Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Friday, September 28, 2012

በደቡብ ክልል ” መለስ ዜናዊ እንኳን ሞተ” ብለው ተናግረዋል የተባሉ 80 ሰዎች ታሰሩ

ኢሳት ዜና:-በደቡብ ኦሞ ዞን በደቡብ አሪ ወረዳ የሚገኙ አርሶአደሮች፣ ” መለስ ዜናዊ እንኳንም ሞተ፣ አናዝንም” በማለት ሲናገሩ ተሰምተዋል በሚል ነው የወረዳው አቃቢ ህግ ክስ ያቀረበባቸው። የክስ መዝገቡ እንደሚያመለክተው አርሶ አደሮቹ በኢፌዲሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 4 /86 ሀ ላይ የተደነገገውን ተላልፈዋ ል። 


በመዝገብ ቁጥር 4103/30/2004 ፣ በ ቀን ጻጉሜ 1፣ 2004 በተጻፈው የክስ ቻርጅ ላይ የሰፈረው የወንጀሉ ክስ ዝርዝር ይዘት እንደሚያመለክተው ተከሳሾቹ በ18/ 12 /04 ዓም እለቱ አርብ ጧት 3 ሰአት ላይ በጎይዳመር ቀበሌ ውስጥ አቶ ገዛሀኝ ሀሞሾ ቤት ውስጥ ሀዘንተኛ ለማጽናናት በተሰበሰቡበት 4ቱም ተከሳሾች አንድ ላይ ሆነው “መለስ እንኳን ሞተ አናዝንም፣ መንግስት ሞቷል፣ መንግስት የለም” በማለት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መንግስት እንደሌለ በማሰብ ህዝብ ለማናወጥ በሚችል ሁኔታ ህዝብን በማሳሳት ወንጀል “ተከሰዋል ይላል።ከሸንቃማ ቢሊ፣ ሸንጋማ ወሰት፣ ሌጠር፣ አመር፣ ጉመር ፣ አይዳና ከነአመር ከሚባሉ ቀበሌዎች ወደ ጋዘር ፖሊስ ጣቢያ ከታሰሩት 80 የሚሆኑት ገበሬዎች መካከል አብዛኞቹ ከሳምንታት እስር በሁዋላ ክሳቸው ተቋርጦ በከፍተኛ መስጠንቀቂያና በገደብ የተለቀቁ ሲሆን፣ አቶ ገረሱ ጭሊ የተባሉ የአንድነት ፓርቲ አባል ከስምንት ቤተሰቦቹ ጋር ታስረው የስድስት ወራት እስር ተፈርዶባቸዋል። የአቶ ገረሱ ሌሎች ቤተሰቦቻቸውና ከእስር ሲለቀቁ እርሳቸውና አንድ ወንድ ልጃቸው የስድስት ወር እስራት እንደተፈረደባቸው የደቡብ ኦሞ ዞን አንድነት ፓርቲ ተጠሪ የሆኑት አቶ ስለሺ ጌታቸው ለኢሳት ገልጠዋል ።

ውድ ተመልካቾቻችን እና አድማጮቻችን ይህንን አስገራሚ ክስ በተመለከተ የክስ ቻርጁን በኢሳት ድረገጽ ላይ የምናወጣው በመሆኑ ድረገጻችንን እንዲጎበኙት እንጋብዛለን። ከዚሁ ዞን ዜና ሳንወጣ 13 የጂንካ ከተማ ተማሪዎች የተቃውሞ ድምጽ አሰማችሁ በሚል መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

በወጣት ናትናኤል ጳውሎስ የክስ መዝገብ የተከሰሱት ወጣቶች መታፈሪያ ታዲዮስ፣ ናትናኤል ጳውሎስ፣ ወንድወሰን ካሳ፣ ፍሬው በቀለ፣ ተመስገን ወንድም አገኘሁ፣ ሰለሞን ደጀኔ፣ ተስፋነህ ጋተው ፣ በረከት ደሴ፣ በረከት ታደሰ፣ ፍጹም መተው፣ ማስረሻ በለጠ፣ መኳንንት ወሌ እና መላኩ ካሳሁን ናቸው።

የክሱ ርእስ እንደሚያመለክተው ወጣቶቹ የተከሰሱት” የተከለከሉ ቦታዎችን በመድፈር እና የስራ ማስቆም ” በማድረግ ወንጀል ነው።  ” ማን ” የተባለ የአስፓልት ተቋራጭ ድርጅት በከተማው ያለውን መንገድ በማፍረስ በአስቸኳይ ለመስራት ባለመቻሉ ወጣቶች ተቃውሞአቸውን በዞኑ መስተዳድር አጥር ላይ ተንጠላጥለው ተቃውሞአቸውን በማሰማታቸው ፣ የማይደፈረውን ቦታ ደፈራችሁ” የሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው አቶ ስለሺ ተናግረዋል::

No comments:

Post a Comment