Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Thursday, September 6, 2012

ኢሳት በአውስትራሊያ የተሳካ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት አደረገ


 

ኢሳት ዜና:-አርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን መርጃ እንዲውል በአውስትራሊያ ከተሞች ባካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ከ 115 ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ።

የሜልቦርን ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ ቡድን ባደረገለት ግብዣ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ባለፈው ኦገስት 12 ቀን አውስትራሊያ የገባው ተወዳጁ አርቲስት፤ በአምስት የአውስትራሊያ ከተሞች ማለትም በሜልቦርን፣ በሲድኒ፣  በአድላይድ፣ በብሪዝበንና በፐርዝ  እንዲሁም በኒውዝላንድ-ኦክላንድ ባካሄዳቸው ደማቅ ዝግጅቶች በድምሩ ከ 115 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ ችሏል።


ከዋሽንግተን ተነስቶ ከ 20 የበረራ ሰዓታት በሁዋላ ኦገስት 12 ቀን  ሜልቦርን የገባው አርቲስት ታማኝ በየነ፤ ለአንድ ሰዓት እንኳ ሳያርፍ ወዲያውኑ ወደ ሲድኒ በመብረር እና  በሲድኒ በተዘጋጀው  የኢሳት የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ በመገኘት ከ 10 ሺህ ዶላር አሰባስቧል።

ከሁለት ቀናት የሲድኒ ቆይታ በሁዋላ ወደ ሜልቦርን በመመለስ እንደገና ወደ አድላይድ ያቀናው አርቲስት ታማኝ፤በዚያም ተዘጋጅቶ በነበረው  ደማቅ ዝግጅት ከ 12 ሺህ ዶላር በላይ ለማሰባሰብ ችሏል።አብይ አፈወርቅ ከስፍራው እንዳጠናቀረው  ሪፖርት፤የአድላይድ ዝግጅት የተጠናቀቀው ከእኩለ-ሌሊት በሁዋላ ቢሆንም፤ ታማኝ በማግስቱ በብሪዝበን በሚደረገው ዝግጅት ላይ መድረስ ስለነበረበት፤ ለጥቂት ሰዓታት እንኳ ማረፍ አልነበረበትም።

የተከታታይ  ቀናት  ረዥም በረራና  የመድረክ ዝግጅት መምራት  ከእንቅልፍ ጋር ሲዳመር በሰውነት ላይ የሚያስከትለው ድካምና መዛል ከባድ ቢሆንም፤ ሰንቆት የሄደው እቅድ ከዚያ በላይ በመክበዱ ሁሉንም ተቋቁሞ  በእኩለ ሌሊት ወደ ብሪዝበን አምርቷል። ሲበር አድሮ በተያዘለት ሰዓት በብሪዝበን የተገኘው አክቲቪስት ታማኝ ፤  በዚያም በመራው አስደሳች ዝግጅት ከ 16 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ ችሏል።

የብሪዝበን ዝግጅት ከተጠናቀቀ ከጥቂት ሰዓታት ዕረፍት በሁዋላ ዳግም በሜልቦርን በሚጠብቀው ዝግጅት ላይ ለመገኘት ማልዶ ወደ ሜልቦርን የተጓዘው አርቲስት ታማኝ፤በዚያም ለ አንድ ሳምንት በጉጉት ሲጠብቁት ከነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጋር ስኬታማ ዝግጅት ማድረጉ ታውቋል።

በሜልቦርን የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ታማኝ ወደ ሥፍራው  ይደርሳል ተብሎ ከተጠበቀበት ከሰኣታት በፊት ዝግጅቱ ወደሚካሄድበት አዳራሽ ማምራታቸውን የሚያመለክተው  ከስፍራው የተላለፈው ሪፖርት፤እስከ 350 ሰው የሚይዘው አዳራሽ ሞልቶ  ተጨማሪ 150 ሰዎችን ለማስተናገድ መገደዱን አትቷል።

አርቲስት ታማኝ ወደ ስፍራው መድረሱ እንደተሰማም በአዳራሹ ውስጥ ሲጠባበቀው የነበረው እድምተኛ ወደ ውጪ በመውጣት በዝማሬና በእልልታ ደማቅ የጀግና አቀባበል  እንዳደረገለት ከቋጠሮ ድረ- ገጽ ላይ ያገኘነው ተከታዩ ቪዲዮ ያመለክታል።
የዝግጅቱ ግብረ ሀይል አስተባባሪ ሊቀ-መንበር በሆነው በጋዜጠኛ ሳምሶን አስፋው መክፈቻ ንግግር በተጀመረውና  እጅግ ደማቅ በነበረው በዚህ  የሜልቦርን ዝግጅት ላይ የታዋቂው ሰዓሊ የታምራት ገብረማሪያም “ያልታወቀው ጀግና” የሚል ስያሜ ያለው የቅብ ስራ ለጨረታ ቀርቦ  ፤ከብርቱና አጓጊ ፉክክር  በሁዋላ በላሊበላ ሬስቶራንት ባለቤት በአቶ አበራ አሸናፊነት ተጠናቋል።

አቶ አበራ ጨረታውን ያሸነፉት በ30 ሺህ ዶላር ሲሆን፤ ከትኬት ሽያጭና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ጋር ተደምሮ አጠቃላይ በሜልቦርን ከ 50 ሺህ ዶላር በላይ መሰብሰቡ ታውቋል። የሜልቦርኑ ዝግጅት ከተጠናቀቀ ከሁለት ቀናት በሁዋላ ወደ ፐርዝ ያቀናው አርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በዬነ፤ በዚያም በተደረገው  ደማቅና አስደሳች የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ከ 14 ሺህ ዶላር በላይ አሰባስቧል።

ከዚያም ወደ ሜልቦርን በመመለስ የመጨረሻውን ዝግጅቱን ለማካሄድ ወደ ኒውዚላንድ-ኦክላንድ ያቀናው ታማኝ፤ በኦክላንድ ባደረገው እጅግ የተዋጣለት ዝግጅትም ከ 18 ሺህ የ አሜሪካን ዶላር በላይ አሰባስቧል። በተጠቀሱት ከተሞች በተደረጉት የኢሳት የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች በአጠቃላይ ከ 115 ሺህ ዶላር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን፤  የ 64 ሰዓታት ተከታታይ በረራዎችን በማድረግ በዝግጅቶቹ ስፍራ እየተገኘ ፕሮግራሞቹን የመራው አርቲስት ታማኝ በየነም፤ ከ 21 ቀናት ቆይታ በሁዋላ ረቡዕ ዕለት ወደ ዋሽንግተን ተመልሷል።

ከወራት በፊት አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ፣ አርቲስት ሻምበል በላይነህ እና እርቲስትና ጋዜጠኛ ገሊላ መኮነን  ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ ፤ ለኢሳት ስኬታማ የገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራም  ማካሄዳቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment