By አቤ ቶኪቻው
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የትንሳኤ በዓል ሊመጣ ሳምንት የማይሞላ ግዜ ቀርቶታል። እስቲ በሰላም ያምጣውና ሌላው ቢቀር እንኳን አደረሳችሁ ለመባባል ያብቃን።
አሁን ህማማት ላይ እንገኛለን። በሀይማኖቱ የበቁ ወዳጆቻችን እንደሚነግሩን በዚህ ሰሞነ ህማማት ውስጥ ያሉ
እያንዳንዱ ቀናት ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ የደረሰበት ስቃይ የሚታሰብባቸው ናቸው። በተለይም ኢየሱስ በአደባባይ ቆሞ
ባስተማረ እና በተናገረ ግዜ የደረሰበት ስቃይ፤ ከአጓጉል ውንጀላ አንስቶ ግርፋት፣ እስራት፣ በመጨረሻም ስቅላትን
ያካተተ ነበር። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በኋላ እሁድ ትንሳኤ ይሆናል። ደስታም ይበዛል።
ከመንፈሳዊው ጉዳይ ፊታችንን ዘወር ስናደርግ የሚከተለውን እናገኛለን፤ ኢህአዴግ አዲሳባን እና መላውን አገሪቷን “ለሰፊው ህዝብ ጥቅም” ብሎ ከተቆጣጠረ ስንት አመት ሆነው? ግንቦት
ሲመጣ ሃያ አንድ አመት ይሞላዋል። (ደህና ጎርምሶ የለም እንዴ!?) አሁንማ ሚስት አምጡ ብሏል! አይሉኝም?
ከደርግ ጋር ሲነፃፀር የኢህአዴግ በትረ ስልጣኑን መያዝ እንደ አዲስ ኪዳን የቆጠሩት ብዙዎች ነበሩ። በተለይ
ለዲሞክራሲ ናፋቂዎች ትልቅ ተስፋ ፈንጥቆ ነበር። “የመናገር እና የመፃፍ ነፃነት ተከብሯል።” ተብሎ ታወጀ። እሰየው
ተባለ። “ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ይቻላል ተብሎ ተነገረ።” እንዲህ ነው እንጂ ብለን አደነቅን! “የነፃ
ገበያ ስርዓት ተግባራዊ ይሆናል” ተባለ። እልልል… ይህንን ሁሉ አለም የሚያሳዩን እነዚህ እነማን ናቸው? የሚል
ውዳሴ ጎረፈ። ህዝቤም በየ መስኩ ተሳትፎውን አሳየ።
ቀን ቀንን እየወለደ ሄደና ዛሬ ሀያ አንድ አመት ሞላን አዲስ ኪዳን ስንል ያሞካሸነውም ዘመነ ኢህአዴግም
በመግቢያው ያበሰራቸውን በሙሉ ረሳቸው። ችግር ረሀብ እና እርዛትም በዙ። ነፃ ገበያም ሆነ ነፃ ንግግር ተግባር
ላይ ጠፉ። ይልቁንም በአደባባይ ቆሞ መናገር ያስወነጅል ጀመር። እስራት እንግልት ምርመራውም በረከተ። በሁሉም
ዘንድ ስቃዩ በዛ! በርካቶችም አሉ፤ “ህማማቱ ገባ”
እውነትም ወዳጄ ኢህአዴግ አዲሳባ ሲገባ አዲስ ኪዳን ሆኗል ካልን አሁን ያለነው በርግጠኝነት ህማማቱ ላይ
ነው። ከህማማቱ ቀጥሎ ምን የሚከሰት ይመስላችኋል? እኔ ግን እላለሁ ትንሳኤ እየመጣ ነው! እናም በህማማቱ ላይ
ያላችሁ በሙሉ አይዟችሁ!
ለማንኛውም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ወዳጆቼ መልካም ሰሙነ ህማማት ይሁንላችሁ! ተግታችሁ “አቤት” በሉ!
No comments:
Post a Comment