም ሲል አምባሳደር ብርሀኔ ባሳደሱት ቤትና አሁን ካሱ ኢላላ በሚኖሩበት የአምባሳደሩ መኖሪያ ተኝተው እንደዋሉ ምንጮች ገልጠዋል። የአቶ መለስ በፍጥነት ወደ ብራሰልስ መምጣታቸውም ከሰሞኑተቃውሞ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ምንጮች ጠቁመዋል።

አቶ መለስ  ከጤናቸው ጋር በተያያዘ ከሶስት አመታት በሁዋላ ስልጣናቸውን ሊለቁ ይችላሉ የሚሉ ዘገባዎች እየቀረቡ ቢሆንም፣ ኢህአዴግ  አቶ መለስ በስልጣናቸው እንዲቀጥሉ ማስታወቂያ ማስነገር መጀመሩ የኢህአዴግን አባላት ሳይቀር ግራ እያጋባ ነው።

አቶ መለስ  በአእምሮ እጢ በእንግሊዝኛው አጠራር ብሬን ቲሞር በሽታ እንደሚሰቃዩ ይታወቅ እንጅ የበሽታው የአሳሳቢነት ደረጃ ምን ያክል እንደሆነ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። አቶ መለስ ከአምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስ ቀጥሎ ወዳጅ አድርገው የሚያቀርቡት ዶ/ር ካሱ ኢላላን እንደሆነ ይነገራል።
አቶ በረከት ስምኦንም በአእምሮ በሽታ እንደሚሰቃዩ ፣ ከምርጫ 97 በሁዋላ በደቡብ አፍሪካ ተገኝተው ህክምና ሲከታተሉ እንደነበር ይታወቃል። በቅርቡ ሼህ ሙሀመድ አላሙዲን አቶ በረከት በደቡብ አፍሪካ ህክምና ሲከታተሉ ወጪያቸውን እንደሸፈኑላቸው መናገራቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment