Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Saturday, June 9, 2012

የጣት አሻራ መረጃን ለደህንነት ተግባር ለመጠቀም ታቅዷል

ኢሳት ዜና:-
የኢትዮጽያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የግብር ከፋዮች መለያ ቁጥርን በጣት አሻራ ለማስደገፍ ባለፉት ሶስት ዓመታት እየሰበሰበ ያለውን በፎቶግራፍ የተደገፈ የአሻራ መረጃ ከታለመለት ዓላማ ውጪ ለአገሪቱ ደህንነት ተቋም ሥራ ለማዋል ዕቅድ መኖሩን አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ገለጹ፡፡

ባለሥልጣኑ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም የጣት አሻራ መሰብሰብ ሲጀምር ታሳቢ አድርጎ የነበረው የታክስ ሥርዓቱን ዘመናዊ በማድረግ ንግድ ውስጥ የሚገባውንና ያለውን በሙሉ መመዝገብና ግብር ከፋይ ማድረግ እንዲሁም በአንድ ሰው ስም ጭምር ተደጋጋሚ የንግድ ፈቃድ እያወጡ ግብር የሚሰውሩ አንዳንድ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ነበር፡፡በዚሁ መሰረት ሥራው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካለፈው ወር ድረስ የ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች የጣት አሻራ ከየመ/ቤቱ፣ከየቀበሌና ክፍለከተማዎች ተሰብስቦ፤ አብዛኛዎቹ ለ10 ዓመታት የሚቆይ የግብር ከፋይ መታወቂያ ደብተር እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ምንጫችን እንደሚሉት ይህንኑ መታወቂያ እንደብሔራዊ መታወቂያ ጭምር እንዲያገለግል በመወሰኑ በአሁኑ ሰዓት መታወቂያውን የያዙ ሰዎች እንደቀበሌ መታወቂያ በሰፊው የሚጠቀሙበት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል የሁሉም ዜጋ አሻራና ፎቶ ቀስበቀስ በዳታ ስለሚያዝ ወደፊት መረጃውን ለደህንነት ጉዳይም ለመጠቀም ዝግጅቱ መኖሩን ጠቁሟል፡፡ሆኖም ይህ ጉዳይ ለዜጎች ግልጽ አለመደረጉንም አመልክቷል፡፡

ባለስልጣኑ እስካሁን ከሰበሰበው አሻራ ውስጥ ወደ 2ሺ ተኩል ያህሉ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጽያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መሆኑ ታውቋል፡፡ ገዢው ፓርቲ እያንዳንዱን ዜጋ ለመቆጣጠር የሚያመች አሰራር መዘርጋቱንም ምንጫችን ጠቁመዋል። የጣት አሸራ ተግባራዊ እንደሆነ በርካታ ነጋዴዎች ተቃውሞ ማንሳታቸው ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment