Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, April 11, 2012

በዘጠኙም ክልሎች የሰፈራ ፕሮግራም ይካሄዳል

By Ethiopian reporter 

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች የቦታ እጥረት እስካልተከሰተ ድረስ የሰፈራ ፕሮግራም የሚቀጥል ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በማደግ ላይ ናቸው በሚባሉት ክልሎችም በሦስት ዓመት ውስጥ 200 ሺሕ የሚጠጉ ቤተሰቦችን በመንደር ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡ በአራቱ ክልሎች የሚካሄደው የሰፈራ ፕሮግራም በክልሎቹ ውስጥ ብቻ ራሱን ችሎ የሚካሄድ እንጂ፣ እንደቀድሞው የሰፈራ ፕሮግራም ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል የሚሻገር አይደለም ተብሏል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል በአራቱ ትላልቅ ክልሎች የተካሄደው የሰፈራ ፕሮግራም ውጤት አስገኝቷል፡፡ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎች ተበታትነው የሚገኙ በመሆኑ፣ የመሠረተ ልማት ለማሟላት አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም የመሠረተ ልማት ለማሟላት እንዲቻል ሕዝቦቹን በመንደር ማሰባሰብ አስፈልጓል ሲሉ አቶ ምትኩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በተካሄደው የሰፈራ ፕሮግራም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች 1.3 ሚሊዮን ሰዎች ሰፍረዋል፡፡ አቶ ምትኩ እንደገለጹት፣ ከእነዚህ ሰፋሪዎች ውስጥ 99 በመቶዎቹ የምግብ ዋስትናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በዚህ መሠረትም በአራቱ ክልሎች በ2004 ዓ.ም. ከ69 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ለማስፈር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ከመሆኑም በተጨማሪ በ2005 ዓ.ም. ፕሮግራሙ እንደሚቀጥል  አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ አራት ክልሎች የሚካሄደው ሰፈራ በዝናብ እጥረትና በአካባቢ መራቆት ምክንያት በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ አባወራዎችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም አባወራዎቹ በሌሎች አካባቢዎች ለመስፈር ፈቃደኝነታቸው ሲረጋገጥ የሚካሄድ ነው ተብሏል፡፡

በቤንሻንጉልና በጋምቤላ ክልሎች ባለፈው ዓመት ነዋሪዎችን በመንደር የማሰባሰብ ሥራ ተጀምሯል፡፡ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኡምድ ኡቦንግ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 45 ሺሕ ሰዎችን በመንደር ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ በየዓመቱ 15 ሺሕ ሰዎችን ለማስፈር የሚያስችሉ ተግባሮች እየተከናወኑ መሆናቸውን አቶ ኡምድ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ታዳጊ የሚባሉት አራት ክልሎች ነዋሪዎቻቸው ተበታትነው የሚኖሩ በመሆኑ ክልሎቹ ለሕዝቦቻቸው ጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤት፣ ውኃና የመሳሰሉ ግንባታዎችን ለማካሄድ ተቸግረው መቆየታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ፕሮግራሙ እነዚህ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ዕቅድ እንዳለው ታውቋል፡፡

አቶ ምትኩ እንደሚሉት፣ በሰፈራ ፕሮግራሞቹ የምግብ ዋስትና ችግሮችን ማስወገድ የሚያስችሉ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡
በተያዘው ዓመት የበልግ ዝናብ ከየካቲት ወር ጀምሮ መጣል ቢኖርበትም ዝናቡ መጣል የጀመረው በመጋቢት ወር ሦስተኛው ሳምንት ላይ ነው፡፡ የምርት ዘመኑ የበልግ ወቅት የዝናብ መዛባት ችግር ያስከትላል ቢባልም፣ በቦረናና በጉጂ ዞኖች ጥሩ ዝናብ በመጣሉ ለግጦሽ የሚሆን ሳር ይገኛል ተብሏል፡፡
በዚህ ምክንያት ባለፈው ጥር ወር በአገሪቱ የምግብ ዋስትና ችግር አለባቸው ከተባሉት 3.2 ሚሊዮን ሰዎች ውጭ የተለየ የተረጂዎች ቁጥር ይኖራል ተብሎ እምብዛም አይጠበቅም፡፡ እርግጠኛ መሆን የሚቻለው ግን በሰኔ ወር የዳሰሳ ጥናት ከተካሄደ በኋላ መሆኑን አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡ 

በግብርና ሚኒስቴር ሥር የሚተዳደረው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ዘርፍ 206 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እህል ከአምና ተላልፎለት በእጁ እንደሚገኝና በመጠባበቂያ እህል ክምችት ኤጀንሲ ደግሞ 180 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እህል እንዳለ ተገልጿል፡፡

No comments:

Post a Comment