ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በሜጋ ኪነጥበባት ኀ/የተ/ግ/ማ እና በቀድሞ ስራአስኪያጁ
አቶ ዕቁባይ በርሄ ላይ በመሰረተው ክስ መሰረት አቶ ዕቁባይ አራት ዓመት ከአምስት ወራት ቅጣት ከተላለፈባቸው በኋላ
ቅጣቱ በገደብ ተደርጎላቸው ተለቀዋል። የባለስልጣኑ መለቀቅ የፍትህ ሥርዓቱ አድሎአዊነት በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን አንድ የሕግ ባለሙያ ገለጸዋል፡፡
የባለስልጣኑ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ መሰረት የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አስረኛ ወንጀል ችሎት
ጉዳዩን ሲመለከት ቆይቶ ተጠርጣሪዎቹ በሁሉም ክሶች ጥፋተኛ ናቸው ያላቸው ሲሆን ድርጅቱም ሆነ ግለሰቡ ጥፋተኛ
የተባሉበት አንቀጾች የ15 ዓመት ጽኑ እስራትና የ50 ሺ ብር መቀጫን የሚያስከትሉ ቢሆንም ባልተለመደ መልኩ አቶ
ዕቁባይ 12 እርከን ዝቅ ያለ ቅጣት ማለትም አራት ዓመት ከአምስት ወራት ፍ/ቤቱ ከማስተላለፉም በተጨማሪ ቅጣቱም
በገደብ እንዲያዝላቸው ትላንትና የሰጠው ውሳኔ የፍትህ ስርዓቱን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል አሳዛኝ ውሳኔ ነው ሲሉ
ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከዚህ በፊት ከሰሳቸው ሰዎች መካከል አይኤምአፍ በመባል የሚታወቁት አራጣ
አበዳሪ አቶ አየለ ደበላ ከፍተኛ ተደራራቢ ሕመም እንዳለባቸው በቅጣት ማቅለያነት አቅርበው እንደነበር ባለሙያው
አስታውሶ ነገር ግን እሳቸው በዚህ ምክንያት ቅጣቱ በ12 እርከን ቀርቶ በስድስትም ዝቅ ሊልላቸው አልቻለም፡፡
አቶ ዕቁባይ ግን የሥርዓቱ ቁንጮዎች አንዱ በመሆናቸው፤ የሳንባ ሕመምተኛ መሆናቸው ተረጋግጧል በሚል እንደትልቅ
የቅጣት ማቅለያ ፍ/ቤቱ መያዙ የፍ/ቤቶች ነጻነት የይስሙላ መሆኑን ከማሳየት ባለፈ በዜጎች መካካል አድልኦ መፍጠሩ
እጅግ እንደሚያሳዝን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህግ ለዳኞች ሕሊና የሚተወው ነገር መኖሩን የጠቀሱት ባለሙያው እንደአገር ግን አንዱን 15 እና 20 ዓመት እየቀጡ ሌላውን በአራት ዓመትና በገደብ መልቀቅ ለፍትህ ሥርዓቱ ትልቅ ኪሳራ ነው ብለዋል፡፡
የሜጋ ኪነጥበባት ከ1997-2000 ዓ.ም ድረስ ገቢን አሳውቆ ግብርን ባለመክፈልና አትራፊ ድርጅት ሆኖ ሳለ እንደከሰረ በማስመሰል የንግድ ትርፍ ግብር ባለማስታቅና የተጭበረበረ መረጃ በማቅረብ ወንጀል መከሰሱ የሚታወስ ነው፡፡
አቶ ዕቁባይ ግብርና ታክስ በዚህ መልኩ ሲያጭበረብሩ የቅርብ አለቃቸው የሜጋኔት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጇ የአቶ መለስ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን እንደነበሩም ይታወቃል፡፡
ወ/ሮ አዜብ ግን በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጠያቂ አልሆኑም ነበር።
No comments:
Post a Comment