Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Thursday, September 13, 2012

በሊቢያ የአሜሪካ አምባሳደር ተገደሉ።

ኢሳት ዜና:- በሊቢያ ምሥራቃዊ ግዛት በቤንጋዚ በሚገኘው የ ዩናይትድ ስቴትስ ቆንስላ ታጣቂ ሚሊሺያዎች ድንገት በከፈቱት ጥቃት  በአሜሪካ የሊቢያ አምባሳደርን ጨምሮ አራት የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ተገደሉ።

ቢቢሲ እንደዘገበው፤ታጣቂዎቹ፤አምባሳደር ክርስቶፈር ስቴቨንስ እና ሦስት ሌሎች የዩናይትድስቴትስ ባለስልጣናትን የገደሉት፤ አሜሪካ ውስጥ በተዘጋጀና የነቢዩ መሀመድን ታሪክ ያጎደፈ ነው ባሉት ፊልም ምክንያት ተተቃውሟቸውን ለመግለጽ ነው።


የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት እስካሁን ያረጋገጠው የአምባሳደሩን ሞት ሲሆን፤ ስለ ሌሎቹ  ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል። በካይሮ በተመሳሳይ በፊልሙ የተቆጡ ተቃዋሚዎች ግብጽ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

በቤንጋዚ በተፈጸመው ጥቃት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች መሬት ለመሬት እየተኮሱ ወደ ኤምባሲው ከመግባታቸውም ባሻገር፤ በቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ቅጥር ግቢ የእጅ ቦንብ ወርውረዋል። የሊቢያ የደህንነት ሀይሎች በስፍራው በመድረስ ተኩስ የከፈቱ ቢሆንም፤ ተደራጅተው የመጡትን ታጣቂዎቹ ጥቃት ለመቋቋም ሳይችሉ ቀርተዋል።

የሊቢያ ባለስልጣናት አምባሳደር ክርስቶፈር ስቲቨንስ በጥቃቱ እንደተገደሉ ገልጸዋል። የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሄላሪ ክሊንተን በበኩላቸው የ አምባሰደር ክርስቶፈርን ሞት እንዳረጋገጡ በመጥቀስ፤ “በተፈፀመው ነገር ልባችን በሀዘን ተሰብሯል” ብለዋል።

“አንዳንዶች ይህን የነውጠኝነት ድርጊት በኢንተርኔት ለተሰራጨ  ቆስቋሽ የሆነ ማቴርያል እንደ አፀፋ ቆጥረውታል” ብለዋል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ።ሂላሪ ክሊንተን አክለውም፦”ዩናይትድስቴትስ በማናቸውም ሀይማኖቶች ላይ የሚፈጸሙ ማንቋሸሾች እንዲቆሙ ዓለማቀፍ ጥረቷን ትቀጥላለች።ነገር ግን አንድ ነገር ግልጽ መሆን አለበት። ለዚህ ዓይነቱ የነውጥ ድርጊት ምንም ዓይነት ምክንያት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም” ብለዋል።

የቢቢሲ ዘጋቢ  ራና ጁዋድ  ከትሪፖሊ  እንዳጠናቀረችው፤አንሳር አል ሻሪያ ተብሎ የሚጠራ የታጣቂዎች ቡድን በጥቃቱ ተሳትፏል።ቡድኑ ግን ‘በጥቃቱ እጄ የለበትም’በማለት ዘገባውን አስተባብሏል።

No comments:

Post a Comment